ዘመን ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው የ636 ሚሊዮን ብር ትርፍ ከባለፈው ዓመት ትርፉ 86 በመቶ ዕድገት ያለውን መሆኑን ገለጸ፡፡
ባንኩ የ2011 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ከባለፈው ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ አገኘዋለሁ ብሎ በዕቅድ ከያዘው አንፃርም በ55 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ይጠቀሳል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ከባለፈው ዓመት የ293.5 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ ደግሞ 483.7 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ዘመን ባንክ ባለፉት 12 ዓመታት ውስጥ በአንድ ዓመት ውስጥ ዓመታዊ ትርፉን በ86 በመቶ ያሳደገበት ወቅት ያልነበረ በመሆኑ፣ የ2011 የሒሳብ ዓመቱ የትርፍ ምጣኔው በባንኩ ታሪክ በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡
በአጠቃላይ በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው ትርፍ መጠን በአንድ አክሲዮን የሚገኘውን ትርፍ 398 ብር አድርጎታል፡፡ በ2010 የሒሳብ ዓመት አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 286 ብር ነበር፡፡ ይህም 28.6 በመቶ አማካይ የትርፍ ግኝቱ አንፃር በ39.2 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን ያሳያል፡፡
ባንኩ በ2011 የሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከታክስ በፊት ዓመታዊ ትርፋቸውን በከፍተኛ ደረጃ ካሳደጉት ሁለት ባንኮች መካከል አንዱ አድርጎታል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ዓመታዊ ትርፉን 100 በመቶ በማሳደግ ተጠቃሽ የሆነው ደቡብ ግሎባል ባንክ ሲሆን፣ ሁለተኛው ከፍተኛ የትርፍ ዕድገት በ86 በመቶ ማሳደግ የቻለው ዘመን ባንክ ነው፡፡
ባንኩ በ2009 የሒሳብ ዓመት 368.4 ሚሊዮን ብር፣ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ 342.3 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ይታወሳል፡፡
የዘመን ባንክ ዓመታዊ የትርፍ መጠን ዕድገት በዚህን ያህል ደረጃ እንዲያድግ ካደረጉት ውስጥ፣ ባንኩ ባለፈው ዓመት ያደረገው የአመራር ለውጥና ስትራቴጂ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ባንኩ ወጪውን በመቀነስ ያደረገው ጥረት ለአትራፊነቱ አስተዋጽኦ እንዳበረከተም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ የባንኩ ዓመታዊ የብድር መጠንም ከባለፈው ዓመት በበለጠ ማደጉም ባንኩ ላገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል፡፡
የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አበበ ድንቁ (ዶ/ር) እንደጠቀሱትም፣ ‹‹ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 1.84 ቢሊዮን ብር ወጪ ይኖረዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ በዓመቱ ውስጥ በተሠራ የወጪ ቅነሳ መርሐ ግብሮች አጠቃላይ ወጪው 947 ሚሊዮን ብር እንዲሆን በማድረግ ትርፋማነቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሻሻል ረድቶታል፡፡››
ባንኩ ከሰጠው የአገር ውስጥና የውጭ አገር የባንክ አገልግሎት ዘርፎች 1.58 ቢሊዮን ብር ያገኘ ሲሆን፣ በዕቅድ ተይዞ ከነበረው 1.49 ቢሊዮን ብር ገቢ አንፃር የስድስት በመቶ ብልጫና ከቀዳሚው ዓመት የ39 በመቶ ወይም የ447 ሚሊዮን ብር ዕድገት የተመዘገበበት ገቢ እንደተገኘ የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ለተለያዩ ኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር መጠን 2.56 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የባንኩን የብድር ክምችት መጠን ወደ 7.7 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የሰጠው የብድር መጠን በቀዳሚው ዓመት ከሰጠው ጋር ሲመሳከር የ50.7 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለብድር ከዋለው ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሰጠው ብድር ነው፡፡ ብልጫ ያለውን የብድር መጠን ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በመስጠት ከሌሎች ባንኮች የተለየ ያደርገዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ከሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ 28 በመቶውን ይህ ዘርፍ ሲወስድ፣ ቀጣዩን ደረጃ ደግሞ የአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት 16 በመቶ፣ ትራንስፖርት 13 በመቶ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ባንኩ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት አንፃር በሒሳብ ዓመቱ ያገኘውን 371.1 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ የዘመን ባንክ አጠቃላይ ሀብት 14.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው ዓመት በ18 በመቶ ወይም በ2.2 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ለዚህም የተቀማጭ ገንዘብና የብድር ዕድገቶች ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ባንኩ በብድር ረገድ ያሳየው ዕድገት አመርቂ ሲሆን፣ ላለፉት አራት ዓመታት በአማካይ 1.8 ቢሊዮን ብር ዕድገት የተመዘገበና የዘንድሮው ዓመት ብቻውን 2.6 ቢሊዮን ብር በመሆን ከባለፈው ዓመት በንፅፅር ሲታይ የ50.7 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት ዓመት እንደነበር ተመልክቷል፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ደግሞ በ2010 ዓ.ም. ከነበረበት 10.2 ቢሊዮን ብር ወደ 11.6 ቢሊዮን ብር ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታልም በባለፈው ዓመት ከነበረው 1.1 ቢሊዮን ብር ወደ 1.4 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህም በ871.1 ሚሊዮን ብር ጨምሯል፡፡ የተፈረመ ካፒታልም ሁለት ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡
ባንኩ በኤቲኤም የሚጠቀሙ ደንበኞቹን እያሳደገ ከመሆኑ አንፃር በ68 ኤቲኤሞቹ እየሰጠ ባለው አገልግሎት በቀን በአማካይ ወደ 2.3 ሚሊዮን ብር በዓመት ደግሞ ወደ 859.9 ሚሊዮን ብር የክፍያ አገልግሎት የሰጠ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህ የአገልግሎት መስጫ ማሽን የቪዛና ማስተር ካርድ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች በመስጠት ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍ እንዲል የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደነበረው ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ የኢንተርኔት ባንኪንግም ከአሥር ሺሕ በላይ ለሆኑ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
የተንቀሳቃሽ ባንኪንግ ዘመን ባንክ ከሚታወቅባቸው መልካም የሆኑ የባንክ አገልግሎቶች አንዱ መሆኑን የሚጠቀሰው ይኸው ሪፖርት፣ በ2011 በሒሳብ ዓመት 3096 አገልግሎቶችን በዚሁ በተንቀሳቃሽ አገልግሎት ደንበኞቹን ደርሷል፡፡ በዚህም የ1.2 ቢሊዮን ብር ትራንዛክሽኖች ማካሄድ ችሏል፡፡ ደንበኞች ወደ ባንኩ መምጣት ሳያስፈልጋቸው አገልግሎቱን ባሉበት ሆነው ማግኘት የሚያስችላቸው አሠራር በኢንዱስትሪው ከመጀመርያ ጀምሮ የሚታወቅበት አገልግሎት ነው፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ አበይት ክንውኖቹ ስለመኖራቸው በሪፖርቱ ካካተታቸው ውስጥ፣ ባንኩ እየተጠቀመበት ያለውን የኮር ባንኪንግ ሲስተም ጊዜው በደረሰበት ቴክኖሎጂ ደረጃ የማሳደግ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በሥራ ላይ መዋሉ ነው፡፡ የግብይት መፈጸሚያ ማሽኖችን ወደ ሥራ እንዲያስገባ ከማስቻሉም በላይ የባንኩን የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎቶች ለማዘመን የሚያስችለውን ሥራ ሠርቷል፡፡ ባንኩ በ2011 ሒሳብ ዓመት የተንቀሳቃሽ የግብይት መፈጸሚያ ማሽን አገልግሎት በመጀመር የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ ባቀደው መሠረት፣ 160 የፓስ ማሽኖች በማስገባት ሥራ ማስጀመሩ ተገልጿል፡፡
ዘመን ባንክ በ2011 በሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የቅርንጫፎቹን ብዛት ኪዩስኮችን ጨምሮ ወደ 43 ከፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡