በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚገበያዩ የምርት ዓይነቶች አሥር መድረሳቸው ተገለጸ፡፡ የዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱን አሳታፊና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ምርት ገበያው እስካሁን ሲያገበያያቸው ከነበሩ ዘጠኝ የግብርና ምርቶች በተጨማሪ፣ ኑግ አሥረኛው የግብርና ምርት ሆኖ ከታኅሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በግብይት ሥርዓት ውስጥ መካተቱን አስታውቋል፡፡
ምርት ገበያው የኑግ ምርቱን በስፋት ለማገበያየት መረከቢያ ቅርንጫፎቹን በአዲስ አበባ ሳሪስ፣ በቡሬ፣ በነቀምት፣ በጎንደር፣ በኮምቦልቻ፣ በአሶሳና በፓዊ እንዳዘጋጀም ገልጿል፡፡ የግብርና ምርቶች በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ውስጥ መገበያየታቸው የኮንትሮባንድ ንግድንና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ እንዲሁም የወጪ ንግድን ለማሳደግ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኅዳር ወር 60,825 ቶን የተለያዩ ምርቶችን በ2.8 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን ገልጿል፡፡ በኅዳር ወር ከተገበያዩት ምርቶች ውስጥ 21,704 ቶን ቡና፣ 29,300 ቶን ሰሊጥ፣ 5,428 ቶን አረንጓዴ ማሾ፣ 3,310 ቶን ነጭ ቦሎቄ እንዲሁም 1,083 ቶን አኩሪ አተር ናቸው፡፡ በወሩ በምርት ገበያው ከተገበያዩት ውስጥ ቡና 36 በመቶኛ የግብይት መጠንና 50 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል፡፡
በወሩ የግብይት ቀናት ሁሉም የቡና ዓይነቶች ለግብይት ቀርበው በምርት ገበያው የግብይት መድረክ በ1.4 ቢሊዮን ብር የተገበያዩ ሲሆን፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና 63 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ በማስመዝገብ የመጀመሪያውን ደረጃ እንደያዘ ያሳያል፡፡ ከዚህ ውስጥ 13,557 ቶን ያልታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ862 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ የኢሉአባቦራ ቡና 29 በመቶ፣ የጊምቢ ቡና 24 በመቶ በመጠን ይዘዋል፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ 160 ሺሕ ቶን የታጠበ ቡናም 10.4 ሚሊዮን ብር ሲገበያይ፣ ከግብይቱ መጠን የጎደሬ ቡና 48 በመቶ፣ የሊሙ ቡና 31 በመቶና የሸካ ቡና 11 በመቶ ይዘዋል፡፡
የኅዳር ወር የቡና ግብይት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ3.7 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየም ተገልጿል፡፡ የወሩ ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ደግሞ ሲነፃፀር 1.1 በመቶ የግብይት መጠን እንዲሁም 0.51 በመቶ የግብይት ዋጋ ጭማሪ አስመዝግቧል ተብሏል፡፡ አማካይ ዋጋውም በ4.3 በመቶ ጨምሯል፡፡ በወሩ 1,815 ቶን ስፔሻሊቲ ቡና በ141 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም 6,172 ቶን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርብ ቡና በ375 ሚሊዮን ብር እንደተገበያየም ይኸው የምርት ገበያው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከቡና ሌላ በኅዳር ወር 29,300 ቶን ሰሊጥ በ1.2 ቢሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁመራ/ጎንደር ሰሊጥ 88 በመቶ በግብይት መጠንና 89 በመቶ በግብይት ዋጋ በማስመዝገብ ትልቁን ድርሻ ይዟል፡፡ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀርም በመጠን የ210 በመቶና በዋጋ ደግሞ 187 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳይ፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ42 በመቶና በዋጋ 50 በመቶ ቅናሽ እንደነበረው አመልክቷል፡፡
በቅርቡ በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያይ የተወሰነው አረንጓዴ ማሾ ደግሞ በዚህ ወር 5,428 ቶን ለግብይት ቀርቦ በ127 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡
እንዲሁም 3,310 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ64 ሚሊዮን ብር ግብይቱ ተፈጽሟል፡፡ የነጭ ቦሎቄ ግብይት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀርም በመጠን 146 በመቶ በዋጋ 125 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም አማካይ የግብይት ዋጋው በ24 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
በተጨማሪም 1,083 ቶን አኩሪ አተር በ16.18 ሚሊዮን ብር ሲገበያይ፣ የጎጃም አኩሪ አተር 67 በመቶ የግብይት መጠን፣ በዋጋ ደግሞ 71 በመቶ በማስመዝገብ ከፍተኛውን ድርሻ እንደያዘ ተጠቅሷል፡፡