Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ደቡብ ግሎባል ባንክ ከታክስ በፊት 284 ሚሊዮን ብር አተረፈ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ደቡብ ግሎባል ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን 100 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ገለጸ፡፡

ደቡብ ግሎባል ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የትርፍ 284 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኑረዲን አወል ገልጸው፣ ይህም ከባለፈው ዓመት አንፃር ሲታይ በ100 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው ብለዋል፡፡

በ2011 የሒሳብ ዓመት በዚህን ያህል ደረጃ የትርፍ ዕድገት ያስመዘገበ ባንክ ስላለመኖሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ ዓመታዊ ትርፍ መጠናቸው ከ500 ሚሊዮን ብር በታች ካስመዘገቡ ጥቂት ባንኮች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ ከታክስ በፊት የ100 በመቶ ዕድገት የታየበትን ትርፍ ከማስመዝገቡም ሌላ ከታክስ በኋላ ያስመገበውም የትርፍ መጠኑንም 98 በመቶ መሆኑ ታውቋል፡፡

የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር በንግግራቸው ‹‹ይህ የባንካችን ትርፍ ለየት የሚያደርገው ደግሞ በአንድ አክሲዮን ድርሻ የ32.3 በመቶ ገቢ ማስገኘቱ ነው፡፡ በቁጥር ሲተመንም ከአንድ የአክሲዮን ድርሻ 323 ብር ተገኝቷል ማለት ነው፤›› በማለት በሒሳብ ዓመቱ የተገኘውን ውጤት ገልጸዋል፡፡

በ2011 የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠናቸውን በዚህን ያህል ደረጃ ያሳደጉ ባይኖሩም፣ ከዚህ ቀደም በአንድ ዓመት ልዩነት ዓመታዊ ትርፋቸውን በከፍተኛ ደረጃ ካሳደጉት ውስጥ አንበሳ ባንክ 110 በመቶና ብርሃን ባንክ ደግሞ 163 በመቶ  ማሳደጋቸው ይታወሳል፡፡

ከነዚህ ባንኮች ሌላ ዓመታዊ ትርፉን በዚህን ያህል ደረጃ በማሳደግ የደቡብ ግሎባል ባንክ ተጠቃሽ ሊሆን ችሏል፡፡

ደቡብ ግሎባል ባንክ በዚህ ደረጃ ከተገለጸው የትርፍ መጠን ዕድገቱ ባሻገር በሌሎች አፈጻጸሞቹ የ2011 የሒሳብ ዓመት ካለፉት ዓመታት ከነበሩት የተለየ ውጤት ያገኘባቸው ስለመሆኑ ከዓመታዊ ሪፖርቱ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ባንኩ ከፍተኛ ዕድገት አግኝቼበታለው ብሎ ከጠቀሳቸው ውስጥ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ አንዱ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት የ64 በመቶ ጭማሪ ያሳየበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ባንኩ በ2011 መጨረሻ ላይ የተቀማጭ ገንዘቡን 3.52 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የገንዘብ አስቀማጮች ብዛት ባለፈው ዓመት ከነበረው በ47 በመቶ ከፍ ብሎ ከ134‚000 በላይ ደርሷል፡፡ ባንኩ ባለፈው ዓመት የነበሩት አስቀማጮች ቁጥር 91‚100 ነበር፡፡

ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለተሰማሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ያበደረው የብድር መጠን በ55 በመቶ በማሳደግ 2.45 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከዚህ የብድር ሥርጭት ውስጥ የውጭ ንግድ 34.64 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት 31.69 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን 11.30 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ 10.88 በመቶ በመውሰድ ቅድሚያውን ሥፍራ ሲይዙ ሌሎች ዘርፎች የተቀረውን 11.49 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡

ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ካለው የገበያ ሁኔታ አንፃር አዳጋችና ከፍተኛ  ፉክክር የሰፈነበት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ደቡብ ግሎባል ባንክ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በሒሳብ ዓመቱ 117 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማድረግ የዕቅዱን 97.5 በመቶ ማሳካት እንደቻለም የባንኩ ሪፖርት ያሳያል፡፡

ይህ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ባለፈው ዓመት አግኝቶት ከነበረው 45.4 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር የ159 በመቶ ከፍተኛ ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡ የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 5.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ሀብት ባለፈው ዓመት ከነበረው የ3.3 ቢሊዮን ብር ሀብት ጋር ሲነፃፀር የ68 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ባንኩ ዓመታዊ ገቢውን 695 ሚሊዮን ብር ያደረሰ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የባንኩ ሠራተኞች ቁጥር ቀድሞ ከነበረው 551 ወደ 730 ሲያድግ፣ በሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ አማካይነት ደግሞ 185 የሚሆኑ ሠራተኞች ባንኩን ያገለግላሉ፡፡ ደቡብ ግሎባል ባንክ በአሁኑ ወቅት 73 ቅርንጫፎች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች