Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የወጋገን ባንክ ከታክስ በፊት ትርፍ በ315 ሚሊዮን ብር ቀነሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ዕድሜ ካላቸው የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ወጋገን ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ፣ ካለፈው ዓመት ከ315 ሚሊዮን ብር በላይ ቀንሶ 735 ሚሊዮን ብር ሆነ፡፡ ባንኩ የ2011 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን የሚያመለክተው ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ ከታክስ በኋላ ያገኘው የትርፍ መጠን ባለፈው ዓመት አግኝቶት ከነበረው በ172.5 ሚሊዮን ብር ዝቅ ያለ ነው፡፡

ባንኩ በቀዳሚው 2010 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.05 ቢሊዮን ብር ማትረፉ ይታወሳል፡፡ ወጋገን ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ያሳየው የትርፍ መጠን  ከቀዳሚው ዓመት ቅናሽ ማሳየቱ አንድ አክሲዮን የሚያስገኘውን የትርፍ ድርሻ ቀንሶታል፡፡ በ2010 የሒሳብ ዓመት አንድ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ ድርሻ 365 ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ግን 256 ብር ሆኗል፡፡

ባንኩ ባለፈው ዓመት ከታክስ በፊት ትርፋቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካደረሱ ሦስት ባንኮች አንዱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ግን ትርፉ በዚህን ያህል ደረጃ በመቀነሱ ባለአክሲዮኖች ለምን የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል፡፡

በሌሎች የ2011 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሞቹም ከበፊቶቹ በተለየ ዓመታዊ ዕድገቱ ያነሰበት ምክንያት ማብራሪያ ተጠይቆበታል፡፡ ባንኩ የሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ የ14.8 በመቶ ዕድገት የታየበት ቢሆንም፣ ቀደም ሲል በየዓመቱ ያሳይ የነበረውን ያህል እንዳልነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በ2011 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 23.5 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዳለ የተገለጸ ሲሆን፣ ከቀደሙት ዓመታት ከነበረው ዕድገት ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው ተብሏል፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት ለብድር ያዋለው የገንዘብ መጠንም ቢሆን ጭማሪ ያሳየው በ1.6 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ባንኩ የብድር መጠኑም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 15 ቢሊዮን ብር ወደ 16.5 ቢሊዮን ብር ማደጉ ተገልጾ፣ በአንድ ዓመት ለብድር የዋለው ገንዘብ ከባንኩ የቀደሙ ዓመታት አፈጻጸምም ሆነ ከአቻ ባንኮች አንፃር ሲታይ አነስተኛ ብድር የሰጠበት ዓመት እንደሆነ በሪፖርት ቀርቧል፡፡

ባንኩ በ2010 የሒሳብ ዓመት ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ማበደሩ ይታወሳል፡፡ በ2009 የሒሳብ ዓመትም ከ3.3 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ብድር የሰጠ ከመሆኑ አንፃር፣ የ2011 አፈጻጸሙ ዝቅ ያለ መሆኑን ተመላክቷል፡፡

የሒሳብ ዓመቱን አፈጻጸም በተመለከተ ባንኩ ይፋ ባደረገው መግለጫ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዓባይ መሐሪ እንደተናገሩት፣ በ2010 የሒሳብ ዓመት 2.3 ቢሊዮን ብር የነበረው የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በ2011 የሒሳብ ዓመት የ9.4 በመቶ ዕድገት በማሳየት 2.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ጠቅላላ ካፒታሉም ከ3.8 ቢሊዮን ብር የ12.2 በመቶ ዕድገት በማሳየት 4.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ጭማሪ ያሳየው በ8.7 በመቶ ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የሀብት መጠኑ 29.8 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡ ባለፈው ዓመት የሀብት መጠኑ 27.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የባንኩ ትርፍ መጠን ማነስና በሌሎችም የታየው አፈጻጸም የባንኩን ባለአክሲዮኖች አስከፍቶ ነበር፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ላይም ይኸው ሐሳብ ተንፀባርቋል፡፡ ባንኩ አለበት የተባለው የተበላሸ የብድር መጠንም እንደሚያሳስባቸው ባለአክሲዮኖቹ ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ያሳየው አፈጻጸም በባንኩ አሠራር ላይ ችግር እንዳለ የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከቦርዱ በኩል ከተሰጠው አስተያየት መረዳት እንደተቻለው፣ በበፊቱ ቦርድና በማኔጅመንቱ መካከል ያለመናበብ ችግር መኖሩን ነው፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ ክፍተቶች በመታየታቸው ይህንን የማረም ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እንዲያውም የከፋ ችግር እንዳይፈጠር ብዙ ሥራዎች አለመከናወናቸው ተወስቷል፡፡

በተለይ  ባንኩ አለበት የተባለው የተበላሸ ብድር መጠን ከፍ እያለ መምጣቱ በአሳሳቢነት የሚገለጽ መሆኑን የተናገሩ አንድ ባለአክሲዮን፣ ‹‹ገንዘቡን ለማን ሰጥታችሁት ነው?›› እስከ ማለት ደርሰው ነበር፡፡

ስለዚህ ባንኩ አሁን ለደረሰበት ችግር ተናቦ ያለ መሥራትና ሌሎች ከአመራርና ከማኔጅመንት ጋር የተያያዙ ክፍተቶች መሆናቸውን፣ ይህንን ችግር በማረም የተሻለ ሥራ እንዲከናወን ቦርዱም ሆነ ማኔጅመንቱ ሊሠሩ ይገባል ተብሏል፡፡ ለዚህም አሠራሩን ማስተካከል ይኖርበታል በማለት አስተያየት የሰጡም አሉ፡፡

ወጋገን ባንክ በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ በሚኙት 361 ቅርንጫፎቹ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ በተጓዳኝም የደንበኞቹን ፍላጎት የበለጠ ለማርካት የወኪል ባንክና የኢንተርኔት የሞባይል፣ የክፍያ ካርድ (ኤቲኤም) እና የክፍያ መፈጸሚያ ማሽን (ፖስ) አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን በባንኩ መግለጫ ተወስቷል፡፡ የባንኩ የኤቲኤም ማሽኖች ቁጥር 249 የደረሰ መሆኑን፣ የክፍያ መፈጸሚያ ማሽኖች (ፖስ) ቁጥር ደግሞ 283 እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል ወጋገን ባንክ የቅርንጫፎቹን ቁጥር በመጨመርና አዳዲስ የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎቶችን በጥራትና በተደራሽነት በማሳደግ፣ ደንበኞቹን የበለጠ ለማርካት የሚያስችለውን አቅም የሚፈጥርለትን ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል፣ የኔትወርክና ደኅንነት ጥበቃ ሥርዓት በቅርቡ ገንብቶ በማጠናቀቅ ሥራ እንዳስጀመረ በመግለጫው አስታውቋል፡፡  

በአሁኑ ወቅት የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥር 3,285  ሲሆን፣ የሠራተኞቹ ቁጥር ደግሞ 4,510 ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች