ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርታቸውን ካቀረቡ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ዓባይ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ከግብር በፊት ያገኘው ትርፍ በዕቅድ ከያዘው በላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የባንኩን የ2011 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም አስመልክቶ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ የኋላ ገሠሠ እንደገለጹት፣ ባንኩ ከግብር በፊት ይገኛል ብሎ በዕቅድ የያዘው 526 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ 683 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህ የባንኩ የምንጊዜውም ከፍተኛ ትርፍ ሲሆን፣ ይህ ክንውን ካለፈው ሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ63 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡
በዚህም መሠረት የባንኩ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን 343 ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ በቀደመው ዓመት የአንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 284 ብር ነበር፡፡
በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 11.6 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን የገለጹት አቶ የኋላ፣ ይህም ከቀዳሚው የሒሳብ ዓመት የሁለት ቢሊዮን ብር ጭማሪ በመሰብሰብ የ21 በመቶ ዕድገት እንዳስመዘገበ ጠቅሰዋል፡፡
በተመሳሳይ የባንኩ ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ስለማደጉ ተገልጾ፣ በቀዳሚው ዓመት ከነበረበት የ60 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 462 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞችን ጨምሮ አጠቃላይ የባንኩ አስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው የ31 በመቶ ዕድገት በማሳየት 624,566 መድረሱንም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ የሰጠውን ብድር በተመለከተ አቶ የኋላ እንደገለጹት፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት የብድር መጠኑ ከቀዳሚው ሒሳብ ዓመት የ29 በመቶ ጭማሪ በማሳየት አጠቃላይ የብድር መጠኑ 7.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ባንኩ ለሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የብድር አገልግሎት የሰጠ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ንግድ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞች ያቀረበው የብድር መጠን የ36 በመቶ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚ ነው፡፡ ለአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት ያቀረበው የብድር መጠን 22 በመቶ ድርሻ በመውሰድ ይከተላል፡፡ ለኮንስትራክሽን ዘርፍና ለትራንስፖትና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፎች የቀረበው ብድር በቅደም ተከተል የ17 በመቶና የስምንት በመቶ ድርሻ ሲይዙ፣ በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የዋለው ብድር የ18 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡
ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር በተያያዘ ከዓባይ ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች እጥረት እንዳለባቸው ቢገለጽም፣ የብዙዎቹ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እያደገ መሆኑን ያሳያል፡፡ ዓባይ ባንክም የዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ረገድ ያገኘው ገቢ ከፍ ማለቱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ የባንኩ የዳይሬክተር ቦርድ ሪፖርትም፣ ‹‹ምንም እንኳን የውጭ ምንዛሪ ግኝት በከፍተኛ ውድድርና ተግዳሮቶች የታጠረ ቢሆንም፣ ባንኩ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ50 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ የውጭ ምንዛሪ ማፍራት ተችሏል፤›› ብሏል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ባንኩ የተለያዩ ሥልቶችን የተከተለ ሲሆን፣ ከእነዚህ ሥልቶች ውስጥ ለሁለት ተከታታይ ዓመት ተግባራዊ የተደረገው በዕጣ ደንበኞችን ለመሸለም የተደረገው ጥረት ተጠቃሽ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
ከወጪ ንግድ የሚመነጨውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ በትኩረት የተሠራበት ሲሆን፣ በዓመቱ ውስጥም በአጠቃላይ ከመነጨው የውጭ ምንዛሪ ከወጪ ንግድ የተገኘው የ84 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡ በስዊፍት ከተላለፉና ከውጭ ከተላኩ ገንዘቦች የተመዘገበው ድርሻ እንደ የቅደም ተከተላቸው የሰባትና የሦስት በመቶ ድርሻ ሲኖራቸው፣ ከቀሪዎቹ ምንጮች የተገኘው ውጭ ምንዛሪ ቀሪውን የስድስት በመቶ ድርሻ ይወስዳል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 15.1 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካፈለው ሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ23 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ የተከፈለ ካፒታል መጠኑን በ346 ሚሊዮን ብር ወይም በ26 በመቶ በማሳደግ 1.7 ቢሊዮን ብር ስለመድረሱ ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል 2.5 ቢሊዮን ብር እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ባለፈው ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ከነበረው የካፒታል መጠን የ36 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ባንኩ 1.8 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ይህም ካለፈው ሒሳብ ዓመት ክንውን ጋር ሲነፃፀር የ40 በመቶ ጭማሪ የታየበት ሆኗል፡፡ የባንኩ የዓመቱ አጠቃላይ ወጪ 1.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ29 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በአንፃሩ ለብድርና ሌሎች መጠባቂያ የዋለው ወጪ ካለፈው ዓመት የ17 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ተገልጿል፡፡
የአገልግሎት ተደራሽነቱን የሚያሰፉለትን የአገልግሎት መስጫ መዳረሻዎችን ቁጥር ከማሳደግ አንፃር ተጨማሪ 25 የገንዘብ መክፈያ ማሽኖችን (ኤቲኤም) ሥራ ያስጀመረ መሆኑን ተገልጿል፡፡
ከዚህም ሌላ በአሁኑ ወቅት የባንኩን የካርድ ባንኪንግ 100,133፣ የሞባይል ባንኪንግ 94,595 እና የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር ደግሞ 3,136 ደርሷል፡፡ ባንኩ የሠራተኞቹን ቁጥር 3,280 ያደረሰ ሲሆን፣ የቅርንጫፎቹ ቁጥርም 192 ነው፡፡