Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበጥላቻ ንግግርና በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕጋዊነት ጥያቄና ሥጋት እንዳላቸው...

በጥላቻ ንግግርና በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕጋዊነት ጥያቄና ሥጋት እንዳላቸው የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ራፖርተር አስታወቁ

ቀን:

ከሲቪልና ከፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ድንጋጌዎች ጋር ቅራኔ አለው ብለዋል

ብሔር ተኮር ውጥረትን የበለጠ በማባባስ ግጭት እንዳይቀሰቅስ ሥጋታቸውን ገልጸዋል

የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ለመገምገም የአንድ ሳምንት ቆይታ ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ልዩ ራፖርተር ዴቪድ ኬይ፣ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ የመረጃ ሥርጭት ለመከላከል በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕጋዊነት ጥያቄና ሥጋት እንዳላቸው አስታወቁ፡፡

- Advertisement -

በኢትዮጵያ ያደረጉትን ግምገማ ሰኞ ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል በተረቀቀው አዋጅ ላይ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል ስለመሆናቸው፣ በሕገ መንግሥቱ የተዘረዘሩት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ እንደሚተረጎሙ የሚደነግጉትን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(4) እና አንቀጽ 13(2) ድንጋጌዎች ረቂቅ አዋጁ እንደሚቃረን በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡ ልዩ ራፖርተሩ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ኢትዮጵያ ተቀብላ ካፀደቀችው ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ሰነድ (ICCPR) አንቀጽ 20(2) እና አንቀጽ 19(3) ድንጋጌዎች በተቃራኒ፣ የተለጠጡ መሠረታዊ አንቀጾችን እንደያዘ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን በአንቀጽ 20(2) ላይ መንግሥታት በብሔር፣ በዘርና በሃይማኖት ላይ መገለልን፣ እንዲሁም ግጭትን የሚያነሳሱ የጥላጫ ቅስቀሳዎችን (አድቮኬሲ) በሕግ መከላከል እንዳለባቸው የሚገልጽ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 19(3) ላይ መንግሥታት ይህንን ሕጋዊ ክልከላ ሲጥሉ፣ የመናገርና የሚዲያ ነፃነት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የሚገድቡ መርሆችን ማስቀመጡን ይገልጻሉ፡፡ ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከዚህ አንፃር ሲመዘን በእጅጉ የተለጠጠ፣ ለትርጉም ክፍት የሆነ፣ እንዲሁም ለችግሩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ሊያባብስ፣ የመናገርና የሚዲያ ነፃነትን ሊገድብ የሚችል መሆኑን ልዩ ራፖርተሩ አመልክተዋል፡፡

የረቂቅ አዋጁ መግቢያ የመናገር ነፃነት ገደብ የሚደረግበት ስለመሆኑ የሚገልጸውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በአመክንዮነት ሲያስቀምጥ፣ ኢትዮጵያ የተቀበለችውን ዓለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳንን አለመጥቀሱን በህፀፅነት አውስተዋል፡፡ ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ በሚሰጠው ትርጓሜ፣ “የጥላቻ ንግግር፣ መገለልና በሰዎች ላይ ጥቃት እንዲደርስ የሚያበረታታ ንግግር ምን ማለት እንደሆነ፣ በዚህ ድንጋጌ ውስጥ የሚወድቀው ምን ዓይነት ንግግር እንደሆነ በግልጽ የማያመለክት በመሆኑ፣ ሕግ አስከባሪዎችና አቃቢያነ ሕጎች በፈለጉት መንገድ እንዲተረጉሙት ዕድል ይሰጣል፤” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

 በተመሳሳይ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን በተመለከተ በረቂቅ አዋጁ ከተሰጠው ትርጓሜ ውስጥ፣ “ሐሰተኛ መረጃ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው” በማለት የተሰጠው ትርጓሜ፣ ከዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን አንቀጽ 19 ድንጋጌ ጋር የሚቃረን ነው ብለዋል፡፡

የቃል ኪዳን ሰነዱ አንቀጽ 19 የመናገር ነፃነትን በንግግሩ ወይም በመረጃው እውነተኛነት ፈጽሞ አይገድብም ብለው፣ ረቂቅ አዋጁ ግን በዚህ መልኩ የመናገርና የሚዲያ ነፃነትን ሊገድብ የሚችል ድንጋጌ መያዙን፣ እንዲሁም ሐሰተኛ መረጃን ሲተረጉም ‹‹ሐሰተኛ›› የሚለው ቃል ቋሚ ትርጉም እንዳለው ታሳቢ እንዳደረገ፣ ነገር ግን “ሐሰት” ቋሚ ትርጉም ሊኖረው እንደማይችል አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም ረቂቁ የሚጥለው የገንዘብና የእስር ቅጣት በእጅጉ የተጋነነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ የመረጃ ሥርጭትን ለመከላከል ያስፈለገበትን ምክንያት እንደሚረዱ ያስታወቁት ልዩ ራፖርተሩ፣ የችግሩ ምንጭ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርዓት የፈጠረው እንደሆነ እንደሚያምኑና መፍትሔውም ፖለቲካዊ ቢሆን እንደሚመርጡ ጠቁመዋል፡፡ ሕጉ አሁን ባለበት ሁኔታ የሚወጣ ከሆነ ግን ያለውን ብሔር ተኮር ውጥረትና ግጭት ሊያባብሰው እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ፓርላማው ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ሊፈትሸው እንደሚገባ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ውሳኔ አግኝቶ ለፓርላማ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ አባሪ ማብራሪያ ሰነድ ልዩ ራፖርተሩ ዴቪድ ኬይ ያነሷቸው የቃል ኪዳን ሰነዱ አንቀፆች አዋጁን ለማውጣት በአመክንዮነት ይጠቅሳቸዋል፡፡ ማብራሪያ ሰነዱ ኢትዮጵያ የተቀበለችው የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 19(3) ላይ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከኃላፊነት ጋር እንደሚመጣና በተለይም የሌሎችን መብት፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ሰላምን ለመጠበቅ ሲባል በሕግ ሊገደብ እንደሚችል በግልጽ መደንገጉን ያመለክታል፡፡ ከዚህም ባለፈ የስምምነቱ አንቀጽ 20 ላይ የስምምነቱ ፈራሚ አገሮች በብሔር፣ በዘር ወይም በሃይማኖት ላይ በመመሥረት ጥላቻን፣ ጥቃትና መድልኦን የሚያራግቡ ንግግሮችን በሕግ እንዲከለከሉ ግዴታ እንደሚጥል የማብራሪያ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለፓርላማ በቀረበበት ወቅት አስተያየት ከሰጡ የፓርላማ መካከል ከአንዱ በስተቀር፣ አዋጁ እጅግ የዘገየ ካልሆነ በስተቀር አስፈላጊ መሆኑን፣ እንዲሁም ቅጣቱ አነስተኛ በመሆኑ እንዲጠነክር መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የፓርላማው የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ ዝርዝር ምርመራ እያከናወነ መሆኑንና በቅርቡም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርግ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...