በምሥረታ ላይ የሚገኘው አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ የሚባለውን የባለአክሲዮኖች ቁጥር በመያዝ ወደ ሥራ ሳይገባ፣ 1.62 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በማስመዝገብ ቀዳሚ ባንክ ሆነ፡፡ የአክሲዮን ሽያጭ ጊዜውን በማራዘም ተጨማሪ ካፒታል ለማሰባሰብ አቅዷል፡፡
ባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ ጊዜውን ማራዘሙን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 1.62 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቋል፡፡ ቃል የተገባው ወይም የተፈረመ ካፒታል መጠን ደግሞ 2.13 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን፣ የባንኩ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ አስታውቀዋል፡፡ የተለያየ መጠን ያላቸው አክሲዮኖች የገዙ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ቁጥር፣ ከ31 ሺሕ በላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ አማራ ባንክ በአክሲዮን ሽያጭ አፈጻጸሙ፣ ሥራ ከመጀመሩ በፊት 1.63 ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ይዞ ኢንዱስትሪውን የሚቀላቀል የመጀመሪያው ባንክ ይሆናል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ካሉ የግል ባንኮች ከፍተኛ የሚባለውን ካፒታል ወደ ሥራ ይዞ የገባው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በ120 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ሌሎች የግል ባንኮች ከ120 ሚሊዮን ብር በታች በሆነ ካፒታል ወደ ሥራ የገቡ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ባንኮች በወቅቱ ሕግ ከሚፈቅደው የተከፈለ ካፒታል ወይም መጠነኛ ጭማሪ ይዘው የተነሱ ሲሆን፣ አማራ ባንክ ግን በአሁኑ ወቅት ሥራ ለማስጀመር ከሚጠየቀው 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በላይ በሦስት እጥፍ አሰባስቧል፡፡ በዚህም በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ባንኩ ወደ ሥራ ሲገባ 1.63 ቢሊዮን ብር ካፒታል በመያዝ የመጀመርያ ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በባለአክሲዮኖች ቁጥርም አማራ ባንክ የመጀመርያውን ደረጃ ለመያዝ ችሏል፡፡ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የባንኩን አክሲዮኖችን የገዙ 31 ሺሕ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሲሆኑ፣ ይህም ከፍተኛ ቁጥር ከሌሎች ባንኮች የተለየ አድርጎታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢንዱስትሪው ውስጥ ካሉ 16 የግል ባንኮች ውስጥ እናትና ብርሃን ባንክ የባለአክሲዮኖቻቸው ቁጥር 17 ሺሕ ከመሆኑ አንፃር፣ አማራ ባንክ በባለአክሲዮኖች ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ መሥራች ጉባዔውን የኅዳር ወር 2012 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ በፊት አደርጋለሁ ቢልም፣ እንዲራዘም አድርጎታል፡፡ በዚህ ምክንያት አሁንም የአክሲዮን ሽያጩን ለማራዘም መወሰኑ ተገልጿል፡፡ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫም ባንኩ ሽያጩን እስከ ታኅሳስ አራዝሟል፡፡ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በርካታ የማራዘሚያ ጥያቄዎች በመቅረባቸው፣ የአክሲዮን ሽያጭ ጊዜውንና መሥራች ጉባዔውን አራዝሟል፡፡ መሥራች ጉባዔውና የአክሲዮን ሽያጭ እንዲራዘም የተፈለገበት ምክንያት በሰብል ስብሰባ ላይ ያሉ አርሶ አደሮች አክሲዮን ለመግዛት ጊዜው እንዳነሳቸው መጠየቃቸው አንዱ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ዘርፍ የአክሲዮን ባለቤት መሆን የሚያስችላቸው አዲስ አዋጅ በቅርቡ የፀደቀ በመሆኑና የአክሲዮን ግዥ ጥያቄዎችን በማቅረባቸው፣ ለእነሱም ዕድል ለመስጠት ጭምር መሆኑን ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በእነዚህና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የጊዜ መጣበብ ያጋጠማቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማስተናገድ፣ ጊዜ መስጠት ተገቢ መሆኑን የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
አማራ ባንክ በይፋ የአክሲዮን ሽያጩን የጀመረው ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለውን የተከፈለ ካፒታል ያሰባሰበውም በሦስት ወራት ተኩል ጊዜ ውስጥ ነው፡፡