Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊልኳንዳ ነጋዴዎች ግብር ለመክፈልና ፈቃድ ለማደስ ተቸገርን አሉ

ልኳንዳ ነጋዴዎች ግብር ለመክፈልና ፈቃድ ለማደስ ተቸገርን አሉ

ቀን:

ለቀረበው አቤቱታ መልስ እስኪሰጥ በትዕግሥት ይጠብቁ

የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን

በአዲስ አበባ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ተመዝጋቢ የሆኑ ልኳንዳ ነጋዴዎች፣ የ2011 በጀት ዓመት ግብር ለመክፈልና በዚህም ፈቃዳቸውን ለማደስ የሚያስችላቸውን ክሊራንስ (ማስረጃ) ለማግኘት መቸገራቸውን ገለጹ፡፡ የሒሳብ አመዘጋገባቸው ባለፈው ዓመት በወጣው መመርያ መሠረት ካልተከናወነ በስተቀር የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ሊያስተናግዳቸው ፈቃደኛ ሆኖ አለመገኘቱን አመለከቱ፡፡

- Advertisement -

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሣህሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ነጋዴዎቹ እስከ 2010 ባሉት የበጀት ዓመታት ውስጥ ግብር ሲያስገቡና ባለሥልጣኑም ግብሩን ሲቀበላቸው የቆየው ነሐሴ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. በወጣው መመርያ መሠረት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የ2011 በጀት ዓመት ግብር በተለመደው መንገድ ለመገበር ሲሄዱ፣ ያልሰሙትና የማያውቁት ቁጥር 138/2010 ዓ.ም. በግምት ለመወሰን የሚያስችል አዲስ መመርያ መውጣቱ ተነግሯቸዋል፡፡

በተጠቀሰው በጀት ዓመት ከቫት የሰበሰቡትን ገቢ ማድረግ የሚገባቸው በአዲሱ መመርያ እንደሆነ፣ በፊት የተፈጸመውንም ውዝፍ ወይም የተጨማሪ እሴት ታክስ ልዩነቱንም መክፈል እንደሚጠበቅባቸው እንደተነገራቸው፣ ይህ ዓይነቱም አካሄድ ግርታ እንደፈጠረባቸው አቶ አየለ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ መመርያ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት፣ ከችግሮቹም መካከል ባለሥልጣኑ አዲስ መመርያ መውጣቱን ቀደም ሲል ለግብር ከፋዮች አለማሳወቁ፣ በዚህም የተነሳ አካሄዱ ዱብ ዕዳ እንደሆነባቸው፣ ነባሩ መመርያ ሳይሻር ሌላ አዲስ መመርያ ማውጣቱ ተገቢ አለመሆኑና መመርያው ሲወጣ ማኅበሩ እንዲሳተፍ አለመደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

መመርያው ግብር በግምት ስለሚሰበሰብበት ሁኔታ የወጣ እንጂ በግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 መሠረት ለተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ የማይውል መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ አብራተዋል፡፡

የማኅበሩ አባላት የቫት ተመዝጋቢ መሆናቸው እየታወቀና የሒሳብ መዝገብ ይዘው ላልቀረቡና በግምት ላይ የተመሠረተ አካሄድ ለሚከተሉ የወጣውን አዲስ መመርያ በቫት ተመዝጋቢዎች ላይ ለማስፈጸም የሚደረገው እንቅስቃሴ በዘርፉ የሚገኙ ነጋዴዎችን ከሥራ ሊያስወጣ የሚያስችል መንገድ ይከፍታል የሚል ሥጋት እንዳሳደረባቸውም ተናግረዋል፡፡

ነባሩና በ2006 ዓ.ም. የወጣው መመርያ፣ ነጋዴዎችን በሁለት ክፍሎች ይለያቸዋል፡፡ በአንደኛው ክፍል የተመደቡት በአነስተኛ እንዲሁም በሁለተኛ ክፍል የታቀፉት በከፍተኛ ዋጋ የሥጋ ምርት ለኅብረተሰቡ የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት አነስተኛ ነጋዴዎች ከአንድ በሬ ላይ 1053 ብር ከ15 ሳንቲም፣ መካከለኛና ከፍተኛ ነጋዴዎች ደግሞ ከአንድ በሬ 1975 ብር ከ15 ሳንቲም ተጨማሪ እሴት ታክስ እየሰበሰቡ ገቢ እንደሚያደርጉ አቶ አየለ ገልጸዋል፡፡

ከፍ ብሎ ለተጠቀሰው ችግር መፍትሔ እንዲፈለግለት ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለገቢዎች ሚኒስትር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ ለአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ ለንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ለንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ኅዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሑፍ እንዳሳወቀ፣ በዚህም የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለምክትል ከንቲባው፣ ምክትል ከንቲባው ደግሞ ለባለሥልጣኑ ጉዳዩን እንዳስተላለፍ፣ ባለሥልጣኑም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት መፍትሔ አለመስጠቱን አቶ አየለ አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አማካሪ ወ/ሮ ሠናይት ፀጋዬ ስለዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፣ ‹‹ማኅበሩ አቤቱታውን በጽሑፍ አቅርቧል፡፡ ባለሥልጣኑ መልስ እስከሚሰጥበት ድረስ በትዕግስት ይጠብቅ፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...