Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንብ ባንክ ከታክስ በፊት ከ928 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲስ የመዋቅር ማስተካከያ በማድረግና አዳዲስ አመራሮችን በመሰየም የ2011 የሒሳብ ዓመትን የጀመረው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ዓመታዊ ገቢውን በ34.5 በመቶ በማሳደግ በባንኩ ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን አስታወቀ፡፡

ባንኩ የ2011 የሒሳብ ዓመቱን አፈጻጸሙን ኅዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንዳስታወቀው፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ከ928.4 ሚሊዮን ብር በላይ አትርፏል፡፡

እንደ ባንኩ የዳሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ወልደ ተንሳይ ወልደ ጊዮርጊስ ገለጻ፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት የተገኘው ትርፍ ከቀዳሚ ዓመት በ269.7 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ከመሆኑም በላይ፣ በ20 ዓመታት ውስጥ ባንኩ ያስመዘገበው ከፍተኛ ትርፍ ሆኗል፡፡ ከታክስ በፊት የተገኘው ትርፍ የ41 በመቶ ዕድገት ያለው ሲሆን፣ ከታክስ በኋላ የተገኘው ትርፍም የ40 በመቶ ዕድገት በማሳየት 720.7 ሚሊዮን ብር ሊደርስ መቻሉ ተገልጿል፡፡

ይህ የትርፍ መጠን በሒሳብ ዓመቱ አንድ አክሲዮን ያስገኘውን የትርፍ መጠን ከፍ እንዲል አስችሏል፡፡ በቀዳሚው ዓመት 134 ብር ያስገኝ የነበረው አንድ አክሲዮን በ2011 የሒሳብ ዓመት ግን ወደ 154 ብር ከፍ ብሏል፡፡

ለባንኩ የትርፍ ዕድገት ባንኩ ያደረገው አዲስ የመዋቅር ማስተካከያዎችና አዳዲስ አሠራሮች የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደነበራቸው የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ሩጋ በበኩላቸው፣ አሁንም ባንኩን ሊያራምዱ የሚችሉ ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚተገበሩ አስታውሰዋል፡፡ ከዓመታዊ ሪፖርቱ መረዳት እንደተቻለው ደግሞ፣ ባንኩ ዓመታዊ ገቢውን በ34.5 በመቶ በማሳደጉ 3.3 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ በመቻሉ ለተሻለ አፈጻጸሙ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ያገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ856 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡

የሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ27.7 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከቀዳሚ ዓመት አንፃር አፈጻጸሙ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወይም የ28 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ታውቋል፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት በስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ያለው የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የተቻለው፣ ባንኩ አዳዲስ አስቀማጭ ደንበኞችና ቁጥር በ196,239 ማሳደግ በመቻሉ ነው፡፡ ይህም በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 679,178 የነበረውን የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር በ28.9 በመቶ በመጨመር ወደ 875,417 ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡

ባንኩ ለተለያዩ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠን በ41.9 በመቶ ማሳደግ ችሏል፡፡ በመሆኑም ባንኩ በአጠቃላይ የሰጠው የብድር ክምችት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 19.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ5.7 ቢሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት 11,626 የነበረው የተበዳሪዎች ቁጥር በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ወደ 13,136 ከፍ ስለማለቱ የባንኩ ሪፖርት ጠቅሷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ የተሰጠው የብድር ክምችት ከአጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር 70 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ባለፈው ሒሳብ ዓመት ከነበረው 63 በመቶ አኳያ የሰባት በመቶ መሻሻል አሳይቷል፡፡

የባንኩን የሀብት መጠን ዕድገትን በተመለከተም እንደተገለጸው፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 33.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 26.7 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ26.3 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይህ ጠቅላላ የሀብት መጠን በባንኩ የተሰጠን የብድር ክምችት፣ በእጅ ያለን ጥሬ ገንዘብ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባንኮች ያለን ተቀማጭ፣ በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠን መጠባቂያ፣ የባንኩን ቋሚ ንብረቶች፣ እንዲሁም በአክሲዮኖችና ሌሎች ቋሚ ንብረቶች ላይ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶችን የሚያጠቃልል እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡  

የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከአጠቃላይ የባንክ ካፒታል ውስጥ 60 በመቶውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ27.6 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 2.65 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ወደ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያድግ በተወሰነው መሠረት፣ በሒሳብ ዓመቱ እንዲሸጥ የታቀደው አክሲዮን መጠን ይህ ሪፖርት እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ ሙሉ ለሙሉ ተሸጦ እንደተጠናቀቀም ተጠቅሷል፡፡  

የባንኩ ዓመታዊ አጠቃላይ ወጪ 2.4 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ይህ ከቀዳሚ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ586.8 ሚሊዮን ብር ወይም የ32.1 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ የሚጠቁመው ይኼው ሪፖርት፣ ለባንኩ ዓመታዊ ወጪ ማደግ በዋናነት የተቀመጠው ወለድ የሚታሰብበት የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ነው፡፡ የጊዜ ገደብ ተቀማጭ ወለድ ምጣኔ መጨመሩ፣ በባንኩ የድርጅት መዋቅር ለውጥና የቅርንጫፍ ማስፋፊያ ሥራን ተከትሎ ተጨማሪ የሰው ኃይል ቅጥር መፈጸሙ፣ የቢሮ ሕንፃ ኪራይ ዋጋ መጨመሩና በአጠቃላይ የባንኩ የሥራ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱ ለወጪው መጨመር አስተዋጽኦ አድርገዋል ተብሏል፡፡

ንብ ባንክ በቀጣይ የበለጠ ሊሠራባቸው ካቀዳቸው ሥራዎች ውስጥ የደንበኞችን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለማርካት የሚያስችሉ አሠራሮችን መዘርጋት እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ገነነ ደግሞ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ፈታኝ ቢሆንም በዚህ ረገድ ደንበኞችን በተሻለ ለመደገፍ የተለያዩ አዳዲስ አሠራሮች ይተገበራሉ ብለዋል፡፡ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ 20 ዓመታትን በኢንዱስትሪው የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 4,972 ሠራተኞች ሲኖሩት የቅርንጫፎቹን ቁጥር 261 አድርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች