በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዲስትሪ ውስጥ ጉምቱ ከሚባሉ ጥቂት የኢንሹራንስ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑትና አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያን ላለፉት 25 ዓመታት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የመሩት አቶ ፀጋዬ ከምሲ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት እንዳገኘ ተገለጸ፡፡ በምትካቸውም ምክትላቸው አቶ ጉዲሳ ለገሠ የኢንሹራንስ ኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሰይመዋል፡፡
በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ45 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው አቶ ፀጋዬ፣ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት በቂ ተተኪዎችን ማፍራት በመቻላቸውና ከዚህ በኋላ ማረፍ አለብኝ በሚል ምክንያት እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የአቶ ፀጋዬን የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ቦርዱ ለመቀበል የዘገየ ቢሆንም፣ ለአንድ ዓመት በአማካሪነት እንዲሠሩ በማግባባት ላቀረቡት የመልቀቂያ ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ እንደተሰጠውም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
አቶ ፀጋዬ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የመጀመርያ ቅጥራቸው የሆነው ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ በመባል የሚታወቀው የግል ኩባንያ ነበረ፡፡ ከዚያ በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት ከኢንዱስትሪው ቢርቁም፣ ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ የመድን ድርጅት በመግባት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሠርተዋል፡፡ ከ1984 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያን ለመመሥረት ዝግጅት ሲደረግ ከፕሮጀክት ቀረፃው ጀምሮ ዋና ተሳታፊ በመሆን ሠርተዋል፡፡ ኩባንያው ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለ25 ዓመታት የኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ወደ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ከመቀላቀላቸው በፊት በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ለአራት ዓመት አስተምረው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አሁን በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን የለቀቁት አቶ ፀጋዬ፣ ለአንድ ዓመት በአማካሪነት ይሠራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ 25 ዓመታት ያለማቋረጥ ያገለገሉ ብቸኛው ባለሙያ በመሆንም ይጠቀሳሉ፡፡
በአቶ ፀጋዬ ምትክ ከ25 ዓመት በኋላ የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሁለተኛው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን በቦርዱ የተሰየሙት አቶ ጉዲሳ፣ ከ18 ዓመታት በላይ በአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመሥራት እስከ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ የደረሱ ናቸው፡፡
አዋሽ ኢንሹራንስን ከመቀላቀላቸው በፊት በሌሎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የሠሩት አቶ ጉዲሳ፣ በኢንዱስትሪው ከ22 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡