Tuesday, May 21, 2024

ግብፅ በአሜሪካ በኩል ለመፍጠር የፈለገችውን ጫና ለመግታት ኢትዮጵያ ምን ያህል ዝግጁ ነች?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የግብፅ መንግሥት ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የጀመረችው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በመቃወም፣ በኋላም ተቃውሞዋንና ሥጋቷን በውይይትና በድርድር ለመፍታት ስምንት ዓመታት የፈጀ ፈርጀ ብዙ ሙከራዎችን አድርጓል፡፡

ታላቁ ኢትዮጵያ ህደሴ ግድብ ግንባታ ይፋ በተደረገበት ወቅት የታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገር የሆነችው ግብፅ ከፍተኛ ተቃውሞ ስታሰማ፣ ሌላኛዋ የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገር የሆነችው ሱዳንም የጎላ ተቃውሞ ባታሰማም ሥጋት ውስጥ እንደነበረች ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለቱ አገሮች ላይ የተፈጠረውን ሥጋት ለመቅረፍና መተማመንን ለመፍጠር በማሰብ ባቀረበው የውይይት ግብዣ አትዮጵያን ጨምሮ ሦስቱ አገሮች በጠረጴዛ ዙረያ ውይይት የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ ላለፉት ስምንት ዓመታት ፈርጀ ብዙ የፖለቲካና የቴክኒክ ምክክሮችን አድረገዋል፡፡

በህዳሴ ግድቡ የሚታቆረው ውኃ ለኢትዮጵያ ኃይል አመንጭቶ ሲያልፍ ለሱዳን የተመጣጠነ ውኃ ዓመቱን ሙሉ የሚያቀርብ መሆኑ፣ ይህም ለግብርና ልማቷ የላቀ ዕድል እንደሚያስገኝ በውይይቱ ሒደት የተገነዘበችው ሱዳን፣ ከሥጋት ተላቃ የህዳሴ ግድቡን የሚደግፍ አቋም ማራመድ መጀመሯ የግብፅን የሥጋት ጩኸት ያለ አጋር በብቸኝነት የሚሰማ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በዚህ የውይይት ሒደት ውስጥ ግብፅ ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ምንም ዓይነት ስምምነት እንዳይደረስ የተለያዩ ማጨንገፊያ ሥልቶችን በመጠቀም ረዥም ርቀት ብትጓዝም፣ ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎቹ የተፋሰሱ ተጋሪ አገሮችን የሚጠቅም አንድ ትልቅ ስምምነት እንደ ፈረመች፣ በዓባይ ፖለቲካ ተመራማሪነታቸው የሚታወቁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

አሥሩ የዓባይ (ናይል) ተፋሰስ አገሮች ውኃውን በተናጠል በእኩልነትና በፍትሐዊነት መጠቀም የሚችሉበትን የትብብር ማዕቀፍ (CFA) እ.ኤ.አ. በ2010 በኡጋንዳ ሲፈራረሙ በልዩነት ከስምምነቱ ራሷን ያገለለችው ግብፅ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የተደረጉት ውይይቶች ውጤት የሆነውን የትብብር መግለጫ ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2015 ስትፈርም፣ ኢትዮጵያ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ሳታደርስ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የዓባይን ውኃ መጠቀም እንደምትችል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀብላ እንደነበረ ተመራማሪው ያስረዳሉ፡፡

የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የሱዳንን ድጋፍ ያጣችው ግብፅ ውይይቱ ዕልባት እንዳያገኝ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ከሱዳን ያጣቸውን ድጋፍ በሌላ መንገድ ለማካካስ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ እንዲገባ ከመጀመሪያው አንስቶ ጥረት ስታደርግ እንደቆየች ይነገራል፡፡

በመጨረሻም ከአሜሪካ ጋር ያላትን ፖለቲካዊ ቅርበት በመጠቀም የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ፣ በሦስቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በአሜሪካ አወያይነት ወደ መፍትሔ እንዲያመራ ያደረገችው ጥሪ የአሜሪካንን ይሁንታ አግኝቷል፡፡

ግብፅ አሜሪካ በአወያይነት እንድትገባ ጥሪ ከማቅረቧ አስቀድሞ ሦስቱ አገሮች በህዳሴ ግድቡ ላይ ያደርጉት የነበረው የውይይት አጀንዳ ምዕራፎችን ዘሎ በግድቡ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ላይ እንዲያተኩር በተናጠል ያዘጋጀችውን የውኃ አሞላል ሒደት ያጠናቀረ ሰነድ ለውይይት አቅርባለች፡፡

በዚህ ሰነድ የግድቡ ውኃ አሞላል በተራዘመ ሒደት እንዲከናወን፣ በአሞላል ሒደቱም ኢትዮጵያ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለግብፅ ለመልቀቅ እንድትስማማ፣ እንዲሁም የአስዋን ግድብ ውኃ ከ165 ሜትር በታች እንዳይወርድ፣ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከግድቡ ውኃ ለመልቀቅ ዋስትና እንድትሰጣት ጥያቄ አቅርባለች፡፡

ነገር ግን ግብፅ ያቀረበችው ጥያቄ በኢትዮጵያም ሆነ በሱዳን በኩል ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ሱዳን የራሳቸውን አማራጭ የውኃ አሞላል ሰነድ አቅርበዋል፡፡ ግብፅ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንዲለቀቅ ስትጠይቅ፣ ሱዳን ደግሞ 35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በየዓመቱ እንዲለቀቅ ሐሳብ አቅርባለች፡፡

የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ደግሞ የዓባይ ውኃ ቋሚ የሆነ ፍሰት ስለሌለው፣ በየዓመቱ 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለመልቀቅና ከዚህ ያነሰ ፍሰት በሚኖርበት ወቅት ከግድቡ ለማስወጣት ሐሳብ አቅርባለች፡፡ በዚህ ምክንያት የግብፅ ጥያቄ ውድቅ በመሆኑና ውይይቱ ከዚህ ልዩነት የሚነሳ ሆኖ፣ በአሜሪካ የአወያይነት ሚና ውይይቱ እንዲቀጥል ሙከራ አድርጋለች፡፡

የግብፅ ፍላጎት አሜሪካ በሚኖራት ሚና ውይይቱ የፖለቲካ ይዘት ተላብሶ በሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሳትፎ እንዲቀጥል ፈልጋ የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በኩል የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ ቴክኒካዊና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሯን የሚመለከት መሆኑን በማስረዳት ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በመጀመሪያው ውይይት እንዲሳተፉ አድርጋለች፡፡

ከዚህም ባለፈ ውይይቱ በአሜሪካ የትሬዥሪ ዲፓርትመንትና በዓለም ባንክ መሪነት እንዲከናወን የቀረበውን ሐሳብ በመቃወም ባቀረበችው ክርክር፣ የእነዚህ ተቋማት ሚና ምንም ዓይነት አስተያየት ሳይሰጡ ውይይቱን መታዘብ ብቻ እንዲሆን ማድረግ ችላለች፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት የመጀመሪያው ውይይት ከሦስት ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

ይህንን ውይይት አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ የቴክኒክ ቡድን ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር)፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውይይቶች በተለየ መንገድ በስምምነት ተጠናቋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በኩል ቀርቦ ግብፅ ያልተስማማችበት ቀሪ የውይይትና የልዩነት ጉዳዮችን የያዘ ሰንጠረዥ፣ ታዛቢዎቹ በተገኙበት የመጀመሪያ ውይይት ላይ ግብፅ ሙሉ በሙሉ በመቀበሏ በስምምነት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ይህም የታዛቢዎች መኖር የፈጠረው ተፅዕኖ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ታዛቢዎቹ መሳተፍ የጀመሩበት ሁለተኛው ውይይት ከሳምንት በፊት በግብፅ ካይሮ የቀጠለ ቢሆንም፣ ይህ ውይይት ግን ከመጀመሪያው በተቃራኒ ምንም ዓይነት ስምምነት ያልተደረሰበት ነበር፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊ፣ በካይሮ የነበረው ውይይት ግድቡን ከአምስት እስከ ሰባት ዓመመት ለመሙላት የተደረሰውን የአዲስ አበባ ስምምነት የሚያፈርስ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በግብፅ በኩል የተነሳው ሐሳብ አዲስ አለመሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ የግድቡ የውኃ ሙሌት በሚከናወንባቸው ዓመታት ቢያንስ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ወደ ግብፅ መፍሰሱን ኢትዮጵያ እንድታረጋግጥ፣ በግብፅ የሚገኘው የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን ከፍታ 165 ሜትር ላይ ከደረሰ ኢትዮጵያ ውኃ መያዝ እንደማትችል ዳግም መጠየቋን ተናግረዋል፡፡

ይህ ማለት ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን ውኃ መሙላት እንዳትችል የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች የዓባይ ገባር ወንዞችን እንዳትጠቀም በእጅ አዙር የሚጠመዝዝ፣ የዓባይን ውኃ በዋናነት ለግብፅ የሚሰጠውን የቅኝ ግዛት ስምምነት ኢትዮጵያ እንድትቀበል ተድበስብሶ የቀረበ ሐሳብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ግብፅ ወደ ስምምነት ለመምጣት በሚደረገው ጥረት እየተሳተፈች እንደሆነ በማስመሰል፣ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ወቅት የተፈረመውን የግብፅ የውኃ ድርሻ እንድትቀበል ጫና ማድረግ ላይ ትኩረት ማድረጓን አክለዋል፡፡

በግብፅ የተካሄደው ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ አሜሪካ የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ወደ ዋሽንግተን በመጋበዝ በልዩነቶቻቸው ላይ እንዲወያዩ አድርጋለች፡፡ ውይይቱ ሰኞ ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የደረሱበትን ስምምነት አስመልክቶም መግለጫ አውጥተዋል፡፡

በአሜሪካ የአወያይነት ሚና አራት ዙር ስብሰባዎችን አድርገው እ.ኤ.አ. እስከ ጃንዋሪ 15 ቀን 2020 ድረስ ስምምነት ላይ ለመድረስ የተግባቡት ሦስቱ አገሮች፣ እስካሁን ባደረጓቸው ሁለት ስብሰባዎች ይህ ነው የሚባል ስምምነት አልተደረሰም፡፡

የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰሞኑን በአሜሪካ ባደረጉት ውይይት ቀሪዎቹ ሁለት ውይይቶች ውጤታማ እንዲሆኑ፣ በውይይቶቹም የህዳሴ ግድቡ ውኃ አሞላልን በተመለከተ የቴክኒክ መመርያ ለማውጣት የስምምነት አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

ለማዘጋጀት የተስማሙት የቴክኒክ መመርያ “የድርቅ ወቅት” ለሚለው የጋራ ትርጓሜ ለመስጠት ድርቁ በግድቡ የውኃ ሙሌት፣ እንዲሁም በዚህ ወቅት የሚደረገው የውኃ ሙሌት በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ድርጊት መመርያዎችን፣ በቀሪዎቹ ሁለት ስብሰባዎች ለማውጣት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

የተወሰኑ ዓመታት የዓባይ ተፈጥሯዊ ፍሰትንና ከግድቡ የሚለቀቅ የውኃ መጠንን ያገናዘበ በድርቅ ወቅት ሊከሰት የሚችል ጉዳትን የሚቀንስ መመርያ ለማውጣት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኃላፊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የውኃ ሙሌቱ የሚከናወንበትን የቴክኒክ መመርያ ለማውጣት መስማማታቸው ተገቢ እንደሆነ፣ የሦስቱ አገሮች መሪዎች በተፈራረሙት የትብብር መግለጫ ስምምነት አንቀጽ አምስት ላይም በግልጽ የተቀመጠ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሰሞኑ ስምምነት ከዚህ ቀደም ያልነበረ አዲስ ነገር የተጨመረው፣ የድርቅ ወቅት ምን ማለት እንደሆነ ስምምነት እንዲደረስበት መቀመጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ግብፅ የድርቅ ወቅት አድርጋ የምትቆጥረው የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን 165 ሜትር በታች ሲወርድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ለመሙላትና በየዓመቱም 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለመልቀቅ ሐሳብ ያቀረበች ሲሆን፣ የድርቅ ወቅት ሲያጋጥምና ከ31 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በታች የውኃ መጠን በሚሆንበት ጊዜ በግድቡ ውኃ እንደማትይዝ ሐሳብ ማቅረቧን አስረድተዋል፡፡

በግብፅ በኩል ግን በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ እንዲለቀቅላት፣ የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን 165 ሜትር በሚሆንበት ጊዜ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ከያዘችው ውኃ መልቀቅ ይኖርባታል የሚል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ግብፅ በአስዋን ግድብ የታችኛው ክፍል ውኃ የምትለቅና ሥልታዊ በሆነ መንገድ ይህንን ውኃ የምትጠቀም መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፣ በዚህ መንገድ የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን 165 ሜትር ላይ እንዲረጋ በማድረግ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን እንደ ሐውልት ታቅፋ እንድትኖር እንደምትፈልግ፣ በዚህም የዓባይን ውኃ ከግብፅ በስተቀር ማንም እንዳይጠቀምበት ለማድረግ ያቀረበችው ሴራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የውኃ ሙሌት በማትቆጣጠረው የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን ከ165 ሜትር በታች መውረድ የለበትም የሚለውን መከራከሪያ መቀበል የለባትም ሲሉ ያሳስባሉ፡፡ ለዚህም እንደ መከራከሪያ በ1980ዎቹ የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን ከ165 ሜትር በታች ወርዶ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር፣ የአስዋን ግድብ አገልግሎት መስጠት የማይችለው ከ147 ሜትር በታች የወረደ እንደሆነ ነው ብለዋል፡፡

ግብፅ በዚህ የክርክር ነጥብ ላይ የፀና አቋም እያራመደች እንደሆነ የሚናገሩት ኃላፊው፣ ነገሮችን ለማመቻቸት ካልወሰነች በስተቀር ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ይህንን ከተቀበለች የህዳሴ ግድቡ በውኃ የማይሞላ ባዶ ኮንክሪት እንደሚሆን አክለዋል፡፡

ከዚህ በመነሳት ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያ ራሷን ማዘጋጀት ነው የሚሉት ኃላፊው፣ ከግብፅ የተሻለ ጥቅም ያላት አሜሪካ አሁን በታዛቢነት የተቀመጡትን አሜሪካ የገንዘብ ተቋምንና የዓለም ባንክን በመጠቀም ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ ከሁለቱ ተቋማት እንዳታገኝ ጫና ማድረጓ ያመዘነ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህ ሁለት ተቋማት የሚገኘው የገንዘብ ዕርዳታና ብድር የህዳሴ ግድቡ ከሚያስገኘው ገቢ ሲነፃፀር ግዙፍ በመሆኑ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ የግብፅን ሐሳብ ተቀብላ ስምምነት ብትፈጽም ለሚደርስባት ጉዳት ጠቀም ያለ ገንዘብ በካሳ መልክ እንድታገኝ በማድረግ ኢትዮጵያን አጣብቂኝ ውስጥ የመክተት አካሄድ ሊኖር ስለሚችል፣ ከወዲሁ ለሁሉም ነገር መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ወደ አሜሪካ ከማቅናታቸው አስቀድሞ በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ በግብፅ በኩል እየቀረበ ያለው ሐሳብ የኢትዮጵያን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት የሚጋፋና በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የማይኖረው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“አስዋን ግድብን ኢትዮጵያ መቆጣጠር ወይም በዚህ ግድብ ያለውን ውኃ ያፍሱት ወይም ያባከኑት ኢትዮጵያ ማወቅ በማትችልበት ሁኔታ እንዴት እንደ ቅድመ ሁኔታ ልንቀበል እንችላለን? ከአስዋን ግድብ የውኃ መጠን ጋር ምንስ ጉዳይ አለን? በዓለም አቀፍ የውኃ ስምምነቶች መሠረት መለቀቅ የሚገባው ውኃ ይለቀቃል፣ ከዚህ ውጭ የሚሆን ነገር የለም፤” ብለዋል፡፡

አሜሪካ ልታደርገው ስለምትችለው ጫና የተጠየቁት አቶ ገዱ አሜሪካ በታዛቢነት እየተሳተፈች መሆኗን አውስተው፣ በኢትዮጵያ ላይ ምንም ዓይነት ልዩ ጫና ለማድረግ እስካሁን እንዳልሞከረች ተናግረዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ሙከራ ሲያደርጉ አላየንም፡፡ ቢሞክሩም የሚሳካ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ አቋም ምን እንደሆነ ያውቁታል፤” ያሉት አቶ ገዱ፣ “የህዳሴ ግድብ ማለት ኢትዮጵያ ከዓባይ ውኃ ልትጠቀም ከሚገባት ኢምንት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ግድብ የሚገባትን ለመጠቀም የሚያግዳት ወይም የሚገታት ማንም ኃይል ሊኖር አይችልም፤” ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -