Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለምን የባንክ ወለድ ብቻ የሸቀጥ ዋጋም ይቀንስ!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየን በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የባንኩ 21 መመርያዎችና ሦስት አዋጆች ተሻሽለዋል፡፡ አንድ አዲስ አዋጅም ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ እነዚህም ባንኩ ከጀመራቸው የሪፎርም ዕርምጃዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሌሎችም ማሻሻያዎችን ለማካተት ጥናቶች መካሄዳቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ይተገበራሉ የተባሉ አዳዲስ ማሻሻያዎችም ይፋ እንደሚደረጉ ባንኩ አስታውቋል፡፡

እንዲህ ያሉት ማሻሻያዎች የፋይናንስ ዘርፉን አሠራሮች እንደ ልብ ከፋፍተው  የዘርፉ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ለማስቻል የሚኖራቸው አስተዋጽኦ በብዙ የሚመነዘር ነው፡፡ አላፈናፍን ያለ ሕግጋት ተብራርተውና ተስፋፍተው ቀርበዋል፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው አማራጭና አዳዲስ አሠራሮች እንዲፈጠሩ የሚያግዙ ለውጦች መምጣታቸው እየተነገረ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚተገበሩ የማይታሰቡና የማይጠበቁ ሕጎች ተሽረው፣ የተከለከሉ ሥራዎች ተፈቅደው ኢንዱስትሪው ከእስራት መፈታቱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ለዓመታት እንዲስተካከሉ ጥያቄ ሲቀርብባቸው የቆዩ መመርያዎች መሻሻላቸውና አዳዲስ አሠራሮችን የሚፈቅዱ ሕጎች መምጣታቸው ኢንዱስትሪው ጥሩ ፉክክር እንዲያሳይ፣ ገበያ እንዲመራውና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ መንገዱን ጨርቅ አድርገውለታል፡፡

ይህም ይባል እንጂ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ተደረገ ማለት ግን አይደለም፡፡ የሚቀሩ ጉዳዮች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ማሻሻያ የተደረገባቸው መመርያዎችም ሆኑ አዳዲሶቹ ሕግጋት በኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፉ ስለሚታመን፣ ለተወሰደው አዎንታዊ ዕርምጃ መልካምነት ምሥጋና ሲያንስ ነው፡፡

ማሻሻያ ከተደረገባቸው መመርዎች አንዱ የግል ባንኮች በአስገዳጅነት የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ እንዲፈጽሙ የሚያዘው መመርያ መሻሩ ትኩስ መነጋገሪያ ነው፡፡ በርካታ ባንኮችና ኃላፊዎቻቸው ደስታቸው ገና አልበረደም፡፡ አንዳንዶቹም ለብድር የሚያስከፍሉት ወለድ ላይ ቅናሽ እንዳደረጉ ሲያውጁ ዓይተናል፡፡ ከሳምንት በፊት  ይኼው የግል ባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ ለማድረግ የመወሰናቸው ጉዳይና አዎንታዊ ምላሻቸው ሲስተጋባ ሰንብቷል፡፡

አዋሽ ባንክ አንድ ባንክ የብድር ማስከፈያ ወለድ ላይ ቅናሽ ማድረጉን በማስታወቅ የቀደመው የለም፡፡ ሌሎችም እንዲሁ የብድር ወለድ ለመቀነስ መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በምን ያህል እንደቀነሱ ለመስማት እንጠባበቃለን፡፡ ቅናሻቸውን ይፋ የሚያደርጉ ባንኮችን ማስታወቂያ የሚጠባበቀው አብዛኛው ነጋዴና ባለሀብት ከወዲሁ ሥራውን ማጣደፍ የጀመረ ይመስላል፡፡ ይህም የተቀዛቀዘው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ያግዛል ተብሎ ይታመናል፡፡

ሰሞኑን ብሔራዊ ባንክ ከግል ባንኮችና ከመድን ኩባንያዎች ጋር በነበረው ውይይት ወቅት፣ የ27 በመቶውን የቦንድ ግዥ መመርያ ማንሳቱ ተቋማቱ ላይ ያሳደረው ዕፎይታ መልካም ዕድል ይዞ መምጣቱ ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡ ባንኮች የብድር ወለድ ላይ የጫኑትን ምጣኔ ቀስ በቀስ እያነሱ ከመጡ፣ ገበያ የማረጋጋት ኃላፊነታቸውን እንደተወጡ ይቆጠራል፡፡ በተደጋጋሚ እንደተገለጸውም፣ ባንኮች የብድር ማስከፈያ ወለዳቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ካስገደዷቸው ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ይኼው የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ ነበር፡፡ የመመርያውን መነሳት ተከትሎም እንደ ድሮው በግዴታ ሳይሆን በውዴታቸውና በፈቃዳቸው እየተነሳሱ የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን እንደ ተቋማቸው አሠራርና ምጣኔ ላይ ቅናሽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ሁሉንም ያስማማል፡፡

ለዚህ ማሳያውም እየታየ ያለው አዎንታዊ ምላሽ ነው፡፡ በመልካምነታቸው የሚታዩ ናቸው፡፡ ሳይገለጽ መታለፍ የሌለበት ነገር ግን ብሔራዊ ባንክም ሆነ መንግሥት የ27 በመቶውን አስገዳጅ የቦንድ ግዥ መመርያ መሻሩን ቢገለጽም፣ ባንኮችም በግድ የብድር ወለዳችሁን መቀነስ አለባችሁ አላላቸውም፡፡ ይሁን እንጂ በተፈጠረው ዕድል አግባብ ወለድ ብትቀንሱ ጥሩ ነው ብሏቸዋል፡፡ ባንኮችም በቀናነት ለውጡን ተከትለው ቅናሽ እንዲያደርጉ፣ ከማስታወስ በቀር ጫና አልተደረገባቸውም፡፡ ምንም ዓይነት አስገዳጅ ሁኔታም አላስመጣባቸውም፡፡

ባንኮችም የተሰጣቸውን ዕድል ዓይተው፣ የብድር ወለድ ለመቀነስ ያሳዩት ፍላጎት፣ መግባባትና በቅንነት መነጋገር መቻላቸው፣ በንግግርና በመልካም አስተሳሰብና መተማመን ለውጥ ለማምጣት ብዙ እንደማይቸግር የሚያሳይ ዕርምጃ መታየቱን መጥቀሱ ተገቢ ነው፡፡

እንዲህ ባለው መንፈስ ሁሉም ባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን ከቀነሱ፣ በኢኮኖሚው ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው አዎንታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ መታየት የለበትም፡፡ ለኢኮኖሚው መነቃቃት እንደሚፈጥር መጠበቅና ማሰቡም ተገቢ ነው፡፡ ከባንኮቹ የብድር ወለድ ቅናሽ በኋላ በእርግጥም ለውጥ መምጣቱ እየታየ፣ ገበያውም ስክነት እየታየበት፣ ከሚፈረጥጥበት ልጓም አልባ ግስጋሴው መጠነኛ መረጋጋት ይታይበት ዘንድ የተበዳሪዎች አስተዋጽኦም መታየት መቻል አለበት፡፡

የወለድ ምጣኔ ከፍ ማለት ለዋጋ መናር አንዱ ምክንያት ከሆነ፣ በባንክ ብድር ወለድ ከፍተኛነት አሳበው ዋጋቸውን የሰቀሉ ሁሉ ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የራሱን ድርሻ ከተወጣ፣ ባንኮችም ወለድ ከቀነሱ ቀጣዮቹ ተዋናዮች ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ነጋዴዎች በተለይም በባንክ ብድር የሚያመርቱና የሚነግዱ ሁሉ ገበያውን ማረጋጋት አለባቸው፡፡ እውነታው የሚያሳየንም ይህንኑ በመሆኑ ገበያ ውስጥ ለውጥ መታየት እንዳለበት ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል፡፡

ከዚህ አንፃር ነጋዴው የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ ዝግጁ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በሰበብ አስባቡ ዋጋ መቆለል አመል የሆነበት ሁሉ በይፋ ቅናሽ ሲደረግለትም ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ጨመረ እንጂ ቀነሰ በማይሰማበት አገር ውስጥ ባንኮች ዋጋ መቀነሳቸው አዲስ ታሪክ ነው፡፡ ስለዚህ የብድር ወለድ ቅናሽ ማድረጉ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ገበያን በማረጋጋት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት በመሆኑ፣ ይህ ውጤት ስለመገኘቱ የሚያረጋግጥ ጥናት ማድረግና የለውጥ ዜናዎችንም ማዳረስ ያስፈልጋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት