የፋይናንስ ተቋማት በዋናነት አምስት ባንኮች ለመጀመርያ ጊዜ በይፋ በተሳተፉበት የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ፣ 500 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሰነድ ለገበያ ቀርቦ መሸጡ ታወቀ፡፡
ረቡዕ ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ፣ ለሽያጭ ከቀረበው 500 ሚሊዮን ብር ዋጋ ካለው ሰነድ ውስጥ 250 ሚሊዮን ብሩ የ28 ቀናት ቆይታ የሚኖረው ወይም ተመላሽ የሚደረግ ሲሆን፣ የተቀረው 250 ሚሊዮን ብር ለዘጠና ቀናት በሚቆይ ግብይት መሠረት ግዥውን ለፈጸሙ ተቋማት ባሸነፉበት የወለድ ምጣኔ ታስቦ እንደሚመለስ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ግብይት ላይ ባንኮች እንዲሳተፉ ከወሰነ ወዲህ በዚህ ሳምንት የተጀመረው የጨረታ ሒደት ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ከተሳተፉ የግል ባንኮች ውስጥ አዋሽና እናት ባንኮች ተጠቅሰዋል፡፡ ይህ የግብይት ሥርዓት ወደፊት ለስቶክ ወይም ለካፒታል ገበያ መንገድ ጠራጊ እንዲሆን ታስቦ የተጀመረ ሲሆን፣ ስያሜውም የመጀመርያ ደረጃ የቦንድ ገበያ የሚል ስያሜ ያለው ነው፡፡ ከዚህ ግብይት ሒደት የሚገኘው ውጤት ታይቶ ወደ ሌሎች ገበያዎች ለመግባት የሚያስችል መነሻ እንደሚኖረው ብሔራዊ ባንክ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ከዚህ ቀደም የመንግሥት ግምጃ ቤት ጨረታዎች ላይ በመሳተፍ የሚታወቁት በአብዛኛው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ነበሩ፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአዲሱ የግብይት ሒደት ግን የግል ባንኮች ከመሳተፋቸውም ባሻገር የተወሰኑ የግብይት ሰነዶችን በመግዛት ጨረታዎችን ማሸነፍ እንደቻሉም ታይቷል፡፡