Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እስከ 200 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ሊጣል ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሀብቶች ኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ለማምረት ልዩ ፈቃድ እንዲያወጡ ይገደዳሉ

በቢራና በሲጋራ ዋጋ ላይ 30 እና 40 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጣላል

ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ከ130 እስከ 200 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ክፍያ የሚጥል ሕግ ሊታወጅ ነው፡፡ ሕጉ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡ ሕጉ ከተመረቱ ከአሥር ዓመት በላይ የሆናቸው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር እንዳይገቡ እንደሚያደርግ፣ የአገር ውስጥ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ዕድገትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚደግፍ ታምኖበታል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የተረቀቀው ይህ የሕግ ማዕቀፍ ተሽከርካሪን ጨምሮ፣ በ19 የምርት ዓይነቶች ላይ አዲስ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል ተደርጎ የተሰናዳ ነው፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ስብሰባ በኤክሳይዝ ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወሰን ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሪፖርተር ያገኘው አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ፣ ከአሥር ዓመት በላይ የሆናቸው ተሽከርካሪዎች ላይ እንደ የጉልበት መጠናቸው ከ130 እስከ 200 በመቶ የሚደርስ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል የሚያደርግ ድንጋጌዎችንና የታክስ ምጣኔ ሰንጠረዦችን ይዟል፡፡ ሰነዱ እንደሚያመለክተው፣ የጉልበት መጠናቸው ከ1300 ሲሲ በታች በሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ 130 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል ይደነግጋል፡፡

ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉና የጉልበት መጠናቸው 1300 ሲሲ በላይ እስከ 1500 ሲሲ በሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ደግሞ 160 በመቶ ኤክሳዝ ታክስ እንዲጣል የሚደነግግ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉ ከ1500 ሲሲ በላይ ጉልበት ያላቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ደግሞ 200 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል በድንጋጌው ተካቷል፡፡

የአረጁ ተሽከርካሪዎች በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ የካርቦን (የተቃጠለ ጭስ) የሚለቁ በመሆናቸው፣ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ እንደማይፈቀድላቸውና በዚህም ምክንያት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች የእነዚህ የአረጁ ተሽከርካሪዎች ማራገፊያ እንደሆኑ የሚያስረዳው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ፣ ይህንን ሁኔታ ለማስቀረት ከፍተኛ ኤክሳይዝ ታክስ መጣል በአማራጭነት መወሰዱን ያመለክታል፡፡

 ከዚህ በተጨማሪም የአረጁ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ የነዳጅና የመለዋወጫ ፍጆታ፣ አገሪቱ ለነዳጅና ለመለዋወጫ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ እንዳናረው ሰነዱ ያስረዳል፡፡

“የአረጁ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር እንዳይገቡ የሚከለክል ሕግ ማውጣት የሚቻል ቢሆንም፣ የዚህ ዓይነቱ ዕርምጃ በዓለም የንግድ ድርጅት ስምምነቶች የተከለከለ በመሆኑና ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት ይፈጥራል፤” የሚለው ማብራሪያ ሰነዱ፣ ተመሳሳይ የክልከላ ውጤት የሚኖረውን ሥልታዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው በአማራጭነት መወሰኑን ያስረዳል፡፡ ከአሥር ዓመት በታች ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችም ቢሆኑ ወደ አገር እንዳይገቡ ኤክሳይዝ ታክስ እንደሚጣል፣ በረቂቅ ሕጉ ላይ የተቀመጡት የታክስ ምጣኔዎች ያስገነዝባሉ፡፡

ለምሳሌ ከ1300 ሲሲ ያልበለጠ ጉልበት ያላቸውና የአገልግሎት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት በሆነ ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲጣል የታቀደው ኤክሳይዝ ታክስ 70 በመቶ ነው፡፡ በሌላ በኩል በዚሁ ምድብ ሆነው ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የአገልግሎት ዕድሜ ባላቸው ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ 50 በመቶ እንዲሆን በረቂቁ ድንጋጌ ተካቶ ቀርቧል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ከውጭ የሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ለማስቀረት ከፍተኛ ኤክሳይዝ እንዲጣል በረቂቅ አዋጁ ተካቶ ቢቀርብም፣ ሙሉ በሙሉ የተበታተኑ የተሽከርካሪ ክፍሎችን ከውጭ አስመጥተው፣ ወይም በከፊል የተገጣጠሙ ተሽከርካሪዎችን አስመጥተው በአገር ውስጥ በሚገጣጥሙ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪዎች ላይ ዝቅተኛ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው በማድረግ፣ ዘርፉን ለመደገፍ የታለመ የታክስ ምጣኔ እንዲጣል በድንጋጌዎቹ ተካተዋል፡፡

 ለምሳሌ ሙሉ በሙሉ የተበተነ የተሽከርካሪ ክፍሎችን (CKD) በማስመጣት ከ1300 ሲሲ ያልበለጠ ጉልበት ያላቸውን ተሽከርካሪዎች ገጠጥመው ለገበያ በሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች የመሸጫ ዋጋ ላይ 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል፣ በከፊል የተገጣጠሙ ተሽከርካሪዎችን አስመጥተው ከ1300 ሲሲ በታች የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥመው ለገበያ በሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች የመሸጫ ዋጋ ላይም እንዲሁ 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣል በረቂቁ ድንጋጌ ተመልክቷል፡፡

በከፊል የተገጣጠሙ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም የሚታወቀው በላይ አብ ሞተርስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምንተስኖት ታደሰ ስለአዲሱ ኤክሳዝ ታክስ ምጣኔ መረጃ እንደሌላቸው ለሪፖርተር ገልጸው፣ “ይህ እውነት ከሆነ ለአገር ውስጥ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ትንሳዔ ይሆናል፤” ብለዋል፡፡

ለሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች በአሁኑ ወቅት የሚከፈለው ኤክሳይዝ ታክስ 100 በመቶ እንደሆነ አቶ ምንተስኖት ገልጸው፣ አዲስ የተባለው ኤክስይዝ ታክስ እንደተባለው ዝቅተኛ የታክስ ምጣኔን የሚያሰፍን ከሆነ ኢንዱስትሪውን በከፊል ከመገጣጠም ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ወደ መገጣጠም ተግባር እንደሚያሸጋግረው፣ በገበያ ደረጃም ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጎረቤት አገሮችንም መዳረሻ ለማድረግ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር በዚህ ዓመት ከውጭ በሚገቡ ምርቶችና በአገር ውስጥ በሚመረቱት ላይ ከሚጣል ኤክሳይዝ ታክስ 19 ቢሊዮን ብር እንዲሰበስብ በበጀት አዋጁ ኃላፊነት የተጣለበት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አምስት ቢሊዮን ብር ከውጭ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች የሚሰብሰብ መሆኑን በፓርላማ የፀደቀው የዘንድሮ በጀት አዋጅ ያስረዳል፡፡

ረቂቁ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ በተሽከርካሪዎች ላይ ከሚጣለው የታክስ ምጣኔ በተጨማሪ፣ ከፍተኛ የታክስ ገቢ በሚያስገኙት የቢራና የሲጋራ ምርቶች ላይም አዲስ ምጣኔ አስቀምጧል፡፡

በሥራ ላይ በሚገኘው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ መሠረት ኤክሳይዝ ታክስ የሚሰላው በሁለት መንገድ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ላይ በምርቶቹ ማምረቻ ዋጋ ላይ ነው፡፡ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ የሚሰላው ደግሞ የዕቃው ዋጋ፣ የኢንሹራንስ ወጪ፣ እስከ ወደብ ድረስ የሚወጣው የትራንስፖርት ወጪ ድምር ላይ የጉምሩክ ቀረጥ ተከፍሎ ከሚገኘው አጠቃላይ ዋጋ ላይ ነው፡፡ በተረቀቀው አዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ የሚሰላበት መንገድ እንዳለ እንዲቀጥል ድንጋጌ የያዘ ሲሆን፣ በአገር በሚመረቱት ላይ ግን ኤክሳይዝ ታክስ የሚጣለው በምርቱ ማከፋፈያ ዋጋ ላይ መሆኑን ይደነግጋል፡፡

በዚህ መሠረት በቢራ ላይ የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ በጠርሙስ 40 በመቶ ወይም በሊትር 11 ብር እንዲከፈል በረቂቅ ድንጋጌነት ቀርቧል፡፡ ሃያ ፍሬዎችን በሚይዝ አንድ ፓኬት ሲጋራ መሸጫ ዋጋ ላይ 30 በመቶና ተጨማሪ አምስት ብር እንዲሰላ በድንጋጌው ተመልክቷል፡፡

በእያንዳንዱ የቢራና የሲጋራ ምርት ላይ ኤክሳይዝ ታክስ የተከፈለበት መሆኑን የሚያመለክት ቴምብር መለጠፍ እንደሚኖርበት በአስገዳጅነት ተቀምጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኤክስይዝ ታክስ የሚከፈልበትን ምርት ለማምረትም ሆነ ለማስመጣት፣ እንዲሁም አገልግሎት ለመስጠት ከገቢዎች ሚኒስቴር ልዩ ፈቃድ መያዝ በአስገዳጅነት ተካቷል፡፡ በቢራ አምራችነት ፈቃድ ከተሰጣቸው ኩባንያዎች ውጪ በባር ወይ በምግብ ቤቶች አነስተኛ ቢራ ጠመቃ ለማካሄድ ተጨማሪ ፈቃድ ማግኘትም አስገዳጅ ሆኖ በረቂቁ ተካቷል፡፡

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በቢራ ምርቶች የማምረቻ ዋጋ ላይ የሚጥለው ኤክሳይዝ ታክስ 50 በመቶ ሲሆን፣ በትምባሆ ምርት የማምረቻ ዋጋ ላይ ደግሞ 75 በመቶ ይጥላል።

በመሆኑም የማኅበረሰብ ጤናን በከፍተኛ ደረጃ ያቃውሳሉ የተባሉት በሁለቱ ምርቶች ላይ እንዲጣል የቀረበው አዲስ የኤክሳይዝ ታክስ፣ እጅግ ዝቅተኛና የማኅበረሰብ ጤናን ያላገናዘበ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በተለይ በትምባሆ ምርት ላይ የዓለም የጤና ድርጅት የሚያስቀምጠው የታክስ ምጣኔ 70 በመቶ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዎቹ፣ አሁን የተረቀቀው ኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ በዓለም የጤና ድርጅት ከተቀመጠውም ሆነ ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች በሲጋራ ላይ ከሚጥሉት ኤክሳይዝ ታክስ በእጅጉ እንደሚያንስ ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ፓርላማ ትምባሆን ለመቆጣጠር ባወጣው ጥብቅ ሕግ በዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት መሸለሙን የሚያስታውሱት ባለሙያዎቹ፣ አዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ በሲጋራ ላይ ለመጣል ያቀደው የታክስ ምጣኔ የኅብረተሰብ ጤናን ለመጠበቅ ታስቦ የፀደቀውን የትምባሆ ቁጥጥር አዋጅ ዓላማ የሚቃረን በመሆኑ መንግሥት በድጋሚ ሊያጤነው ይገባል ብለዋል።

በዘንድሮው የበጀት አዋጅ መሠረት 4.2 ቢሊዮን ብር በአገር ውስጥ በሚመረቱ ቢራ መጠጦች ላይ ከሚጣል ኤክሳይዝ ታክስ ለመሰብሰብ፣ እንዲሁም 1.1 ቢሊዮን ብር ከሲጋራ ወይም ከትምባሆ ምርቶች ኤክሳይዝ ታክስ እንዲሰበስብ ለገቢዎች ሚኒስቴር ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

በሥራ ላይ በሚገኘው አዋጅ ኤክሳይዝ ታክስ ካልተጣለባቸው ምርቶች በረቂቁ እንዲካተቱ ከተደረጉት መካከል አንዱ ሰው ሠራሽ ፀጉር ወይም “ሂዩማን ሄር” ሲሆን፣ 100 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልበት በረቂቁ ተካቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች