Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊድንበር ተሻጋሪ ወረርሽኝ ሌላው የጤና ዘርፍ አደጋ

ድንበር ተሻጋሪ ወረርሽኝ ሌላው የጤና ዘርፍ አደጋ

ቀን:

በዓለም የሚከሰቱ ሰው ሠራሽም ሆኑ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች በማኅበረሰብ ጤና ረገድ የሚያመጧቸው ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ተላላፊ በሽታዎች ከአንዱ አገር ወደ ሌላ አገር የሚኖራቸው ሥርጭትና በየአገሮች ላይ የሚያስከትሉት ቀውስ አደገኛ እየሆነም መጥቷል፡፡ የኢቦላ ወረርሽኝ ለዚህ ጥሩ ማሳያም ነው፡፡ ፖሊዮ (የልጅነት ልምሻም)፣ ኮሌራና ሌሎችም ድንበር ተሻግረው ከሚያጠቁ በሽታዎች ይጠቀሳሉ፡፡

በምዕራብ አፍሪካ በ2006 ዓ.ም. – በ2007 ዓ.ም. የተከሰተው ኢቦላ በወቅቱ ወደ 11,000 የሚጠጉ ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት የዳረገ ሲሆን፣ በአገሮቹም ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና አሳድሯል፡፡

ከኅዳር 23 ቀን እስከ ኅዳር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ የተካሄደውን የዓለም የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማኅበር ሳይንሳዊ ስብሰባን አስመልክተው ኤባ አባተ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ ኢቦላ ከአንድ ዓመት ወዲህ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተከስቶ እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር አልዋለም፡፡ 2000 ሰዎችም በበሽታው ተቀጥፈዋል፡፡

- Advertisement -

ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ድንበር ተሻጋሪ እየሆኑ በመምጣታቸው የተነሳ እንደ ከዚህ በፊቱ ግንዛቤ የአንድ አገር ችግር ብቻ ነው የሚባልበት ጊዜ ያበቃና አንድ ቦታ ላይ የሚኖረው ችግር ለሌላውም አገር ችግር መሆኑ በተጨባጭ ሁኔታ እየታየ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ከጊኒ የተነሳው ኢቦላ በአፍሪካ ብቻ ሳይወሰን የአሜሪካንና የአውሮፓን አገሮች በር ማንኳኳቱን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር በአንድ አገር የሚከሰት የጤና ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ቅንጅታዊ አሠራርን እንደሚጠይቅና በከፍተኛ ቅንጅት ካልተሠራም ውጤታማ ለመሆን እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት አገሮች እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱባቸው በተገቢው መንገድ ለመመለስ የሚያስችላቸውን ተቋማት አደራጅተዋል፡፡ እነዚህም ተቋማት ብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ይባላሉ፡፡ በኢትዮጵያም ይህ ዓይነት ኢንስቲትዩት ተቋቁሞ የኅብረተሰቡን ጤና ከማረጋገጥ አኳያ ከፍ ብሎ የተጠቀሱት የጤና ችግሮች ወደ አገር እንዳይገቡ፣ ከገቡም ችግሮቹን በተገቢው መንገድ ለማስተካከል የሚያስችሉ ሥራዎችን በኃላፊነት ተረክቦ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹ኤቪደንስ ኢንፎርምድ ግሎባል አክሽን ፎር ትራንስ ባውንደሪ ፐብሊክ ሔልዝ ቻሌንጅስ›› በሚል ጭብጥ ላይ ያተኮረው ስብሰባ፣ ሳይንሳዊ ምልክታና ቴክኒካዊ ሒደትን እንዳጠናከረ፣ በተጨማሪም ሙያዊ ልምድን ለማዳበርና የኢንስቲትዩቶችን ትስስር ለመፍጠር የሚረዱ ሁኔታዎችን እንዳመቻቸ፣ ዶ/ር ኤባ አስረድተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ ‹‹በዓለም ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው በግልጽ እየታየ ነው፡፡ አንድ ወረርሽኝ በሽታ ከአንድ አኅጉር ወደ ሌላው አኅጉር በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ይዛመታል፡፡ ከዚህ አንፃር በየአገሮቹ ያሉት የኅብተረሰብ ጤና ተቋማት ለወረርሽኝ ምላሽ በመስጠት ብቻ ሳይወሰኑ የተቀናጀ ቁጥጥር ማካሄድ ይገባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

አዲስ አበባም በየዕለቱ በአውሮፕላን የሚመጡ በርካታ እንግዶችን የምታስተናግድ ከተማ እንደመሆኗ፣ ለወረርሽኝ በሽታ የመጋለጥ አጋጣሚዋ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማኅበር ጽሕፈት ቤት የሚገኘው በፓሪስ ኢንስቲትዩት ፓስተር ውስጥ ሲሆን፣ በ95 አገሮች የሚገኙ 109 አባላት አሉት፡፡ በስድስት አኅጉራት የሚገኙ አምስት ቢሊዮን ሕዝቦችንም ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያም የማኅበሩ የቦርድ አባል ናት፡፡ ማኅበሩ እንዲህ ዓይነቱን ስብሰባ በአፍሪካ ሲያካሂድ ከደቡብ አፍሪካና ከሞሮኮ ቀጥሎ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ አብዛኛውን ስብሰባ ያካሄደውም በአሜሪካና በአውሮፓ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ