Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስመዘገበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዋሽ ባንክ በ2011 ዓ.ም. ከፍተኛ ትርፍ ከማስመዝገቡ ባሻገር፣ ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገባቱን አስታወቀ፡፡

ባንኩ የተጠናቀቀውን ሒሳብ ዓመት ክንውን በማስመልከት ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ በዋና ዋና የባንክ ሥራ ዘርፎች ውጤታማ እንቅስቃሴ በማስመዝገብ ከግል ባንኮች አኳያ የመሪነት ቦታውን እንዳስጠበቀ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታቦር ዋሚ አመላክተዋል፡፡

አዋሽ ባንክ ከፍተኛ አፈጻጸም ካሳየባቸው ክንውኖቹ መካከል የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከውጭ ንግድ ዘርፍ፣ ከውጭ የሐዋላ አገልግሎት፣ እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ918.9 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከ2010 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ327.2 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ55 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ባንኩ ያስመዘገበው የውጭ ምንዛሪ መጠን፣ ከኢትዮጵያ የሚላኩ ሸቀጦች የሚያስገኙት ጠቅላላ ገቢም ሆነ ከተለያዩ ምንጮች የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እየቀነሰ በመጣበት ወቅት በመሆኑ፣ ለባንኩ ብቻም ሳይሆን ለኢኮኖሚውም በትልቅ ውጤት እንደሚገለጽ የቦርድ ሰብሳቢው አስታውሰዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስተቀር ከተቀሩት የግል ባንኮች አብላጫውን የገበያ ድርሻ መያዙን ማሳያ ውጤት ስለመሆኑም አቶ ታቦር ተናግረዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. ሒሳብ መዝጊያ ወቅት አዋሽ ባንክ ያስመዘገበው የ3.34 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ፣ ለአዋሽ ባንክ በታሪክ ትልቁ ብቻም ሳይሆን፣ በአገሪቱ የግል ባንኮችም ረገድ ከዚህ ቀደም ያልተመዘገበ ትልቅ የትርፍ መጠን እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ታቦር፣ ይህም የትርፍ መጠን በ2010 ዓ.ም. ከተገኘው የ1.96 ቢሊዮን ብር ትርፍ ጋር ሲነፃፀር የ70 በመቶ ወይም የ1.38 ቢሊዮን ብር ጭማሪ የታየበት እንደሆነ  ገልጸዋል፡፡

አዋሽ ባንክ ይህን ያህል ትርፍ ማስመዘገብ በመቻሉ፣ በባንኩ አንድ አክሲዮን ያስገኝ የነበረውን የትርፍ ድርሻ መጠንም አሳድጎታል፡፡ በ2010 ዓ.ም. በባንኩ አንድ የአክሲዮን ትርፍ ድርሻ 543 ብር ነበር፡፡ በ2011 ዓ.ም. ግን ወደ ሰሒሒኺኺሒሒአ፣ደደደከደከደሒሒ632 ብር አሻቅቧል፡፡ ይህም በባንኩ ታሪክ ከፍተኛው የትርፍ ድርሻ ክፍያ እንደሆነ የቦርድ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በዚህ ያህል ደረጃ ለአንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ የከፈለ ባንክ አልታየም፡፡ በባንኮች አካባቢ ከዚህ ቀደም ለአንድ አክሲዮን የተከፈለው ከፍተኛ የትርፍ ድርሻ 670 ብር እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ የአዋሽ ባንክ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ሁለተኛው ከፍተኛ መጠን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ 

አዋሽ ባንክ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብም በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን ጨምሮ የ2011 ዓ.ም. የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በ36 በመቶ ወይም በ16.5 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ አጠቃላይ መጠኑም  62.5 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ባንኩ ለተለያዩ ዘርፎች ያሠራጨው ብድርም የ51 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 47.3 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ  አቶ ታቦር አመልክተው፣ በተለይ በመንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ለወጪ ንግድና ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የሰጠው ብድር ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ ዕድገት እንዳሳዩ  ጠቅሰዋል፡፡ አዋሽ ባንክ ከፍተኛ ጭማሪና ዕድገት ያሳየበት ሌላው እንቅስቃሴ የባንኩና ተንቀሳቃሽና ቋሚ ሀብት የሚያሳየው የሒሳብ መጠን ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የ19.5 ቢሊዮን ብር ዕድገት በማስመዝገብ ወደ 74.6 ቢሊዮን ብር ያደገው የባንኩ ጠቅላላ ሀብት በ2010 ዓ.ም. 55.3 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

የባንኩን የተከፈለ ካፒታል በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ ከዚህ ቀደም መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል መጠን 4.4 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ታውቋል፡፡ ባንኩ በወሰነው መሠረት ቀሪውን 1.6 ቢሊዮን ብር እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2021 ዓ.ም ድረስ ለመሙላት ካስቀመጠው ጊዜ ገደብ ቀደም ብሎ ለማሳካት እንደሚችል የባንኩ መረጃ ያስረዳል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ 4.4 ቢሊዮን ብር ቢደርስም የባንኩ ዕድገት ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ የካፒታሉ ዕድገቱ፣ የብድር፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑና ሌሎች እንቅስቃሴዎቹ የዕድገት ምጣኔ በእኩል ደረጃ ሊጓዙለት እንዳልቻሉ ባንኩ ገልጿል፡፡ አቶ ታቦር በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹የባንኩ የብድር መጠን ዕድገት ከፍተኛ መሆኑ ከካፒታሉ መጠን ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑና የብድሩ መጠን ልቆ በመሄዱ፣ የካፒታል አዲኩዌሲ ሬሺዮ ቀንሶ [ካፒታል ከሥጋት አኳያ ያለው ምጣኔ] ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ገደብ ጋር እየተቀራረበ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ጉዳይ ከወዲሁ ዕልባት ካላገኘ ባንኩ የገዥውን ባንክ መመርያ ባለመጠበቁ ምክንያት ከሚጣልበት ዕገዛ ባሻገር፣ የተከፈለ ካፒታሉን በአስቸኳይ ካላሳደገ በቀር ባንኩ ተጨማሪ ብድር እንዳያቀርብ ዕግድ ሊጣልበት ይችላል፡፡ ይህም የባንኩ ትርፋማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል ቦርዱ ተወያይቶበት አሁን ያለው የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ስድስት ቢሊዮን ብር ከሞላ በኋላ በድጋሚ ወደ 12 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ የውሳኔ ሐሳብ በማቅረብ ባለአክሲዮኖችን አስወስኗል፡፡

ከዚህ ባሻገር በ2011 ዓ.ም. የባንኩ ሠራተኞች ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት የበለጠ እንዲያሻሽሉ ለማስቻል ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ሥልጠናዎች እንዲከታተሉ ስለማድረጉም አስታውቋል፡፡  

ከዚህ ባሻገር አዋሽ ባንክ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በየጊዜው ለተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ዕርዳታ ሲለግስ ቆይቷል፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ባሳለፍነው ሒሳብ ዓመት ብቻ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ ስለመለገሱ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡  

አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2025 መጨረሻ ላይ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አሥር ምርጥ ባንኮች ውስጥ አንዱ ለመሆን የሚያስችለውን የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለዚሁ ዓላማው መሳካት ይረዳው ዘንድ የባንኩን የተከፈለ ካፒታል እ.ኤ.አ. በሰኔ 2023 መጨረሻ ላይ ወደ 12 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ተስማምተዋል፡፡ የአዋሽ ባንክ የተከፈለ ካፒታል ባለፈው ሒሳብ ዓመት ብቻ የ1.4 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ባንኩ እያስመዘገበ ካለው ትርፍ አኳያ ባለአክሲዮኖች ካፒታላቸውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማሳደግ እንደሚችሉ ሙሉ እምነት ተጥሎባቸዋል ተብሏል፡፡ አዋሽ ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት 44 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቶ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 410 አድርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች