Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

እናት ባንክ ከታክስ በፊት ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዝገበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከግል ባንኮች በርካታ ባለአክሲዮኖችን በመያዝ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው እናት ባንክ፣ ከታክስ በፊት 231.4 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ፣ የተጣራ ትርፉም (ከግብር ተቀናሽ) 202 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስታወቀ፡፡

እናት ባንክ በ2011 ሒሳብ ዓመት ያከናወናቸውን ሥራዎች ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደገለጸው፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ17 ሺሕ በላይ ደርሰዋል፡፡ ባንኩ ባለፈው ዓመት ከነበረው የሒሳብ እንቅስቃሴ ከታክስ ተቀናሽ በኋላ ያስመዘገበው ትርፍ የ27 በመቶ ዕድገት እንደታየበት አስታውቋል፡፡ የ231 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፉም ከ2010 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ18 ሚሊዮን ብር ዕድገት እንዳሳየ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ ሃና ጥላሁን ገልጸዋል፡፡

በ2011 ሒሳብ ዓመት ባንኩ ስላከናወናቸው ተግባራት ሪፖርት ያቀረቡት የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድም ዕድገት እንደተመዘገበ ገልጸዋል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ከ2010 ዓ.ም. አኳያ ሲታይ የ43 በመቶ ዕድገት በማሳት 7.12 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ጠቅሰዋል፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በአማካይ የ38 በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ እንደመጣም ገልጸዋል፡፡

ከባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ የቁጠባ ሒሳብ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ 48 በመቶውን ሲሸፍን፣ በጊዜ ገደብ የሚሰበሰብ ተቀማጭ 40 በመቶ፣ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ 12 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡ በ2011 ዓ.ም. የተመዘገቡ የባንኩ አስቀማጮች ቁጥር ከ100 ሺሕ በላይ መድረሱን ያመለከቱት የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ ከእነዚህ ውስጥ 56 በመቶው  ሴቶች እንደሆኑም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በተሸኘው የሒሳብ ዓመት ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ ምጣኔን የተረጋጋ ለማድረግ በማሰብና አነስተኛ ገንዘብ አስቀማጮችን ለማበራከት የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ ማድረግ እንደጀመረ ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም በሁሉም የተቀማጭ ሒሳብ ዓይነቶች ላይ፣ በተለይም በቁጠባና በጊዜ ገደብ ሒሳቦች ላይ የሚታየው ዕድገት የሚፈጥረውን የወለድ ወጪ ጫና በባንኩ ገቢ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ሥልቶችን በመንደፍ የፋይናንስ እንቅስቃሴው እንዲረጋጋ ለማድረግ ባንኩ ሲጥር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡  

የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ ማደጉን ተከትሎ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 9.2 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ለተለያዩ ዘርፎች ያበደረው ጠቅላላ የገንዘብ መጠንም 5.1 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ኃላፊዋ ጠቁመው፣ ይህም ከ2010 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ1.8 ቢሊዮን ብር ወይም የ54 በመቶ ዕድገት እንደታየበት አመላክተዋል፡፡  

እናት ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለኮንስትራክሽንና የወጪ ንግድ ዘርፎች በቀዳሚነት የሚቀመጡ ናቸው፡፡ በቦርድ ሰብሳቢዋ ሪፖርት መሠረት፣  ለኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰጠው ብድር ከጠቅላላው ብድር ውስጥ 20 በመቶ ሸፍኗል፡፡ ለወጪ ንግድ 21 በመቶ ተሰጥቷል፡፡ ለገቢ ንግድና አገር ውስጥ ንግድ እያንዳንዳቸው 17 በመቶ የደረሳቸው ሲሆን፣ የተቀረውን የ25 በመቶ ድርሻ ማኑፋክቸሪንግና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች፣ ትራንስፖርትና መሰል የንግድ ዘርፎች ተጋርተዋል፡፡

አስገዳጁ የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መነሳቱ ባንኩ አቅምና እንቅስቃሴ ላይ የበለጠ ለውጥ ለማስመዝገብ እንደሚያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቦንድ ግዥ መመርያውን መሻሩ ለሌሎችም የግል ባንኮች መልካም ዕድል እንደሚፈጥር ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

ባንኩ የፋይናንስ ዘርፉን የተቀላቀለው በቅርቡ ቢሆንም፣ እስካሁን ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የቦንድ ግዝ መፈጸሙ ታውቋል፡፡ እናት ባንክ በ2011 ዓ.ም. ያስመዘገበው ጠቅላላ ገቢ 982 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ ገቢ ካቻምና ካገኘው የ232 ሚሊዮን ብር ገቢ አኳያ የ31 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ተጠቅሷል፡፡  

እናት ባንክ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች 45 ቅርንጫፎችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ይህንን የቅርንጫፍ ቁጥር በ2012 ሒሳብ ዓመት ወደ 70 ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ተሾመ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል በቴክኖሎጂ የታገዘ የባንክ አገልግቶችን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ወንድወሰን፣ በተንቀሳቃሽ ስልክና በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ፕሮጀክት ተቀርፆ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ እነዚህን አገልግሎቶች በአራት ወራት ውስጥ ሥራ ይጀምራል ብለዋል፡፡

የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 1.2 ቢሊዮን ብር የተጠጋ ሲሆን፣ የባለአክሲዮኖች ብዛትም ከ17,000 በላይ ደርሷል፡፡ ከባለአክሲዮኖች ውስጥ የሴቶች ብዛት 64 በመቶ ሲሆን፣ በካፒታል መጠንም 59 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ ይህም ባንኩ የሴቶችን የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት ይዞት የተነሳውን ራዕይ ለማሳካት በሚያስችለው አካሄድ ላይ ለመሆኑ አመላካች ተደርጎ ቢታይም፣ የሴቶችን ድርሻ ከዚህም በላይ ለማሳደግ መሥራት እንደሚጠበቅበት ወ/ሮ ሃና ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  

ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ አክሲዮን ከመግዛት እስከ ባንክ መመሥረት የሚያስችላቸው አዋጅ መውጣቱን በማስታወስ፣ እናት ባንክም የዚህ ውሳኔ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለትልውደ ኢትዮጵያውያን የሚመች አሠራር እየዘረጋ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

እናት ባንክ በተለየ የሚታወቅበትንና ለብድር ማስያዣ ማቅረብ የሚቸገሩ ሴቶችን ለመደገፍ በቀረፀው ፕሮግራም መሠረት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ባንኩ ለሚሰጣቸው ብድር ማስያዣ ማቅረብ ለማይችሉ ሴቶች ብድር በማቅረብ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በ2011 ዓ.ም. ሲተገበር እንደነበር የጠቀሱት የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ ይህንን ለማስፈጸም ከባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻ ተከፋይ ላይ በመቶኛ እየቀነሰ ዋስትና ማቅረብ ለማይችሉ ሴቶች የብድር ዋስትና እንዲሆን በሥጋት ፈንድ ያስቀመጠው ገንዘብ መጠን 11.2 ሚሊዮን ብር እንደተመዘገበበት አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ በዚህ ዓመት በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ 56 ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በንግድ ሥራ የተሰማሩ ሴቶችን ለማገዝ በሚሰጠው ልዩ ድጋፍ በ2011 ዓ.ም. ካበደረው አጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ 933 ሚሊዮን ብር በአነስተኛ ንግድ ላይ ለተሰማሩ 714 ሴቶች ድጋፍ ማድረግ እንደቻለ ወ/ሮ ሃና ገልጸዋል፡፡ ሴቶች በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆኑ ለሁለት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የሰጠውን ብድር ወደ አሥር ሚሊዮን ብር ያሳደገ ሲሆን፣ በዚህም 991 ሴቶች የብድር ተጠቃሚ ለማድረግ እንደተቻለ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡  

ባንኩ ወደፊትም ቢሆን ከሌሎች አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሥራት ሴቶችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሠራ መሆኑን የገለጹትም ወ/ሮ ሃና፣ በሒሳብ ዓመቱ እናት ባንክ ለሴቶች የሚሰጠውን የባንክ አገልግሎት ለማሻሻል ተደራሽነትን ለማሳደግና የአመራር ክህሎታቸውን ከማሳደግ አኳያ የዓለም ባንክ የፋይናንስ ተቋም ከሆነው ጋር ስምምነት ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች