በቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት ከሚገነቡ 20 ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው በምዕራብ ጉጂ ሱሮ ባርጎዳ የተገነባው ትምህርት ቤት ሥራውን ጀምሯል፡፡ ኢፈቱላ ሱሮ ብርሃን የተባለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ የገቡ በፕሮጀክቱ የታቀፉ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር ወደ አራት ከፍ አድርጎታል፡፡
ቀዳማዊት እመቤት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ፕሮግራሞችን ነድፈው መንቀሳቀስ የጀመሩት ጽሕፈት ቤቱን እንደተረከቡ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በትምህርት ማሻሻያ ፕሮግራማቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች ትምህርታቸውን ከአንደኛ ደረጃ የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ለማስቀጠል 20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ይዘው ወደ ሥራ ከገቡ ዓመት አልፏቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለሚገነቡት ትምህርት ቤቶች ግንባታ 304.8 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ አራቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው በዚህ ዓመት ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምሩ በተያዘው ዕቅድ መሠረት ጎንደር፣ ምሥራቅ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ጉጂ የሚገኙት ሥራ መጀመራቸውን ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡
ጎንደር የሚገኘው የሎዛ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በይፋ ተመርቆ ሥራ እንደጀመረ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጭቋላ የተገነባው ኢፈ ሊበን ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁ ሥራ መጀመሩ ተነግሯል፡፡ በሰሜን ሸዋ ውጫሌ የተገነባው ኢፈ ሰላሌ ብርሃን፣ አሁን ደግሞ በምዕራብ ጉጂ የተገነባው ኢፈ ቱላ ሰሮ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ወደ ሥራ መግባታቸው ታውቋል፡፡
አራቱ ትምህርት ቤቶች በዚህ መልኩ ግንባታቸው ተጠናቆ ሥራ ሲጀምሩ፣ የተቀሩት 16ቱ ትምህርት ቤቶች በሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል፡፡
በሁሉም ክልሎች በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እጥረት ያለባቸው ቦታዎች ላይ የተገነቡትና እየተገነቡ ያሉት እነዚህ ትምህርት ቤቶች በተደራሽነት ምክንያት ቤት የሚቀሩ በተለይም ልጃገረዶችን የሚታደግ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ቀዳማዊት እመቤቲቱ በየክልሉ ለሚያስገነቧቸው 20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በየአካባቢው የመሠረተ ድንጋይ ዓምና አስቀምጠዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የጋምቤላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ የሶማሌ ክልል ለአመንጄ የጎል ትምህርት ቤት ይገኙባቸዋል፡፡
ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ከ20ዎቹ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በተጨማሪ በ400 ሚሊዮን ብር ወጪ ለዓይነ ሥውር ተማሪዎች የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ሌሎችም ማኅበራዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ አጠቃላይ ወጪውም 716.1 ሚሊዮን ብር መሆኑ ተነግሯል፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ የሚሸፈነውም ከለጋሽ ድርጅቶች በተገኘ ገንዘብ ነው ተብሏል፡፡