Monday, May 27, 2024

ብልፅግና ፓርቲ ሕጋዊ ዕውቅና ካገኘ የመንግሥት ሥልጣን ከኢሕአዴግ መረከብ አይችልም?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአራት ፖለቲካ ፓርቲዎች ግንባር የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ከተመሠረተና በአምስት አገር አቀፍ ምርጫዎች የመንግሥትነት ሥልጣንን ተቆጣጥሮ አገር የማስተዳደር ኃላፊነቱን እየተወጣ በሚገኝበት 25ኛ ዓመቱ መገባደጃ ላይ፣ ህልውናው ሊያበቃ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

የግንባሩ እናት እንደሆነ በሚነገርለት ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የበላይነት ሲመራ የዘለቀው ኢሕአዴግ በአምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ መቶ በመቶ የፓርላማውን መቀመጫዎች ተቆጣጥሮ የመንግሥትን ሥልጣኑን በ2008 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወር ዳግም ማስቀጠል ቢችልም፣ ቅቡልነቱ ጥቂት ሳምንታትን መሻገር አልቻለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ለመንግሥትነት ሥልጣኑ ከፍተኛውን ድርሻ ከሚሰጠው የኦሮሞ ሕዝብ ሥልጣን በያዘ በማግሥቱ (በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም.) ብርቱ ፖለቲካዊ ተቃውሞ የገጠመው በመሆኑ ነው፡፡

አምስተኛ ዓመት የምርጫ ዘመኑን በዚህ ተቃውሞ ውስጥ የጀመረው ኢሕአዴግ ከኦሮሞ ሕዝብ ከገጠመው ተቃውሞ ባለፈ፣ ሁለተኛ የሥልጣን መሠረቱ ከሆነው የአማራ ሕዝብና እንዲሁም ከሌሎች በርካታ አካባቢዎች ተመሳሳይ ተቃውሞ፣ ፖለቲካዊ ተግዳሮትና የቅቡልነት አደጋ ውስጥ ገብቷል፡፡

ነገሩ በዚህም አላበቃም፡፡ ከማኅበረሰቡ የገጠመው ብርቱ ተቃውሞ በአንድ በኩል እየተፋፋመ ሲሄድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከውስጡ በተወለዱ አለመግባባቶችና የሥልጣን ሽኩቻ ሲናጥ ከርሞ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ለኦሮሞ ሕዝብ ከሚታገለው የኦሮሞ ዴሞክራክ ፓርቲ (ኦዴፓ) በተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሥልጣን ትግሉ ድል አድራጊነት ተጠናቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የግንባሩ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ በኋላ፣ በርካታ ያልተጠበቁ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የፖለቲካ ልሂቃንን አስደምመዋል፡፡

በዚህ ያላበቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የቆየውን ኢሕአዴግ በማዋሀድ፣ እንዲሁም የኢሕአዴግ አጋር ተብለው የሚታወቁትን አምስቱን ታዳጊ ክልሎች የሚያስተዳድሩ ፓርቲዎችን በማካተት ብልፅግና ፓርቲ የተሰኘ አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ለመመሥረት የመጨረሻው ጫፍ ላይ ከሰሞኑ ደርሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢሕአዴግን የማዋሀድና አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ የመመሥረቱ ጉዟቸው የኢሕአዴግ መሥራች፣ አድራጊና ፈጣሪ እንደሆነ ከሚነገርለት ሕወሓት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ ሕዋሓት ሊመሠረት ጫፍ ከደረሰው ብልፅግና ፓርቲ ተቃራኒ የቆመ ሲሆን፣ የዚህ ፓርቲ አባል ላለመሆንም በሥራ አስፈጻሚና በማዕከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የመጨረሻ ውሳኔውንም በሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ አማካይነት በቅርቡ እንደሚያሳልፍ አስታውቋል፡፡ በተቃራኒው ግን የኢሕአዴግ ምክር ቤት ኢሕአዴግን ለማዋሀድ ከስምምነት መድረሱን ተከትሎ፣ ሦስቱ ዋነኛ አባላቱ ማለትም ኦዴፓ፣ አዴፓና ደኢሕዴን በጠቅላላ ጉባዔያቸው አማካይነት ራሳቸውን አፍርሰው ብልፅግና ፓርቲን ለመቀላቀል በተጠናቀቀው ሳምንት ወስነዋል፡፡

ከዚህ በተጫማሪም ከአምስቱ አጋር ፓርቲዎች መካከል አራቱ ራሳቸውን አክስመው ብልፅግና ፓርቲን ለመቀላቀል ተመሳሳይ ውሳኔያቸውን በተጠናቀቀው ሳምንት አሳልፈዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣዮቹ ቀናት ወይም ሳምንታት የሚጠበቀው ዓብይ ጉዳይ፣ የብልፅግና ፓርቲን የምሥረታ ጉባዔ ማካሄድና ፓርቲውን በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት ማግኘት ነው፡፡

ይህ ቢሆንም ሊመሠረት ከታሰበው “ብልፅግና” የተሰኘ ውህድ ፓርቲ አፈንግጦ በተቃራኒ የቆመው ሕወሓት፣ ሌሎቹ የግንባሩ አባል ፓርቲዎች ውህደቱን ለመፈጸም የተከተሉት መንገድ ሕጋዊ አለመሆኑን በመጥቀስ ሲቃወም ቆይቷል፡፡ የዚህ ተቃውሞ መነሻ ውህደቱ እንዲፈጸም የኢሕአዴግ ምክር ቤት የመወሰን ሥልጣን የለውም የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን የኢሕአዴግ ምክር ቤት ውህደቱ ላይ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ በውህደቱ የተስማሙት ሦስቱ ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው ባለፈው ሳምንት ባካሄዱት የተናጠል ጠቅላላ ጉባዔያቸው ውህደቱን ተቀብለው፣ ብልፅግና ፓርቲን ለመመሥረት ውሳኔ በማሳለፋቸው ሕወሓት በውህደቱ ላይ ባነሰው የሕጋዊነት ጥያቄና ተቃውሞ ላይ ውኃ አፍሰውበታል፡፡

ሕወሓት ከሥራ አስፈጻሚው እስከ ማዕከላዊ ኮሚቴው ድረስ ባሉት እርከኖችና ከፍተኛ አመራሮቹ ውህደቱን እንደማይቀበለውና ሕወሓትን በማክሰም ወደ ሚመሠረተው ውህድ ፓርቲ እንደማቀላቀል መወሰኑን፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከቀናት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ይህ አቋም የመጨረሻ ውሳኔውን የሚያገኘው በሕወሓት ሕገ ደንብ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔው የውህደቱ አባል ላለመሆን ሲወስን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ሕወሓት ውህደቱን በመርህ ደረጃ እንደሚስማማበት የሚናገሩት ሊቀመንበሩ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ነገር ግን የውህዱ ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራምን ምን እንደሆነ ፓርቲያቸው አለማወቁና ስለፖለቲካ ፕሮግራሙ ለማወቅ ያቀረቡት ጥያቄም ምላሽ አለማግኘቱ ዋናው የልዩነት ምንጭ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የውህዱ ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ጉዳይ ዋናው የልዩነት ምንጭ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ አሁን ውህደቱን ለመፈጸም የሚችልበት ቁመና ላይ እንዳልሆነ፣ በአባል ድርጅቶቹ መካከል የሐሳብ አንድነትና መተማመን እንደሌለ በተጨማሪ መከራከሪያነት ያቀርባሉ፡፡ ይህንን ተከትሎም ሕወሓት በሌለበት ውህድት የሚፈጽሙት ቀሪ ድርጅቶች፣ ከውህደቱ በኋላ የሚመሠርቱት ፓርቲ (ብልፅግና ፓርቲ) የኢሕአዴግን መንግሥታዊ ሥልጣን በቀጥታ መውረስ አይችልም የሚል መከራከሪያ ከሕወሓት አመራሮች መደመጥ ጀምሯል፡፡

“ብልፅግና ፓርቲ” የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣንን ሊወርስ አይችልም?

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ውህደትንና ሊመሠረት ጫፍ የደረሰው ብልፅግና ፓርቲን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ውህደቱን ለመፈጸም የተስማሙት የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎችና የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶች ውህደቱን ለመፈጸም ሲሉ በተናጠል ሕጋዊ ሰውነታቸውን ለማከሰም መወሰናቸው አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህ የሕወሓት ሊቀመንበር ሥጋት ማጠንጠኛ ሕጋዊ ሰውነታቸውን አክስመው ውህደቱን ለመቀላቀል ፍላጎት ያሳዩትና እየወሰኑ ያሉት ፓርቲዎች፣ ሁሉም በሕዝብ ተመርጠው በክልል መንግሥታትና በፌዴራል መንግሥት ደረጃ አገር በማስተዳደር ላይ ያሉ መሆናቸው ነው፡፡

የውህደቱ ጉዳይ በፓርቲ ብቻ የታጠረ ጉዳይ አይደለም የሚሉት ሊቀመንበሩ፣ የፓርቲዎቹ መክሰምና ውህደቱ መንግሥትንም የሚያፈርስ ሌላ ቀውስ ይዞ እንደሚመጣ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፣ “እነዚህ ፓርቲዎች በሕዝብ ተመርጠው በክልልም በፌዴራልም ሥልጣን ይዘዋል፣ እስከ መጪው ግንቦት ድረስ የገቡት ኮንትራት አላቸው፡፡ በመሆኑም መንግሥትን መምራት የሚችሉት በተመረጡበት ፕሮግራም ነው፡፡ ምክንያቱም በፕሮግራማቸው ነው ሕዝቡ የመረጣቸው፡፡ ስለዚህ መሀል ላይ ልትቆርጠው አትችልም፡፡ መሀል ላይ ከተቆረጡ ሥልጣንም መልቀቅ አለባቸው፤” ሲሉ ደብረ ጽዮን ይከራከራሉ፡፡

ሕዝቡ የመረጠው ኢሕአዴግን እንደሆነ የሚናገሩት ደብረ ጽዮን፣ ውህደት ፈጽሜያለሁ ብሎ በብልፅግና ፓርቲ ስም የኢሕአዴግን የመንግሥት ሥልጣን መውረስ እንደማቻል መፍትሔውም ከሥልጣን መልቀቅ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

“መንግሥት የሚፈርስ ከሆነ ደግሞ እስከ ምርጫው ድረስ አገር የሚያስተዳድር የሽግግር መንግሥት መመሥረት አለበት፡፡ ምክንያቱም በአንድ ጊዜ ኢሕአዴግም ብልፅግና ፓርቲም መሆን አይቻልም፡፡ አለበለዚያ ግን ቀውስ ነው ሊፈጠር የሚችለው፤” ሲል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት የሕግ ምሁሩ አቶ ጌታቸው ረዳም በሊቀመንበሩ አስተያየት በመሠረታዊነት ይስማማሉ፡፡ ቢሆንም የአቶ ጌታቸው አስተያየት ከሕጋዊ አመክንዮ ይልቅ ሞራላዊ አመክንዮ ላይ ይመሠረታል፡፡

ኢሕአዴግን የመሠረቱት ድርጅቶች ራሳቸውን አክስመው እንደ አዲስ የሚቋቋመውን ብልፅግና ፓርቲን ቢቀላቀሉም፣ ብልፅግና ፓርቲ ኢሕአዴግን ለመውረስ በመሠረታዊነት ከሁለት የኢሕአዴግ ተፈጥሯዊ ባህሪዎች ጋር ትስስር ሊኖረው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

አንደኛው የአዲሱ ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም የኢሕአዴግን ፕሮግራም በማሻሻል ላይ ብቻ የተመሠረተ ከሆነና ሁለተኛው ደግሞ በኢሕአዴግ ሕገ ደንብ ላይ ተመሥርቶ፣ ነገር ግን የጠበቡ ናቸው በሚላቸው ክፍተቶችን አስተካክሎ ለመቀጠል የወሰነ እንደሆነ ኢሕአዴግን ለመውረስ እንደሚቻል ለሚዲያዎች ከሰጡት አስተያየት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም መሆን የሚችለው ግን ሁለም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በአንድነት መክረው መስማማትና መፍቀድ ከቻሉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በዘለለ ግን በፕሮግራምም፣ በመተዳደሪያ ደንብም ሆነ በአሠራር ሙሉ በሙሉ ከኢሕአዴግ የተለየ ነገር ይዞ ኢሕአዴግን ለመውረስ ብልፅግና ፓርቲ የሞራል መሠረት እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

 “አባ ወራውን ገድሎ አንድ ቤት የገባ ሰው ሕግና ሥርዓትን ካልፈራ በስተቀር የቤቱ ወራሽ ነኝ ሊል አይችልም፤” የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ ብልፅግና ፓርቲም ከዚህ በተቃራኒ ከተጓዘ ውጤቱ ካስቀመጡት ምሳሌ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠየቁት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ የሕወሓት አመራሮች የሚያቀርቡትን ክርክር አጣጥለውታል፡፡ አቶ ፍቃዱ ኢሕአዴግ ይዋሀዳል ማለት አዲስ ፓርቲ ይፈጠራል ማለት እንዳልሆነ፣ ብልፅግና ፓርቲ ማለት ኢሕአዴግ ውስጥ የነበሩት ፓርቲዎች ሌላ ማንነት ይዘው የሚፈጥሩት ውህድ ፓርቲ መሆኑን ይገልጻሉ።

 “ለምሳሌ በኦሮሚያ ኦሕዴድ ነው የተመረጠው፣ ስሙን ቀይሮ ኦዲፒ ሆኖም መንግሥት ሆኖ እየሠራ ነው። በተመሳሳይ ብአዴን በአማራ ተመርጧል፣ ስሙን ቀይሮ አዴፓ ሆኖ መንግሥት ሆኖ እየመራ ነው፤” የሚሉት አቶ ፍቃዱ፣ ተዋህደው ብልፅግና ፓርቲ የሚመሠርቱት ድርጅቶች በኢሕአዴግ ውስጥ ሆነው ያገኙትን መብትና ግዴታዎችን ይዘው ነው ወደ መዋሀድ የሚመጡት፤” ብለዋል።

 የውህደቱ አፈጻጸም የሚሆነውም በመጀመሪያ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደቱን ከፈጸሙ በኋላ፣ በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ አጋር ፓርቲዎች ብልፅግና ፓርቲን እንደሚቀላቀሉ ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያ የሚዋሀዱት ፓርቲዎች በምርጫ ያገኙትን መንግሥት የመሆን መብታቸው ይዘው እንደሚዋሀዱ የተናገሩት አቶ ፍቃዱ፣ ኢሕአዴግ ስምና አደረጃጀቱን በሚቀይርበት ጊዜ ለኢሕአዴግ ተሰጥተው የነበሩ መብቶችና ግዴታዎች ለውህዱ ፓርቲ እንደሚተላለፉ ገልጸዋል።

“ስለሆነም ኢሕአዴግ ፓርቲዎች ከተዋሀዱ መንግሥት ሆነው በፓርላማ መቀጠል አይችሉም የሚል ነገር አይኖርም። በሕግ ደረጃም እንዲህ የሚል ነገር የለም፤” ብለዋል። በቅርቡ የተሻሻለው የምርጫና ፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ የፓርቲዎች ውህደትንና ውህደት ስለሚፈጸምበት መንገድ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡

በዚህ አዋጅ ድንጋጌ መሠረት “ውህደት” ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ በሕግ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ሕጋዊ ሰውነታቸውን በመተው፣ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሠርቱበት ሒደት እንደሆነ ትርጓሜ ተስጥቶታል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት የሚፈጸመውም ለመዋሀድ የፈለጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን በጽሑፍ ለምርጫ ቦርድ ሲያቀርቡ፣ ቦርዱም አዋጁ ባስቀመጣቸው ሥነ ሥርዓቶች መሠረት የቀረበ መሆኑን መርምሮ ሲያድቀው እንደሆነ ያደነግጋል፡፡

የውህደት ጥያቄ ሲቀርብ መሟላት ከሚገባቸው መሥፈርቶች መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ለመዋሀድ ፈለጉት ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት የፓርቲው ጉባዔ አካሄደው ውህደቱን ጉባዔው የተቀበለ ስለመሆኑ የሚገልጽ ውሳኔ፣ ፓርቲዎቹ ስለውህደቱ ዝርዝር ጉዳዮች ያደረጉት የጽሑፍ ስምምነትና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሲዋሀዱ የሚኖረው አዲስ ስምና በአዋጁ አንቀጽ 67 መሠረት የተዘረዘሩ ሰነዶች፣ ማለትም የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረቻ ጽሑፍ፣ የፖለቲካ ፓርቲው ፕሮግራም፣ የፖለቲካ ፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ፣ የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች ስምና አድራሻ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች በኃላፊነት ለመሥራት መስማማታቸውን የሚያስረዳ በፊርማቸው የተረጋገጠ ሰነድ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ቦርዱ የውህደት ጥያቄው በሕጉ መሠረት የቀረበለት መሆኑን ሲያምን፣ ለተዋሀዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰጥቶ የነበረውን የምዝገባ የምስክር ወረቀት ይሰርዛል፡፡ በዚሁ ሕግ መሠረትም አዲሱን ፓርቲ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚመዘግብ አዋጁ ይደነግጋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ መዋሀድ የሚያስከትለው ውጤትን በተመለከተ ካስቀመጣቸው ድንጋጌዎች መካከልም፣ የውህደት ውጤት የሆነው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የተዋሀዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወራሽ መሆን፣ የተዋሀዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መብትና ግዴታ መተላለፍ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ውህደት የፈጠሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባል የነበረና በማናቸውም ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶች ተመራጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የነበረ ሰው፣ በውህደቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ መቀጠል የማይፈልግ ከሆነ የግል ተመራጭ እንደሆነ ተቆጥሮ የቀረውን የምርጫ ዘመን የሚያጠናቅቅ መሆኑ ተደንግጓል፡፡

የእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ንብረት፣ ገንዘብና አስፈላጊ ሰነዶች በውህደት ወደ ተመሠረተው የፖለቲካ ፓርቲ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲተላለፍ ቦርዱ ትዕዛዝ እንደሚሰጥም አዋጁ ይደነግጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -