አዋሽ ባንክ እስከ 4.5 በመቶ ወለድ ቀንሷል
የባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣት የባንክ ብድር አይቀመስ እስኪሆን እንዳደረሰው ሲነገር ሰንብቷል፡፡ ወለድ ማስከፈያው ማሻቀቡ ለዋጋ ግሽበት መንስዔ እንደሆነም ከኢኮኖሚ ባለሙያዎች ትንታኔ መረዳት ይቻላል፡፡ የባንኮች የብድር ማስከፈያ ወለድ ማሻቀቡ በጠቅላላው ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ በአንፃሩ ባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔያቸው እያሻቀበ የመጣበትን ምክንያት በማቅረብ ሲሞግቱ ከርመዋል፡፡
መንግሥት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የግል ባንኮች ላይ ያስቀመጠው አስገዳጅ የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ እንደ ምክንያት ያቀርባል፡፡ የግል ባንኮች ከሚሰጡት እያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶውን ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ መገደዳቸው የማበደሪያ ወለድ መጠናቸው ላይ ጭማሪ ለማድረግ ምክንያት እንደሆናቸው ያስቀምጣሉ፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በጠቅላላው ከ116 ቢሊዮን ብር በላይ ለቦንድ ግዥ ማዋላቸው የማበደር አቅማቸውን በመቀነሱ የትርፍ ምንጫቸውን ለማሳደግ የወለድ ዋጋቸውን ከፍ እንዳደረገው ይሞግታሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ጥቂት ብድር ስለሚሰጡና ከፍተኛ ፍላጎት ስላለ ወለዳቸውም በዚያ ደረጃ እያደገ እንደመጣ ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ በመሆኑም አብዛኞቹ ባንኮች ከፍተኛ የማበደሪያ ወለድ መጠናቸውን እስከ 20 በመቶ እንዳሳደጉ በየስብሰባውም ወቀሳ ሲሰነዘርባቸው እንደከረሙ ለመታዘብ ተችሏል፡፡
የግል ባንኮች በብዙ ወጪ ካጠራቀሙት ገንዘብ ውስጥ 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ ቢያውሉም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚያስብላቸው የተቀማጭ ወለድ ሦስት በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ለአስቀማጮች የሚታሰበው ወለድ ከአምስት በመቶ ወደ ሰባት በመቶ በማደጉ፣ ለባንኮችም የሦስት በመቶው ወለድ ወደ አምስት በመቶ ከፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አቅማቸው ሲፈተን መቆየቱንና በዚህም ሲያማርሩ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ አንዳንዶቹም በኪሳራነት ሲፈርጁት ታይተዋል፡፡
የ27 በመቶ ቦንድ የገዙበትን ገንዘብ ለብድር ቢያውሉት ኖሮ አሁን ብዙ ለመሥራትና እስካሁን ካስመዘገቡትም በላይ ውጤት ለማምጣት ይጠቅማቸው እንደነበር በዘርፉ ባለሙያዎች ትንታኔ ሲሰጡበት ቆይተዋል፡፡ ምንም እንኳ የመንግሥት ዓላማ በቦንድ ግዥ የሰበሰበውን ገንዘብ በልማት ሥራዎች ላይ ለመዋል የሚያግዝ የአገር ውስጥ ፋይናንስ እንደ ልብ ለማግኘት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት አካሄድ ባንከች ላይ አደጋ ይጋብዛል በማለት መመርያው እንዲሰረዝ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር አቤቱታውን ቢያሰማም ሰሚ አላገኘም፡፡
ለዓመታት ያነታረከው ይህ መመሪያ ሳይታሰብ ከሳምንት በፊት እንደሚሻር የሚያትት ዜና መሰማቱ የግል ባንኮችን አስፈንድቋል፡፡ የቦንድ ግዥ መመርያው መሻር በኢኮኖሚ ላይም አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚያመጣ ከወዲሁ እየተገለጸ ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የመመርያ መነሳት በማስመልከት ሰሞኑን እንደገለጹት፣ በባንኮች የሚሽከረከረውን የገንዘብ ፍሰት እንዲጨምር ስለሚያደርገው፣ ባንኮች ያናሩትን የብድር ወለድ ዝቅ ያደርጉታል፡፡
የመመርያው መነሳት የግል ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሳይገጥማቸው ብድር እንደ ልብ ማቅረብ እንዲችሉ ያግዛቸዋል ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል በቅርቡ በቋሚነት ለሚጀመረው የመጀመሪያ ደረጃ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ግብይት ላይ ባንኮች እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ፣ የ27 በመቶው የቦንድ ግዥው መመሪያ መነሳቱን የባንኩ ገዥ ተናግረዋል፡፡
የመመሪያው መነሳትን ተከትሎ በጥቂት ቀናት ውስጥ አንዳንድ ባንኮች የማበደሪያ ወለድ ቅናሽ ስለማድረጋቸው ፍንጮች ታይተዋል፡፡ አዋሽ ባንክ ቀደም ብሎ የማበደሪያ ወለዱ ላይ ቅናሽ እንደሚያደርግ በይፋ በመግለጹ ሌሎችም ይህንኑ መንገድ ይከተላል የሚለውን ግምት አሳድሯል፡፡
ባንኩ ማክሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው፣ እስካሁን ሲሠራበት የቆየው የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ከ0.5 በመቶ እስከ 4.5 በመቶ ቅናሽ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመሪያ መሻሩ ይፋ በተደረገ በጥቂት አፍታ እንዲህ ያለው ውሳኔ ላይ መድረሱ ቢሰማም፣ ባንኩ ግን ከውሳኔ ላይ የደረሰው ቀደም ብሎ እንደሆነና፣ የወለድ ምጣኔውን ለመቀነስ ሲያጠና በነበረበት ወቅት መመሪያ በመሻሩ ዕርምጃውን እንደወሰደ የአዋሽ ባንክ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ የ27 በመቶው የቦንድ ግዥ መመርያ መነሳቱ እንደተሰማ የወለድ ምጣኔውን የመቀነስ ዕቅዱን እንዳፋጠነው የባንኩ ኃላፊዎች በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
አዋሽ ባንክ የብድር ወለድ ቅናሽ ማድረጉ በገበያው ውስጥ እየታየ ያለውን የዋጋ ግሽበት በጥቂቱም ቢሆን ለመቀነስ አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል በማመን የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነ የባንኩ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ቶሌራ ገልጸዋል፡፡ ባንኩ የወሰደው ዕርምጃ የተቀዛቀዘውን የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃውም ተስፋ ተደርጎበታል፡፡ እንደ አቶ ደሳለኝ ከሆነ፣ ባንኩ የወለድ ምጣኔ ቅናሽ ሲያደርግ ኢንቨስትመንት እንደሚበረታታ በማመኑም የወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡ የባንኩ የንግድ ብድር ኃላፊ አቶ ቶማስ ፍቃዱም የወለድ ቅናሽ ከመደረጉ በፊት ጥናት ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ‹‹የትኛውን ወለድ ብንነካ፣ የትኛው ኅብረተሰብ ይጠቀማል? በማለት ባንኩንም ሆነ ኢኮኖሚውን በማይጎዳ መልኩ ተጠንቶ የተወሰነ ነው›› ብለዋል፡፡
የቦንድ ግዥ መመርያው የፈጠረውን መዛባት ለማካካስ ሲባል ተበዳሪዎች ላይ የተጫነው የወለድ ገቢ በማሳደግ፣ በተበዳሪዎች የወለድ ጫና አሳድረዋል የሚል ሮሮ ይቀርብ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደሳለኝ፣ ለዚህ አንዱ ምክንያት 27 በመቶው የቦንድ ግዥ ባንኮች ላይ ተፅዕኖ በማሳረፉ ነው ብለዋል፡፡ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖርና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲሰፍን መንግሥት ቅድሚያ ለሰጣቸው ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የግል ባንኮችም ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የተወሰደ ዕርምጃ ነበር፡፡
መምርያው ይህን ቢልም በታሰበው መሠረት ተከናውኗል ወይ? የሚለው ግን አነጋጋሪ ሆኖ ይገኛል፡፡ አቶ ደሳለኝ እንደሚሉት፣ መመርያው ይዞት የተነሳው ሐሳብ ላይ ቅሬታ የላቸውም፡፡ ነገር ግን ይህ በቦንድ ግዥ የተሰበሰበው ገንዘብ ለተፈለገው ዓላማ ውሏል ወይ? የሚለው ጉዳይ ላይ ግን ሥጋት አላቸው፡፡ ሌሎች እንደ ህንድ፣ ፓኪስታንና ጃፓን ያሉትን ጨምሮ ከመመርያው ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ፖሊሲዎች እንደተገበሩ አቶ ደሰለኝ ሲገልጹ፣ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ወይም የተሻለውን ብድርን ወደ እነዚህ ዘርፎች እንዲውል ማድረግ አዲስ እንዳልሆነ ያመላክታሉ፡፡
ችግሩ ግን የግል ዘርፉን ተፅዕኖ ውስጥ የከተተ፣ ባንኮችም የብድር ማስከፈያ ወለዳቸውን እንዲጨምሩ ያስገደደ በመሆኑ፣ መበደር አዳጋች እስኪሆን ድረስ የተጋነነ የብድር ወለድ ማስከተሉ ነበር፡፡ ችግሩ ምን ያህል እንደነበር ለማስረዳትም አዋሽ ባንክ ለቦንድ ግዥ ምን ያህል ገንዘብ እንደዋለ በአስረጅነት አቅርበዋል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ አዋሽ ባንክ 17.1 ቢሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ፈጽሟል፡፡ ከዚህ ውስጥ አምስት ዓመት ሞልቶት ተመላሽ ከተደረገለት ገንዘብ ውጪ፣ በብሔራዊ ባንክ ለዚሁ ቦንድ ግዥ ያዋለው 12.1 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ አለው፡፡ ከዚህ ውስጥ 7.1 ቢሊዮን ብሩን በሦስት መቶ ወለድ ግዥ የፈጸመበት ነው፡፡ አምስት በመቶ ወለድ የ4.7 ቢሊዮን ብር ቦንድ መግዛቱን አስታውሰዋል፡፡
አሁን መመርያ ተነስቷል፡፡ በመመርያው ሰበብ ወለዳቸውን ከፍ አድርገው የነበሩ ባንኮች ወለድ በመቀነስ ኢኮኖሚውን የማረጋጋት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡ አዋሽ ባንክ ተጨማሪ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ አቅዷል፡፡ ባንኩ ይህንን ዕርምጃ ሲወስድ ተበዳሪዎች በአገልግሎታቸውና በሚያቀርቡት ምርት ላይ የዋጋ ማሻሻያ እንደሚያደርጉ በማሰብ ጭምር እንደሆነም አስታውቋል፡፡
አዋሽ ባንክ ቅናሽ ያደረገበት የብድር ወለድ ማስከፈያ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎችና የብድር ዓይነቶች እንደየደረጃው ይተገበራል ብሏል፡፡ ሰፊ የብድር ወለድ ቅናሽ ከተደረገላቸው ዘርፎች ውስጥ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ እሴት በመጨመር ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለሚያስገኙ የኢኮኖሚ ዘርፎች ጠቀም ያለ የወለድ ቅናሽ ይደረጋል ተብሏል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶችም ባንኩ ከፍ ያለ የወለድ ቅናሽ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የአገልግሎት ዘርፍ ሆነው የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ለሚታወቁ የቱሪዝምና ባለኮከብ ሆቴሎች፣ አገልግሎት በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ለሚያስገኙ ንግድ ሥራዎችም የወለድ ቅናሹ የተሻለ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ግብርናም እስከ 4.5 በመቶ የወለድ ቅናሽ ከሚደረግባቸው ዘርፎች ውስጥ መካተቱን የባንኩ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ የባንኩ ዕርምጃ ዓመታዊ ገቢው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል አልሸሸጉም፡፡ በዚህ ዕርምጃው እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር የወለድ ገቢ ሊያጣ እንደሚችል በጥናት መታየቱን አቶ ደሳለኝ ገልጸው፣ ባንኩ ይህንን ገቢ ቢያጣም፣ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አስበልጧል ብለዋል፡፡ ባንኩ ተጨማሪ ሀብት በማሰባሰብ ያካክሰዋል ተብሏል፡፡ የብድር ወለድ ቅናሹ ተጨማሪ ተበዳሪዎችን ሊስብ ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ለባንኩ ኃላፊዎች ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መነሳት ብዙ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዲፈስ ያደርጋል የሚለው ይገኝበታል፡፡ የገንዘብ አቅርቦቱ መብዛት በምርትና ኢንቨስትመንት እስካልታገዘ ድረስ የዋጋ ግሽበት አያመጣም ወይ ለሚለው ጥያቄ አቶ ደሳለኝ በሰጡት ምላሽ ይህ አይከሰትም ብለዋል፡፡ ሲያብራሩም ለቦንድ ግዥ የዋለው ገንዘብ የሚመለሰው አምስት ዓመት ከሞላው በኋላ በየዓመቱ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ገንዘብ ወደ ገበያ ከመጣ የዋጋ ግሽበት ያስከትላል የሚለው ሥጋት አይሆንም ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ያለንበት ሁኔታ ብድር ብንፈቅድ እንኳ የማንለቅበት ወቅት ነው፤›› ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ በብሔራዊ ባንክ ገንዘቡን በየዓመቱ የሚመለስ በመሆኑ የተባለው ሥጋት አይኖርም ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለቦንድ ግዥ ያዋለውን ገንዘብ አንድ ጊዜ ቢለቀው እንኳ የዋጋ ግሽበት ሊያመጣ እንደማይችል ሞግተዋል፡፡ እንደውም ገንዘቡ ቢለቀቅ ካለው ዕጥረት አኳያ ለግሉ ዘርፍ ተፈላጊውን የገንዘብ መጠን በማቅረብ የአቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ይረዳል ብለዋል፡፡ ምርት በኢኮኖሚ ውስጥ እንዲስፋፋ የሚያስችልና ለዋጋ ግሽበቱ መረጋጋት አስተዋጽኦ የሚያበርክት ይሆናል በማለት አብራርተዋል፡፡
አቶ ቶማስ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በባንኮች እጅ ያለውን ገንዘብ ዝቅተኛ ሆኖ ሳለ ወለድ እንዲቀንስም በመደረጉ በርካታ ተበዳሪ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይሁንና በቅናሹ ሰበብ ሊመጣ የሚችለውን ተበዳሪ ግምት ውስጥ በማስገባት ሊመጣ የሚችል አስቀማጭ ስለሚኖር አቅርቦቱ ከተቀማጩ ሊመጣጠን የሚችልበት ዕድል እንዳለ አብራርተዋል፡፡
አዋሽ ባንክ ባደረገው ማሻሻያ መሠረት፣ ከፍተኛውን የ17.5 በመቶ ወለድ ወደ 15.75 ዝቅ አድርጓል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ የባንኩ ዝቅተኛ የብድር ወለድ 8.5 በመቶ እንደሆነም አቶ ቶማስ ገልጸዋል፡፡
የ27 ቦንድ ግዥ መነሳቱን ተከትሎ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች የግል ባንኮች ብድር ቢሰጡ ይሻላል በሚለው ሐሳብ ላይ የሚስማሙት አቶ ደሳለኝ፣ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች ቢለይ የግል ባንኮችም ማበደር እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር በሌሎች አገሮችም እንደሚደረግ፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ኢኮኖሚ ዘርፎች ብድር እንዲፈስ የማድረግ የፖሊሲ ውሳኔዎች እንዳሉም አስታውሰዋል፡፡
የመንግሥት የቦንድ መመሪያ ውጤታማ ነው ወይም አይደለም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለተመረጡ ዘርፎች ከሚውለው ጠቅላላ ብድር ውስጥ 20 በመቶ ለግብርና እንዲሰጥ፣ ይህንን ያህል ለኢንዱስትሪ ይዋል ቢባል ኖሮ የተሻለ ውጤት ሊመዘገብ ይችል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አዋሽ ባንክ እነዚህን ዘርፎች የመደገፍ ፍላጎት እንዳለውና እስካሁንም ዘርፎቹን ገሸሽ እንዳላደረጋቸው ተናግረው፣ የብድር ወለድ ቅናሽ ያደረገባቸው ዘርፎች መንግሥት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ያስቀመጣቸው እንደሆኑ አስታውሰዋል፡፡