የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለ አሥር ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት ወደ ሥራ ለመግባት ሲንደረደር ለመቋቋም የሚያስፈልገውን መነሻ ካፒታል የማሟላት ውጣ ውረድ አጋጥሞታል፡፡
ብርሃን ባንክ በወቅቱ ተግዳሮት ከነበሩበት አንዱና ዋኛው የነበረው ካፒታል የማሟላት ፈተና በባንኩ ደንበኞች ተቀርፎለት ወደ ሥራ ቢገባም፣ ተግዳሮቱ ግን እንደማይዘነጋ የባንኩን አሥረኛ ዓመት ምሥረታ ለማሰብ በተሰናዳው ፕሮግራም ወቅት ተንፀባርቋል፡፡ ፈታኝ ሁኔታዎችን አልፎ ወደ ሥራ ከገባ በኋላም በመጀመርያው ዓመት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወይም 600 ሺሕ ብር ገደማ ኪሳራ በማስመዝገብ ሥራ የጅማሬውን ዓመት ለማጠናቀቅ ተገዷል፡፡ ይህ አፈጻጸም ወደፊት ይቀጥል ይሆን? የሚል ሥጋት ቢያሳድርም፣ በሁለተኛው ዓመቱ የቀደመ ኪሳራውን አጣፍቶ አትራፊ መሆን እንደቻለ የሒሳብ ሪፖርቱ አመላከተ፡፡
በዚሁ የተጓዘው ብርሃን ባንክ፣ በትርፍ ብቻም ሳይሆን በካፒታል፣ በሰው ኃይልና በሌሎችም መስኮች አቅሙን ማጎልበት በመቻሉ፣ የዘጠኝ የትርፍ ዓመታትን አሳልፎ አሥረኛ ዓመቱን ለማክበር በቅቷል፡፡ በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ የታየው ውጤትም ባንኩ በብዙ መንገድ ወደፊት እንደተራደመ ይጠቁማል፡፡ ለዚህ በአብነት የሚጠቀሰው በ2011 ዓ.ም. ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ ነው፡፡ ከታክስ በፊት የባንኩ ትርፍ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በማለፍ 580 ሚሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ብርሃን ባንክ አሥረኛ ዓመቱን ማክሰኞ፣ ኅዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ባከበረበት ወቅት እንደተወሳው፣ በግማሽ ሚሊዮን ብር ኪሳራ የተጀመረው ጉዞ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ማትረፍ አሸጋግሮታል፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉማቸው ኩሴ እንደገለጹት፣ ባንኩ እዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ ብዙ ለፍቷል፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት ሲቋቋም በመሥራቾቹ የታሰበው ውጥን በአብዛኛው ዕውን መሆኑን የሚመሰክር ውጤት ባንኩ ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡ በደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ባንኩ ያስመዘገበው ውጤት አበረታች እንደነበር የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ባንኩ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በተደራሽነት፣ በሀብት አሰባሰብ፣ በኦፕሬሽን ክንውኖች እንዲሁም በካፒታል አቋም፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ መልካም የሚባሉ ሥራዎች አከናውኗል፡፡ አያይዘውም ወደፊት በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በሰው ኃይል ልማት፣ በደንበኞች አገልግሎት እንዲሁም የራሱን ዋና መሥሪያ ቤት በመገንባቱ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም አላሮ በበኩላቸው፣ ባንኩ ባለፉት አሥር ዓመታት እንቅስቃሴው በርካታ ውጤቶች እንዳስመዘገበ አስታውሰው፣ ባንኩ ስለሚገኝበት ደረጃም ገልጸዋል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የጠቀሱት አቶ አብርሃም፣ የ15 ቢሊዮን ብር የተቀማጭ ገንዘብ እንዳሰባሰበና የብድር ክምችቱም አሥር ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላላ ሀብቱም 19 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት ተብራርቷል፡፡ የባንኩ ደንበኞች ብዛት ከ706,000 በላይ መድረሳቸው ተዳምረው የባንኩን ዕድገት ደረጃ አመላክተዋል፡፡ ብርሃን ባንክ በአሁኑ ወቅት ከአራት ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ የቅርንጫፎችን ቁጥር 208 አድርሷል፡፡
እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ፣ በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በተመለከተ የሞባይል ባንኪንግ፣ የካርድ ባንኪንግ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ፣ የሞባይል የአየር ሰዓት የመሙላት አገልግሎትና የማስተር ካርድ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ወደፊትም ውስጣዊ አቅሙን አጠናክሮ ለተሻለ ውጤት እንደሚበቃ እምነታቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ባንኩ ስለሚሠራቸው ዋና ዋና ተግባራት አስተዋውቀዋል፡፡
በአሥረኛ ዓመቱ ማግሥት በአዲስ ዓርማ የሚንቀሳቀሰው ብርሃን ባንክ፣ ዓርማውን ይፋ አድርጓል፡፡ ተቋማዊ ገጽታውንና መለያውን ወይም ብራንዱን ከማሻሻልና ከዘመኑ ጋር ለማጣጣም በማሰብ አዲስ ሎጎ ማዘጋጀቱም ተወስቷል፡፡
ባንኩ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ መገንባት መነሳቱ ከአዳዲስ ጅምሮቹ መካከል ዓበይት የተሰኘው ዕቅዱ ሲሆን፣ ለግንባታ የሚሆን ቦታ ማግኘቱንም አስታውቋል፡፡ በስካይ ላይት ሆቴል የተከበረው የባንኩ የምሥረታ በዓል ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ ብርሃን ባንክ ከሌሎች ባንኮች አንፃር ሲገመገም በጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆንም፣ የበለጠ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉ ተግባራት በባንኩ አመራሮችና ባለአክሲዮኖች እንዲተገበሩ ጠይቀዋል፡፡
የባንኩ ኃላፊዎች ባንኩን ለማቋቋም እንዲሁም ለባንኩ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለባንኩ ባለውለታዎች ዕውቅና ከመሰጠቱ በተጨማሪ ለሁለት የበጎ አድራጎት ተቋማት አምስት ሚሊዮን ብር አበርክቷል፡፡