በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እናት ያላት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ሲያጠፋ ትቆጣለች፣ ትገስፃለች አንዱን ከአንዱም አትለይም፡፡ እናት ገበና ሸፋኝም ናት፡፡ ሲከፋንም ሆነ መፍትሔ ስንፈልግ የእናት ጉያ የመጀመርያው ምርጫ ነው፡፡
እናት የአገር ተምሳሌትም ናት፡፡ ይህንን ከግምት በመክተት ሴቶች ለአገር ግንባታ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው በማለት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህር ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሁለት ሐሳቦችን መድረክ ላይ ይዞ ቀርቧል፡፡
ሚኒስቴሩ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ‹‹ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሳይንስ›› በሚል መሪ ቃል ሁለት መርሐ ግብሮችን በማካተት የአንድ ቀን የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት የመጀመርያው መርሐ ግብር በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እየተፈጠረ የሚገኘውን ከትምህርት መቆራረጥ እስከ ሕይወት መጥፋት የደረሰ ግጭት ለመፍታት ሴት ምሁራን በምን መልኩ ማገዝ ይችላሉ? የሴት ምሁራን ዕይታና ምክረ ሐሳብስ ምንድነው? በሚለው ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
ሁለተኛው መርሐ ግብር ያጠነጠነው በሴት ምሁራን ዙሪያ ሲሆን፣ የሴት ተመራማሪዎችና የሴት ምሁራንን በአጠቃላይ ለማበረታታትና ድጋፍ ለማድረግና እነዚህ ምሁራን ለወጣት ሴቶች ተምሳሌት እንዲሆኑ ለማስቻል የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ሒሩት ወልደማርያም (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሒሩት እንደገለጹት፣ ሴቶች በተፈጥሮ ሩኅሩኅ፣ ችግር ፈቺና ለሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ለልጆች፣ ለቤተሰቦች ብሎም ለአካባቢዎች ሰላማዊ መሆን ሴቶች ወሳኝ ናቸው፡፡ ‹‹ሴት በመሆናቸው ብቻ ይኼንን ሚና መጫወት ከቻሉ ሳይንቲስት ሲሆኑ ደግሞ የበለጠ በዕውቀት፣ በክህሎትና በሥሌት መፍትሔ ማፈላለጉ ላይ ትልቅ ድርሻ ስለሚኖራቸው ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፤›› የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ሴቶች በአገር ላይ ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችሉ የሚናገሩት ሚኒስትሯ፣ ‹‹ነገር ግን በሙሉ አቅም ሚናቸውን አልተወጡም፤ ኃይልና አቅም ይዘን ለውጥ የሚመጣበትን የተለየ አካሄድ እንሄዳለንም፤›› ብለለዋል፡፡
‹‹የሴት ምሁራን ዕይታ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላም›› በሚል መወያያ ርዕስ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ ከተለያየ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ባለሙያዎች ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
ከዕንቁነሽ ሕይወት ለሕይወት ቡድን የመጡት ትዕግሥት ወንድሙ (ዶ/ር)፣ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ለሚፈጽሙት ማናቸውም ችግሮች ዕርምት በአስቸኳይ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ችግሩን የሚፈጥረው አካል እየታወቀ ዕርምጃ ሳይወሰድ ጊዜ ወስዷል፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ በጥንቃቄ ሊሠራ ይገባል፡፡
ዶ/ር ትዕግሥት ሌላው ያነሱት በየዩኒቨርሲቲዎች ስለሚገኙ ሕግና መመርያዎች ነው፡፡ ስለዚህም ሲገልጹ፣ ‹‹መመርያዎቹ ላይ ጥናት መደረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም መፍትሔ እንዲመጣ የምንፈልግ ከሆነ ችግሩ ላይ ከሥር መሠረቱ መሥራት አለብን፤›› ብለዋል፡፡
ፖለቲካን ከዩኒቨርሲቲ ማውጣት የሚለው ሌላው ያነሱት ነጥብ ነው፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ ከተቋማቱ እስካልወጣ ድረስ ግጭት ተመልሶ ተመልሶ ሊመጣ የሚችል አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሰላም ግንባታ ሌላ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው የሚሉት እኚሁ ምሁር፣ ‹‹የሰላም ግንባታ ሊሆን የሚገባው ከታች ወደ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ ወደታች ሰላምን እንገንባ ካልን የተሻለ ሰላምን ከማግኘት አኳያ ሊሳካ አይችልም፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ ጠንካራ መሪዎች በየዩኒቨርሲቲው እንደሚያስፈልጉም በአንክሮ ተናግረዋል፡፡
ከሴት ተመራማሪዎች ቡድን ሐሳባቸውን ያጋሩት አስቴር ፀጋዬ (ዶ/ር)፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎቻችን ደሴት አይደሉም›› በማለት ሐሳባቸውን ጀምረዋል፡፡ ‹‹በየዩኒቨርሲቲው ያለው ችግር በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ ያለው ችግር ነፀብራቅ ነው›› የሚሉት ዶ/ር አስቴር፣ ይህንን ችግር ለመፍታት የመምህሩ፣ የተማሪው፣ የፀጥታ አካሉ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር፣ የአካባቢ አስተዳደር እንዲሁም የአካባቢ ማኅረበሰብ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በየዩኒቨርሲቲው የሽምግልና ኮሚቴ ቢቋቋምና ተማሪው እርስ በርስ በሚጋጭበት ጊዜ ሌላ ሦስተኛ አካል መሀል ሳይገባ በሽምግልና ኮሚቴው በኩል ዕርቅ የመፈጸሙ ሁኔታ ቢከናወን መልካም እንደሆነም አሳስበዋል፡፡ ተማሪዎቹ ራሳቸው በዘርና በሃይማኖት ሳይቧደኑ ቅድመ ሥራ መሥራት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የራሳቸውን ተማሪዎች በማንሳት ክፍል ውስጥ ሲቀመጡ አማርኛ ተናጋሪ ለብቻው፣ ትግርኛ ተናጋሪ ለብቻው፣ እንዲሁም ሌሎች ሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ለየብቻቸው ተቧድነው እንደሆነና የተለያዩ የቡድን ሥራዎች በሚሰጧቸው ጊዜ እርስ በርስ ካልሆነ ተደባልቆ የመሥራት ነገር እንደማያዩ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም አንዴ ራሳቸው አደባልቀው ፕሮጀክቶችን እንዲሠሩ እንዳደረጓቸውና በዓመቱ መጨረሻ ላይ ልጆቹ በጣም ደስተኛ እንደሆኑና የቡድን ስሜቱ መጥፋቱን መረዳታቸውን አውስተዋል፡፡
ይኼ ትንሽ ሊመስል ቢችልም እያንዳንዱ መምህር እንደዚህ ጥቃቅን ከሚመስሉ ነገሮች ተነስቶ ሥራዎችን ቢሠራ ውጤቱ ትልቅ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
‹‹ልጆቹ የሚነጋገሩበትና የሚቀራረቡበት እንደ ክበብ ያሉ ማኅበራዊ ክንዋኔዎችን ማብዛት አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ሲቀራረብ ፍቅር እንደሆነ ዓይቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ሴቶች የእናትነት ባህሪ ስላላቸው ሴት መምህን ልጆቹን የማግባባት ሥራ መሥራት ይችላሉ ብለዋል፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያንም በመድረኩ አንስተዋል፡፡ በሥራ ሰዓት ማህበራዊ ገጾች ለሠራተኛውም ለተማሪውም ቢዘጉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ የፀጥታ አካላት መታወቂያ በአግባቡ እያዩ ቢያስገቡ፣ ቢያንስ ከውጭ የሚገቡትን የጥፋት ኃይሎች ቁጥር መቀነስ እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡ እንደ መፍትሔ ሐሳብ ያነሱትም የሰላም ትምህርቶችን ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ለብቻው እንደ አንድ ትምህርት መስጠትን ሲሆን፣ ይህም ትልቅ ሚና እንደሚኖው ገልጸዋል፡፡
ከሕይወት ለሕይወት ቡድን ሐሳባቸውን ያጋሩት አበባ አማረ (ዶ/ር)፣ ‹‹እንደ ወንድማማቾች አብረን መኖር አለብን፡፡ ካልሆነ ግን እንደ ሞኝ ሁላችንም እንጠፋፋለን፤›› በማለት የማርቲን ሉተር ኪንግን አባባል በማውሳት ነበር ሐሳባቸውን የጀመሩት፡፡ አገር ላይ፣ ቤተሰብ ላይ፣ ልጆች ላይ ከመሥራት በፊት ቅድሚያ ራስ ላይ መሥራት ተቀዳሚ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
‹‹ሰው ቅድሚያ ውስጣዊ ሰላም ሊኖረው ይገባል፡፡ ውስጣዊ ሰላም ከሌለው አካባቢውን ሰላም መስጠት አይችልም፤›› በማለትም፣ ቀጥሎ ልጆቹ ፣ ወንድሞቹ፣ እህቶቹ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ላይ ከሠራ መፍትሔውን እዚያው ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን በየዩኒቨርስቲዎች የተፈጠሩትን ግጭቶች በማውሳት፣ ‹‹ያለው ሁኔታ ግዴታ ቤታችንን እስኪያንኳኳ መጠበቅ የለብንም፤ በየትኛውም አቅጣጫ ያለች እናት ለሰላም መነሳት አለባት ፣እንኳን የልጆቻችንን ሬሳ ለመቀበል ቀርቶ ተንከባክበን ያሳደግነውን ፀጉራቸውን እንኳን ተቆርጠው ሲመጡ ይከፋናል፤››ብለዋል፡፡
ከተሳታፊዎችም የተለያዩ ሐሳቦች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ ወ/ሮ ዘሚ የኑስ፣ አንድን ዩኒቨርሲቲ ማስተዳደር ይከብዳል ወይ? ማነው የሚገባው? ማነው የሚወጣው? የሚለውን ማድረግስ ያቅታል ወይ? እንዴት ይኼ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ክፍት ሊሆን ቻለ? የሚሉትን ጥያቄዎች ከጠየቁ በኋላ መንግሥት እዚህ ላይ መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
‹‹ሴቶች መሪዎች ብዙ አሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም ድምፅ ይቀራል፤›› በማለት ከሴት መሪዎች የእናትነት ድምፅ፣ የቁጣ ንግግር እንዲሁም ልጆቻችን እያለቁ ነው፡፤ እዚህ ጋር መቆም አለበት! ብለው በአንክሮ መናገር እንደሚቀር አስገንዝበዋል፡፡
አስናቀች (ዶ/ር) የተባሉ ተሳታፊም፣ ከመንግሥት የምንጠብቀውን ያህል ቆንጠጥ ያለ ዕርምጃ እያገኘን አይደለም ብለዋል፡፡
አሁን እየሆነ ያለው ልጆቹ ብቻ ያደረጉት ነገር አይደለም የሚሉት እኚህ እናት፣ ትልልቅ መንግሥታዊ ድርጅቶች ገብተው የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የማያዳግም ዕርምጃ መንግሥት እንዲወስድ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የማጠቃለያ ንግግር የደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ‹‹እኔ የማምነው እያንዳንዳችን ወንድም እንሁን ሴት ነፃ ሆነን ሐሳባችንን ማቅረብ እንዳለብን ነው፡፡ መስማማት አለመስማማት፣ መቀበል አለመቀበል እንዳለ ሆኖ መደማመጥ ግን መሠረታዊ ነገር ነው፤›› ብለዋል፡፡
ልጄ ለዩኒቨርሲቲ ደረሰልኝ/ደረሰችልን ብሎ መርቆ ሰንቆ ልጁን የላከ ቤተሰብ፣ የላከች እናት አስከሬን መቀበል የለባቸውም፡፡ ይህ ነው የማንተላለፈው ድንበራችን በማለት ይኼ እንዳይሆን ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲዎቻችን በአገራችን ውስጥ የተጫወቱትን ሚና እናውቃን፣ ዩኒቨርሲቲዎች የሐሳብ ማፍለቂ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሁሉም ሰው አንድ አስተሳሰብ ይኑረው ሳይሆን ላለመግባባት መግባባት ላይ መድረስ አለበት›› እንላለን ብለዋል፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲ የሄደ አንድ ወጣት ለመማር ነው የሄደው፣ የቤተሰቡን ሕይወት ለመለወጥ የተነሳ ነው፡፡ ለመቀለድ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ሕይወት ለማጥፋት አይደለም፡፡ በዚህ የሚመጣውን መቀናቀን አለብን በማለት ሁሉም ግለሰብ እንደዚህ ዓይነት እኩይ ተግባርን የመቃወም ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ሁሉም የዚች አገር ጠባቂ ነው፣ አይደረግም ማለት መቻል አለበት የሚሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹መንግሥት የሚችለውን ያደርጋል፡፡ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ደግሞ አብረን ተባብረን የአገራችን ተረካቢ የሆኑ ወጣቶች የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩ እናደርጋን፣ እኛ ሴቶችም ይህን ካጠናከርን ትልቅ ኃይል መሆን እንችላለለን፣ ለአገራችን ሁላችንም ዘብ እንቁም፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመጡ ሴት ምሁራን ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ ይህም ለቀጣዩ ትውልድ የመንፈስ ጥንካሬ እንደሚሆንና ይኼን ፈለግ ተከትሎ ለመሄድ እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጡ ሴት ተመራማሪዎች፣ ሴት መምህራን፣ ከሴቶች የምርምር ማኅበራት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ካሉ የሴቶች የምርምር ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡