Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ30,000 ዜጎች ነፃ ሕክምና የሚያገኙበት ዓለም አቀፍ መድረክ ተዘጋጀ

30,000 ዜጎች ነፃ ሕክምና የሚያገኙበት ዓለም አቀፍ መድረክ ተዘጋጀ

ቀን:

የአዲስ አበባ የግል ጤና ተቋማት አሠሪዎች ማኅበር ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና 30,000 ዜጎች ነፃ የጤና ምርመራና የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ዓለም አቀፍ የጤና ኤክስፖና ኮንፈረንስ ‹‹ለጤናዬ እጠነቀቃለሁ›› በሚል መሪ ከኅዳር 22 እስከ ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊካሄድ ነው ተባለ፡፡

ኅዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ማኅበሩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ፕሮግራሙ የሚከናወነው በሚሊኒየም አዳራሽ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በፕሮግራሙ ከ200 የሚበልጡ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የግል ከፍተኛ ጤና ተቋማት ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡

የማኅበሩ አስተባባሪ ሙሴ ቪክቶሪዮ (ዶ/ር) የደም ግፊት፣ የስኳር፣ የኤችአይቪ፣ እንዲሁም የስፔሻሊቲ ማለትም የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራ (ስክሪኒንግ)፣ የፊዚዮቴራፒ፣ የጥርስ፣ የዓይንና የጆሮ ሕክምና አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

በተጨማሪም የልብ (ኤኮጋርዲዮግራፊክ) ምርመራና የአርቶዶፒክ ስክሪኒንግ አገልግሎት እንደሚሰጡ፣ ለዚህም ከልዩ ልዩ የግል የሕክምና ተቋማት የተውጣጡ 50 ስፔሻሊስቶች መመደባቸውን ከአስተባባሪው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤፍራታ አረጋ ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ዝግጅት ላይ በየዕለቱ 10,000 ዜጎች የጤና ምርመራና ሕክምና ያገኛሉ፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን በየክፍለ ከተሞቹ ቅስቀሳ በመካሄድ ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

50,000 ታዳሚዎች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀው ፕሮግራሙ የግል ጤና ተቋማትን በማነቃቃት ዓለም አቀፍ የሜዲካል ቱሪዝም ገበያን ለመቀላቀል መንገድ የሚከፍት፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮና ዕገዛ የሚገኝበት ይሆናል የሚል እምነት እንዳሳደረ ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በግልና በመንግሥት የጤና ተቋማት መካከልም ተቋማዊ አገልግሎት አሰጣጥ ትስስርን እንደሚፈጥር፣ ኅብረተሰቡ የትኞቹ የጤና ተቋማት ምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚሰጡ መረጃ የሚያገኝበት መድረክ እንደሚሆንም ወ/ሮ ኤፍራታ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና ማበልፀግ ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ቢሳው ‹‹በከተማው 114 የመንግሥት ጤና ተቋማት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል 102ቱ ጤና ጣቢያዎች ሲሆኑ፣ 12ቱ ደግሞ ሆስፒታሎች ናቸው፡፡ ሁሉም ጤና ተቋማት ለኅብረተሰቡ ያላቸው ተደራሽነት እጅግ ከፍ ያለ ሲሆን፣ የጤና ሽፋኑም በአብዛኛው 100 በመቶ ደርሷል ለማለት የአገልግሎትቸውን ጥራት ለመጠበቅና የተገልጋዩን እርካታ ለማሟላት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ሥራዎችም በመከናወን ላይ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በመከናወን ላይ ካሉት ሥራዎች መካከልም አዳዲስ የሕክምና ቴክኖሎጂዎችን ማስገባት፣ ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ይህን የመሰለ ጥረት እያደረገ ቢሆንም ሳይንስ በየጊዜው እያደገ በመሄዱና የተገልጋዩም ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ጥራቱን የማስጠበቁ እንቅስቃሴው በዛው መጠን ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚባ አሳስበዋል፡፡

ከመንግሥት ጤና ተቋማት ባሻገር የግል ጤና ተቋማት እየተበራከቱ መምጣት የጤናውን ዘርፍ ተደራሽነት ከፍ እንዳደረገው፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት (ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ) መርህ መሠረት ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት፡፡

ባደጉት አገሮች ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት የሚገነቡትና የሚንቀሳቀሱት በግሉ ዘርፍ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያም መንግሥት ወደዚሁ አቅጣጫ እያመራ መምጣቱ እንደሚታይ ከዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደብረወርቅ ጌታቸው፣ አዲስ አበባ ውስጥ የባህል ሕክምናን ጨምሮ 2,300 የመንግሥትና የግል ሕክምና ተቋማት እንደሚኙ ተናግረዋል፡፡

የጤና ተቋማት አወቃቀር ወጥነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ቀደም ሲል የወጡት ስታንዳርዶች የግል ጤና ተቋማትን የማይስቡ ሆነው በመገኘታቸው 34 አዳዲስ ስታንዳርዶች እንደተዘጋጁ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ዘጠኙ ስታንዳርዶች ፀድቀው ሥራላይ የዋሉ ሲሆን፣ የቀሩትን 25 ስታንዳርዶች ለማስፀደቅ የሕዝብ አስተያየት እየተጠየቀባቸው መሆኑን ነው አቶ ደብረወርቅ የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...