አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ትርፉን በ57.57 ሚሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 205.1 ሚሊዮን ብር ማድረሱንና የተጣራ ትርፉ ደግሞ 159.3 ሚሊዮን ብር እንደሆነ አስታወቀ፡፡
ባንኩ ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደገለጸው፣ በተለይ ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት በ41 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ነው፡፡ ይህ የተጣራ ትርፉ ደግሞ አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት የበለጠ እንዲሆን አስችሎታል ተብሏል፡፡ ከባንኩ አኃዛዊ መረጃ መረዳት እንደተቻለውም በ2011 የሒሳብ ዓመት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን ያስገኘው ትርፍ 207 ብር ሆኗል፡፡ በቀዳሚው ዓመት ግን አንድ አክሲዮን አስገኝቶ የነበረው 171 ብር እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በ2011 የሒሳብ ዓመት ከነበሩት በርካታ ተግዳሮቶች አንፃር ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ባይሆንም፣ በዚህ ተግዳሮት ውስጥ ውጤታማ ሥራ ስለመሠራቱ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት አመላክቷል፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው አለመረጋጋት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ውጤታማ አፈጻጸሞች አስመዝግብያለሁ በማለት በሪፖርቱ ከጠቀሳቸው ውስጥ አንዱ፣ የአስቀማጮች ቁጥርን በ54 በመቶ ማሳደጉ ነው፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 52‚579 አዲስ አስቀማጭ ደንበኞችን በመጨመር አጠቃላይ ደንበኞቹን 150‚004 ማድረስ ችሏል፡፡ ይህ በባንኩ ታሪክ በአንድ ዓመት ከ52 ሺሕ በላይ ደንበኞች ማፍራት የቻለበት ዓመት ነው፡፡
በዚህ ደረጃ ማሳደግ ችያለሁ ያለው የአስቀማጮች ቁጥርም፣ ዓመታዊ የተቀማጭ ገንዘቡን ከ34 በመቶ በላይ በማሳደግ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 3.9 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንዳስቻለው ከባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ለደንበኞች የሰጠው አጠቃላይ ብድር መጠን 2.7 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 616.8 ሚሊዮን ብር ወይም የ30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ ከሰጠው ብድር ውስጥ የውጭ ንግድ ድርሻ 47 በመቶ በመሆን ከፍተኛውን ደረጃ ይዟል፡፡ ለማምረቻ 11 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት 23 በመቶ፣ ለኮንስትራክሽን ዘጠኝ በመቶ፣ ለገቢ ንግድ አራት በመቶ፣ ለቤት ሁለት በመቶ እንዲሁም ለሌሎች ዘርፎች ሁለት በመቶ የሚሆን ድርሻ ነበራቸው፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ በደንበኞች እጅ ከሚገኘው ብድር ውስጥ 95.4 በመቶ ጤናማ ብድር መሆኑን ያሳወቀ ቢሆንም፣ የተበላሸ ብድር መጠኑ ግን 4.6 በመቶ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ ይኼ የተበላሸ ብድር መጠን ብሔራዊ ባንክ ካወጣው አምስት በመቶ መሥፈርት በታች እንደሆነ ገልጿል፡፡
ባንኩ በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት አበረታች ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን፣ ከዘርፉ በጠቅላላው 159.0 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ችሏል፡፡ ይህም አኃዝ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ36.8 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ይህ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት የተገኘው ገቢ አበረታች ቢሆንም፣ በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ግን ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረበት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይለ መለኮት ተክለ ጊዮርጊስ ተገልጿል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 5.5 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ1.3 ቢሊዮን ብር ጨምሯል፡፡ ከባንኩ ጠቅላላ ሀብት ውስጥ ለደንበኞች የተሰጠ የተጣራ ብድር 48 በመቶ፣ ጥሬ ገንዘብና በባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ 24 በመቶና ሌሎች 28 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይዘዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ካፒታልም 1.1 ቢሊዮን ብር ስለመድረሱ የሚያመላክተው ይኸው ሪፖርት፣ ባለፈው ሒሳብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 899.6 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ24 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡
ከባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው 831.3 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ17 በመቶ ዕድገት ነበረው፡፡ በተመሳሳይ የባንኩ የባለአክሲዮኖች ቁጥርም በዓመቱ የ17.4 በመቶ ዕድገት በማሳየት 11‚682 ደርሷል፡፡ ይህም ባንኩ ሕዝባዊ መሠረቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ እንደመጣ የሚያመለክት እንደሆነ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ 672.4 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ከተገኘው የገቢ መጠን ጋር ሲነፃፀር የ37 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ወቅት 68 ቅርንጫፎች አሉት፡፡