አቢሲኒያ ባንክ ከታክስ በፊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ በማግኘት የ2011 ሒሳብ ዓመት ማጠናቀቁንና በለገሃር አካባቢ ባለ 40 ወለል ሕንፃ ለመገንባት ማቀዱን ገለጸ፡፡
አቢሲኒያ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ባንኩ በ23 ዓመት ታሪኩ ውስጥ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር የቻለበት የመጀመርያው ዓመት ነው፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ ትርፋቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉት አምስት የግል ባንኮች መካከል አንዱ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በተከናወነበት ወቅት የባንኩ የዳሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሠረት ታዬ እንዳመለከቱት፣ ባንኩ በ2011 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.02 ቢሊዮን ብር ሲያተርፍ፣ ከታክስ በኋላ ደግሞ 777 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ከታክስ በፊት የተገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት ተገኝቶ ከነበረው በ 33.7 በመቶ ወይም በ258 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው የቦርዱ ሊቀመንበር ጠቅሰዋል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሰየሙትን አቶ በቃሉ ዘለቀን ለባለአክሲዮኖች በማስተዋወቅ ሪፖርታቸውን ያቀረቡት አቶ መሠረት፣ በሌሎች ክንውኖቹም ባንኩ በተለያየ መጠን ዕድገት ያስመዘገበበት የሒሳብ ዓመት መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ በተለይ የባንኩን የተቀማጭ ገንዘብ በ25 በመቶ በማሳደግ ወደ 35.15 ቢሊዮን ብር ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 6.35 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ እንዳሰባሰበም ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ለደንበኞች የሰጠውን ብር መጠን ደግሞ በ31.9 በመቶ በማሳደግ በ2011 የሒሳብ ዓመት የባንኩ የብድርና ቅድሚያ ክፍያዎች መጠን 23.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይኸም ከቀደመው ሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር 5.74 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከሰጠው ብድር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ለአገር ውስጥ ንግድ የተሰጠው ብድር ነው፡፡ ከጠቅላላ ብድር ውስጥ ለዚህ ዘርፍ የተሰተው ብድር የ52.7 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ የወጪ ንግድ ደግሞ የ18.4 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ ለግንባታ 9.2 በመቶ፣ ለአምራቾች ስምንት በመቶ፣ ለገቢ ንግድ 4.4 በመቶ፣ ለትራንስፖርት ዘርፍ ሦስት በመቶ፣ ለግብርና 1.2 በመቶና ሌሎች ዘርፎች በድምሩ 3.1 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡
ባንኩ ከቀዳሚው ዓመት አፈጻጸሞች ሲነፃፀር ቅናሽ የታየበት ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን 342.6 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አስመዝግቦት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ39.1 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ10.2 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ አቶ መሠረት ለዚህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መቀነስ እንደ ምክንያት የጠቀሱት የወጪ ንግድ ሥራ አፈጻጸም ደካማ መሆኑና ከዚህ ዘርፍ ይገኛል ተብሎ የተጠበቀው የውጭ ምንዛሪ ከዕቅድ በታች አፈጻጸም ማሳየቱ ነው፡፡ ከተሰበሰበው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ መጠን ውስጥ ከውጭ ሐዋላ አገልግሎት የተገኘው ብልጫ አሳይቷል፡፡ ይህም 53.7 በመቶ ነው፡፡ ቀሪው 31.1 በመቶ ከወጪ ንግድ የተገኘ ነው፡፡
በአጠቃላይ የባንኩ ዓመታዊ ገቢ በ2011 መጨረሻ ላይ 4.9 ቢሊዮን ብር ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ30.9 በመቶ ወይም 1.015 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል፡፡ በአንፃሩም የባንኩ ጠቅላላ ወጪ 3.26 ቢሊዮን ብር ስለመድረሱ ተመልክቷል፡፡ ይህ የወጪ መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ 756.5 ሚሊዮን ብር ወይም የ30 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ለአጠቃላይ ወጪው መጨመር በዋናነት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ማደግን ተከትሎ ለአስቀማጮች የተከፈለው ወለድ የ46.3 በመቶ ድርሻ በመያዙ ነው፡፡ ለሠራተኞች የተከፈለው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የ30.1 በመቶ፣ ለጠቅላላና አስተዳደራዊ ወጪዎች (ለቅርንጫፎች የሚከፈለውን የኪራይ ወጪን ጨምሮ) የ19 በመቶና ለተበላሹ ብድሮች መጠባበቂያ የ3.5 በመቶ የወጪ ድርሻ እንደነበራቸውም ታውቋል፡፡
በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ወደ 4.95 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለት የቻለ ሲሆን፣ ይኼም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው አኃዝ ጋር ሲነፃፀር የ0.71 ቢሊዮን ብር ወይም የ17 በመቶ ዕድገት አለው፡፡
እንደዚሁም የባንኩ የተከፈለ ካፒታል መጠን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው ከ2.56 ቢሊዮን ብር ወደ 2.81 ቢሊዮን ብር በማደጉ የ9.7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በ2011 ሒሳብ ዓመት በዘርፉ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት እጥረት ጎልቶ የታየ ቢሆንም፣ ባንኩ በዚህ ረገድ እነዚህን አስቸጋሪ ጊዜያት ያለምንም የጥሬ ገንዘብ እጥረት ተቆጣጣሪው አካል ያስቀመጠውን መሥፈርት በማሟላት ለማለፍ መቻሉ ተገልጿል፡፡
የባንኩ ካፒታል ከአደጋ ሊጋለጥ ከሚችል ጥቅል ሀብት ጋር ያለው ጥመርታ 13.9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህም ተቆጣጣሪው አካል ካስቀመጠው የስምንት በመቶ ዝቅተኛ መሥፈርት ጋር ሲነፃፀር የ5.9 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ በመሆኑም ባንኩ በዚህ ረገድ በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ ጥሩ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል የቦርድ ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል፡፡
ባንኩ ከሚያካሂዳቸው ግንባታዎች መካከል ራስ ቅርንጫፍ ሕንፃ የሚል መጠሪያ ያለውና አሁን ባንኩ በዋና መሥሪያ ቤትነት የሚጠቀምበት ሕንፃ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡ ሕንፃው በካሬ ሜትርሥሌት 1,357 እና 1,596 ስፋት ያላቸው ሁለት የንብረት ይዞታ ማረጋገጫዎች ሲኖሩት፣ ከምድር ቤት እስከ ሦስተኛ ፎቅ ያሉት የሕንፃዎቹ ክፍሎች ለባንኩ በዋና መሥሪያ ቤትነት፣ ለራስ ቅርንጫፍና ለናይል ኢንሹራንስ የኪራይ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ባንኩ የሕንፃውን ግንባታ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ አማካሪ በመቅጠር ቻይና ጃንግሱ ኢንተርናሽናል ኢ.ቲ.ሲ.ሲ. ከተባለ ሥራ ተቋራጭ ጋር ውል ተፈራርሞ ግንባታውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የግንባታ ሥራውም በ17 ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ ተይዞለታል፡፡ ከዚህ ይዞታ ጋር አዋሳኝ የሆኑና ከስታዲዮም በሚመጣው ዋና መንገድ ዳር የነበሩ ስፋታቸው 985 ካሬ ሜትር የሆኑ ሦስት የግለሰብ ይዞታዎችን በግዥ በማግኘቱ፣ እንዲሁም በተጨማሪም ከሕንፃው አጎራባች የሚገኙ የመንግሥት ይዞታዎች ለማስፋፊያነት ጠይቆ አዲስ አበባ አስተዳደር ከሕንፃው ፊት ለፊት የሚገኘውን የኪራይ ቤቶች ሕንፃን ጨምሮ በአጠቃላይ 5,056 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ይዞታ ለባንኩ እንዲሰጠው ወስኖለታል ተብሏል፡፡ እነዚህን ይዞታዎቹን ለመረከብ ቅድመ ሁኔታዎችን እያከናወነ በመሆኑ፣ በዚሁ ቦታ ላይ ተጨማሪ ሕንፃ ለመሥራት ማቀዱን የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ይህንንም ግንባታ ለመጀመር አሁን የባንኩን ግንባታ እያካሄደ ያለው የቻይናው ኩባንያ የዲዛይን ሥራውን እንዲሠራ በማድረግ የመጀመርያ አማራጭ ዲዛይን ተሠርቶ (4B+G+40) እንደቀረበ ተገልጿል፡፡ ይህ ዲዛይን ታይቶም በቦታው ላይ ያለውን ሕንፃ ለማሳረፍ አቅዶ እየሠራ ነው ተብሏል፡፡
ከዚህም ሌላ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ከአሥር በላይ ሕንፃዎችን በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ ሲሆን፣ ግንባታቸው በተጠናቀቁት ላይ አገልግሎት መጀመሩንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ የካርድና ባንኪንግ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በ56.3 በማሳደግ 131,661 ማድረስ መቻሉንና የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎችን ደግሞ በ65.4 በመቶ በማሳደግ 133,105 ማድረስ መቻሉም ተገልጿል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት 51 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈት፣ የቅርጫፎቹን ቁጥር 337 አድርሷል፡፡ በቀጣዩ ዓመት 121 ቅርንጫፎች በመክፈት 458 ለማድረስ አቅዶ እየሠራ ነው፡፡