Wednesday, April 17, 2024

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ከዝግጅት እስከ ውጤት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ የተለያዩ መመሰቃቀሎች እየተስተዋሉበት ቀጥሏል፡፡ ይህ ደግሞ አለመረጋጋቶችንና ግጭቶችንና እያወሳሰበ ነው፡፡ ምንም እንኳ አገሪቱን እየናጣት ያለው የሰላም ዕጦት ቀደም ብሎ የመንግሥት ለውጥ ከመምጣቱ በፊት የጀመረ ቢሆንም፣ እስካሁን ከመሻሻል ይልቅ ወደ ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች እየወሰዳት ነው፡፡

በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ቀደም ባሉት ጊዜያት የተሻለ ተስፋ ይመጣል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ ነገሮች በተቃራኒው መንገድ መጓዝ በመጀመራቸው አገሪቱን ወደ ተወሳሰቡ ችግሮች የሚገፉት ችግሮች እየበዙ ነው፡፡

በተለይ በተለያዩ ክልሎች የሚከሰቱ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ የሥርዓተ አልበኝነት መስፋፋትን ጨምሮ የኮንትሮባንድና የሕገወጥ መሣሪያ ዝውውሮች የአገሪቱንም ሆነ የሕዝቦቿን ደኅንነት ሥጋት ላይ መጣላቸው ይጠቀሳል፡፡

በሌላ በኩልም መንግሥት ሕግ ማስከበር ላይ ከመጠን ያለፈ ትዕግሥት ማሳየቱ፣ በተደጋጋሚ ትችት ሲቀርብበት ይሰማል፡፡ ተደጋጋሚ የግጭት ክስተቶች፣ ሥርዓተ አልበኝነት፣ ሕግ የማስከበር ችግሮች አገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈላቸውን በመቀጠላቸው፣ መተግበር የሚገባውን አገራዊ ጉዳዮችን በይደር ለማለፍ ያስገደዱ ሁነቶች አጋጥመዋል፡፡

ለአብነትም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የምርጫ ዘመኖቻቸው ቢያልቅም ምርጫዎችን ማካሄድ አልተቻለም፡፡ ከአንድም ሁለት ጊዜ ነባር አስተዳደሮች ለተጨማሪ ዓመታት እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይም አገራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንዲሁ ለሁለት ጊዜ ተራዝሞ በአሥር ዓመቱ መካሄድ የነበረበት ቆጠራ አልተከናወነም፡፡

በ2011 ዓ.ም. እና በ2012 ዓ.ም. መከናወን የሚገባቸው ትልልቅ ጉዳዮች  በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች በተፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ መከናወን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በቀጣይ ወራትም እነዚህ ተግባራት የመከናወናቸው ጉዳይ እያነጋገረ ይገኛል፡፡ ዘንድሮ እንደሚከናወኑ ይጠበቁ ከነበሩት ጉዳዮችና አሳሳቢ ሆነው ከቆዩት ውስጥ፣ በደቡብ ክልል ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የሲዳማ ክልልነት ጥያቄን ዕልባት ለመስጠት የተካሄደው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ አንዱ ነበር፡፡

ሕዝበ ውሳኔው አገሪቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ካሳለፈቻቸው ችግሮች አንፃር በሰላም እንዴት ሊጠናቀቅ ይችላል በሚል፣ የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ቀድሞ ከተፈራው በተቃራኒ ረቡዕ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. የሕዝበ ውሳኔው ድምፅ አሰጣጥ በሐዋሳ ከተማም ሆነ በዞኑ አጠቃላይ ወረዳዎች ይህ ነው የሚባል የፀጥታ ችግር ሳያጋጥም መጠናቀቁን፣ የምርጫ ቦርድም ሆነ የክልልና የፌዴራል መንግሥታት አስታውቀዋል፡፡

ምንም እንኳን ክልሉ በጊዜያዊ የአስቸኳይ አዋጅ ምክንያት የፀጥታ ሥራው በኮማንድ ፖስት ሥር በመሆኑ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ ቢጠቅስም፣ ለአብዛኞቹ የክልሉ ነዋሪዎችም ሆነ ለአገሪቱ አብዛኛው ሕዝብ ዕፎይታን የሰጠ እንደነበር ተስተውሏል፡፡

ምርጫ ቦርድና ዝግጅቱ  

የሕዝበ ወሳኔው አፈጻጸም ተዓማኒ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ለማድረግ ቦርዱ እስከ ሕዝብ ውሳኔው ድምፅ መስጫ ዕለት ድረስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ‹‹ቦርዱ የሕዝበ ውሳኔውን ጥያቄ የማስፈጸም ኃላፊነቱን መወጣት የጀመረው ሒደቱ  ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ተዓማኒ እንዲሆን እንዲሁም በሲዳማ ዞንና በሐዋሳ ከተማ  የሚኖሩ ዜጎች ያለ አድልኦ ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል የሲዳማ ሕዝብ ውሳኔ አፈጻጸም መመርያ በማፅደቅ ነው፤›› ሲል ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡  

ከዚህ በተጓዳኝ የሕዝብ ወሳኔውን የአፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው የክልሉና የዞን መስተዳደር አካላት እንዲደርስና ለሕዝብም ይፋ እንዲሆን መደረጉን፣ ቦርዱ በሕዝብ ውሳኔው ዕቅድ አፈጻጸም ከክልሉና ከዞኑ መስተዳደር አካላት ጋር በርካታ ውይይትና ስምምነቶችን ማድረጉን አውስቷል፡፡ በዚህም መሠረት ለሕዝብ ውሳኔ ማስፈጸሚያ የሚያስፈለገውን በጀት በክልሉ መንግሥት እንዲፈቀድ እንዳደረገም አስረድቷል።

ሕዝብ ውሳኔውን በሰላማዊ ሁኔታ ለማስፈጸም አስፈላጊ ሁኔታዎችን የክልሉ ምክር ቤት አስቀድሞ እንዲፈጽም በጠየቀው መሠረት፣ በሕዝበ ውሳኔ የሲዳማ ዞን በክልልነት እንዲደራጅ የሚወሰን ከሆነ በዞኑ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች መብት ጥበቃን፣ አዲስ በሚፈጠረውናነባሩ ክልል መካከል የሚኖረውን የሀብት ክፍፍል የሚወሰንበት አስተዳደርና  የሕግ ማዕቀፍ አውጥቶ ማቅረቡን ገልጿል፡፡  

የቦርዱ ኃላፊዎች እንደገለጹት በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት የቦርዱ ባለሙያዎች፣ የመስክ ጥናት አካሂደው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን መረጃ አደራጅተዋል፡፡ ከቦርዱ በተገኘው መረጃ ለሕዝበ ውሳኔው ማስፈጸሚያ 1,692 ምርጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን፣ ከድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ በኋላ  ተጨማሪ 169 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተደራጅተዋል። የሕዝብ ወሳኔው አፈፃፀም ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲያስችል የክልሉ፣ የዞኑ፣ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ እንዲሁም የፌደራል የፀጥታ ተቋማትናአስተዳደር ተቋማት ለሕዝበ ውሳኔው ፀጥታ ዕቅድ አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡ የዕቅዱንም አፈጻጸም ቦርዱ በጋራ ሲከታተል መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡  

ቦርዱ እንደገለጸው ከቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት እስከ ድኅረ ሕዝበ ውሳኔ በነበረው የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታ፣ በዚህ ዕቅድ መሠረት በጋራ ኮሚቴ በየጊዜው እየታየ ሰላማዊ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ተችሏል።

ሕዝበ ውሳኔውን በገለልተኝነትና በሕግ መሠረት የሚያስፈጽሙ 6,843 አስፈጻሚዎችን ከአዲስ አበባ ከተማናኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በመመልመል በዞኑ ያሰማራ ሲሆን፣ ሁሉም አስፈጻሚዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዴት እንደሚያስፈጽሙ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሥልጠናውም ቀድመው የአሠልጣኞች ሥልጠና በወሰዱ 20 አሠልጣኞች አምስት ቀናት የተከናወነ መሆኑን፣ ሁሉም አስፈጻሚዎች የታተመ የማስፈጸሚያ ማንዋል እንዲኖራቸው መደረጉን አመልክቷል፡፡   

የመራጮች ምዝገባ በዞኑና በሐዋሳ ከተማ መስተዳድር ለሚኖሩ ማንኛቸውም ሕጋዊ መሥፈርቱን ለሚያሟሉ ዜጎች ክፍት ሆኖ ከጥቅምት 27 እስከ ኅዳር 6 ቀን 2012 .ም. ድረስ ምዝገባው ተካሂዶ 2,280,147 ድምፅ ሰጪዎች መመዝገባቸው ተመልክቷል፡፡

ድምፅ ሰጪዎችሕዝበ ውሳኔው ድምፃቸውን ለመስጠት እንዲመዘገቡ ለመቀስቀስ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተለያዩ የምዝገባ መሥፈርቶችን የሚገልጹ እንዲሁም ስለድምፅ አሰጣጡ የሚያብራሩ መልዕክቶች መተላለፋቸው፣ በድምፅ ሰጪዎች ምዝገባና ድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ የዜጎች መብት እንዳይገደብና የሒደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸው፣ ከእነዚህም መካከል የመጀመርያው የቦርዱ አመራር አባላት በሐዋሳ፣ በይርጋ ዓለም፣ በወንዶ ገነትና በሌሎች ሥፍራዎች፣ በመዘዋወር የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባና የድምፅ አሰጣጥ ሒደት ክትትል በማድረግ የታዩ ጉድለቶችና የአሠራር ዝንፈቶች እንዲስተካከሉ የተደረጉ መሆኑን፣ በተጨማሪም ዜጎች በድምፅ ሰጪዎች ምዝገባና በድምፅ መስጠት ሒደቱ የታዘቧቸውን ግድፈቶች በቀጥታ ለቦርዱ ለማሳወቅ እንዲችሉ የቀጥታ የስልክ መስመሮች ተዘጋጅተው ለመገናኛ ብዙኃንና ማኅበራዊ ሚዲያ ይፋ መደረጉ፣ በደረሱት ጥቆማዎችም መሠረት የተለያዩ ማስተካከያ ዕርምጃዎች እንዲሁም መረጃዎች ሲሰጡ መቆየታቸው ተወስቷል፡፡

ማስተካከያዎች

በቦርዱ አባላት በተደረጉ ጉብኝቶችና ቀደም ብሎ ከዞኑና ከክልል መስተዳድር ተቋማት ጋር በተደረጉ ተከታታይ ግንኙነቶች በሕዝበ ውሳኔው ሒደት በርካታ ማስተካከያዎች የተደረጉ መሆኑን፣ ከእነዚህም ውስጥ የአካባቢ ሚሊሻ አባላት በምርጫ ጣቢያዎች ፀጥታ አጠባበቅ  ምንም ዓይነት ሚና እንዳይኖራቸው መደረጉንና በአፈጻጸም  ወቅት ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የፈጸሙ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

በሕዝበ ውሳኔው መራጮች ምዝገባና ድምፅ መስጠት ሒደት ሁለቱንም አማራጮች የሚወክሉ ወኪሎች እንዲገኙ ጥረት መደረጉን፣ በተጨማሪም የተጓደሉ የሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በፍጥነት እንዲሟሉ እንደተደረገ ቦርዱ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

የሕዝበ ውሳኔውን ሒደት ሰላማዊ፣ ፍትሐዊነትና ግልጽነትን ለማረጋገጥና ለወደፊት መሻሻል ላለባቸው አሠራሮች ትምህርት ለመውሰድ፣ 128 የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎችና 74 የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያ ጋዜጠኞች ሒደቱን እንዲታዘቡና እንዲዘግቡ የሚያስችል ዕውቅና መስጠቱ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመነጋገር የኮሚሽኑ 20 ታዛቢዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ መደረጉም ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ፈቃድ የተሰጣቸው የአሜሪካ መንግሥት ወኪሎችና ዲፕሎማቶች ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ አስፈላጊው ድጋፍ እንደተደረገም ተጠቁሟል፡፡

የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት እስከ ድምፅ መስጫው ቀን ባሉት ጥቂት ቀናት ቦርዱ የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶችን ያሰራጨ መሆኑ፣ በዚህም ሒደት 3,000 የድምፅ መስጫ ሳጥኖችና ከ2.5 ሚሊዮን በላይ (መጠባበቂያን ጨምሮ) የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ ቅጾችና ቁሳቁሶች ሥርጭት መከናወኑ ተብራርቷል፡፡

በሕዝበ ውሳኔው ሒደት ፀጥታና ደኅንነትን አስመልክቶ ቦርዱ ሒደቱን በሚመራበት ወቅት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መረጃ በመሰብሰብ፣ በሐዋሳ ከተማ እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የመስክ ጉብኝት ማድረጉን፣ ከአስተዳደር ወሰን ጋር በተያያዘና ቀድሞ ግጭት በነበረባቸው የተወሰኑ ቀበሌዎች ከማኅበረሰብ ክፍሎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በማዳመጥ የቦርድ አመራር አባላት በቦታው በመገኘት የመስክ ቅኝቶችን አድርገው ከቀበሌ አስተዳደሮች ጋርም ውይይት ማድረጋቸው፣ ከውይይቱም በተጨማሪ የሲዳማ ዞንና የደቡብ ክልል የፀጥታ አካላት፣ የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትን ያካተተ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ የሚያይ መድረክ በማቋቋም ሒደቱ ሰላማዊ እንዲሆን መደረጉም በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡  

ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. የተከናወነው የድምፅ መስጠት ሒደት ሰላማዊና ጉልህ የሎጂስቲክስ ችግር ያልታያበት መሆኑን፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሠልፎች ከመኖራቸው በስተቀር በታቀደለት ሁኔታ ተጠናቋልም ሲል ቦርዱ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት በአጠቃላይ ከተመዘገቡ 2,280,147 መራጮች 2,277,063 መራጮች ድምፃቸውን መስጠታቸውን፣ ይህም የምርጫ ቀን የድምፅ መስጠት ተሳትፎ (Voter Turnout) 99.86 በመቶ መሆኑን ያሳያል ብሏል፡፡ ሲዳማ በነባሩ ክልል ውስጥ እንዲደራጅ ጎጆ ምልክትን የመረጡ ሰዎች ብዛት 33,463 ሲሆን፣ የሲዳማ በክልልነት መደራጀትን ሻፌታን የመረጡ ብዛት ደግሞ 2,225,249 እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ በውጤቱም ሻፌታ የመረጡ 98.51 በመቶ ሲሆኑ፣ ጎጆን የመረጡ 1.48 በመቶ መሆናቸውን በሒደቱ የዋጋ አልባ ድምፅ ቁጥር 18,351 (0.000002 በመቶ) እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/2/ እና /3/ ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱን ክልል የመቋቋም መብት አለው በማለት በተደነገገው መሠረት፣ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔሕጋዊናሰላማዊ መንገድ ተፈጽሟል፡፡ የዞኑ ነዋሪዎች በነፃ ፈቃዳቸው በሰጡት ውሳኔ መሠረት ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምፅም በዚህ ውሳኔ አግኝቷል፡፡  

በውጤቱ መሠረትም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/3/ ላይ እንደተጠቀሰው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤትና በሲዳማ ዞን አስተዳደር የሕዝቡን ድምፅ ባከበረ፣ ሰላማዊና ግልጽ በሆነ፣ እንዲሁምሽግግሩን ጊዜን በጠበቀ ሁኔታ የሥልጣን ርክክቡን በአግባቡ አከናውነው ይህንንሕዝበ ውሳኔ ውጤት እንደሚያስፈጽሙ ቦርዱ የፀና እምነት እንዳለው አስታውቋል፡፡

ተግዳሮቶች

ሕዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ሰላማዊና ሕጋዊ መሆኑ በዚህ ሒደት የተገኘ በጎ ውጤት መሆኑን፣ ለዝግጅት ከነበረው አጭር ጊዜም አንፃር ቦርዱ አፈጻጸሙ የተሳካ መሆኑን ያምናል፡፡ የአፈጻጸም ሒደቱ ጠቃሚ ትምህርት የተገኘበትመሆኑን ያህል ተግዳሮቶች የነበሩበት በመሆኑ፣ ለቀጣይ ትምህርት ይሆኑ ዘንድ ያላቸውን ጉዳዮች ቦርዱ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣ (የአነስተኛ ቡድኖች መብት ጥበቃ፣ የሀብት ክፍፍል) በቦርዱ የቀረበው ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት የተሰጠው ምላሽ መዘግየት፣ የሕዝበ ውሳኔው ቅስቀሳ ሒደት የአንድ ወገን አማራጭ ብቻ የቀረበበት መሆኑና የሕዝበ ውሳኔውን ሒደት እንዲታዘቡ የክልሉ መንግሥት ወኪሎች እንዲመድብ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም አለመመደቡ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን ለመወሰን የሚያስፈልገው የሕዝብ ቁጥር የተሟላ መረጃ አለመኖር፣ በተወሰኑ የሐዋሳ ከተማ የገጠር አካባቢዎች ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የማይመለከታቸው ሰዎች መገኘት፣ በድምፅ ሰጪዎች ላይ በአንዳንድ ጣቢያዎች ተፅዕኖ የማሳደር ሁኔታ መታየት፣ በአንዳንድ ቦታዎች በድምፅ ሰጪዎች ብዛት ምክንያት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች መጨናነቅ መከሰቱ፣ በሕዝበ ውሳኔው ውጤት አገላለጽ ላይ ከሐዋሳ ከተማና ከዞኑ መስተዳድር ተቋማት ኃላፊዎች በቦርዱ ይፋዊ መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት አስቀድሞ የመገመት (Projection) እና የመግለጽ ችግር መታየቱ፣ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ውስጥ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

እንዱሁም በአንዳንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በሕግ የተቀመጠን የምርጫ ጣቢያ መክፈቻና መዝጊያ ሰዓት አለመጠበቅ እንደ ዋና ተግዳሮት የሚጠቀስ ሲሆን፣  የክልሉ የፀጥታ ተቋማት፣ የደቡብ ዕዝ (የአገር መከላከያ ሠራዊት) የሕዝበ ውሳኔ ቁሳቁስማጓጓዝ፣ የአካባቢ ፀጥታና ደኅንነትን በመጠበቅ፣ የአስፈጻሚዎች ሥምሪትን፣ እንዲሁም ድምፅ የተሰጠባቸውን ሰነዶችን ጥበቃ በማድረግ እጅግ የሚመሠገን ድጋፍ ማድረጋቸውና በሕዝበ ውሳኔው ሒደት ከፍተኛ ቅንጅት መኖሩ እንደ ትልቅ ስኬት የሚነሳ ነው ሲል ቦርዱ አስታውቋል፡፡

የታዛቢዎች ዕይታ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሒደት በሰላም መጠናቀቁ የሚያስመሠግን መሆኑን ቢገልጽም፣ ያስተዋላቸውንም ችግሮች አመልክቷል፡፡ በኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሚመራው የምርጫ ታዛቢ ቡድን ሕዝበ ውሳኔውን ሒደት መከታተሉ ተገልጿል።

የታዛቢ ቡድኑ ባወጣው ሪፖርት እንደገለጸው፣ አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ አለመረጋጋት አንፃርና በተጣበበ ጊዜ ገደብ ውስጥ የሕዝበ ውሳኔው ሒደት በሰላም መጠናቀቁን አድንቋል። በሪፖርቱ እንደተገለጸው፣ በሲዳማ ዞን በሚገኙ በአምስት የከተማ አስተዳደርና በአሥራ አምስት ወረዳዎች የድምፅ አሰጣጡን ሒደት መታዘብ ተችሏል ብሏል። በምርጫ ወቅትም የሲዳማ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደርን የሚፈቅድ የሻፌታ ምልክት በስፋት ለመራጮች ገለጻ ሲደረግ  እንደነበር ጠቁሟል።

ሲዳማ ዞን ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር መቆየትን የሚደግፈው ምልክት ጎጆ ደግሞ ምንም ጫና ባይደረግበትም፣ በምርጫ ወቅት ገለጻ ለመስጠት በመጠኑ ፍርኃት እንደነበር በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ለምርጫ መመዝገቡን የጠቆመው ቡድኑ በተለይ የመሰብሰብ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብቶች መከበራቸውን ገልጿል።

ይሁን እንጂ በምርጫው አሰጣጥ ሒደት በአንዳንድ የምርጫ አካባቢዎች የተወሰኑ ክፍተቶች እንደነበሩ ሳይጠቅስ አላለፈምሪፖርቱ። የተዘጋጁት የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር ከመራጩ ቁጥር ጋር አለመጣጣም፣ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሥራቸውን በትክክል አለመወጣትና የምርጫ ታዛቢዎች  በትክክል በቦታው አለመገኘት ችግሮች መታየታቸው ተጠቁሟል።

እንዲሁም ከምርጫው ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች በሥፍራው መገኘት፣ ሚስጥር አጠባበቅ አለመከበር፣ በድምፅ አሰጣጡ ላይ በቂ ግንዛቤ የሚሰጥ የሰው ኃይል አለመሟላትና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በአንዳንድ ቦታዎች አለመገኘት መታየቱን ኮሚሽኑ  ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በአጠቃላይ የተፈራው የፀጥታ ሁኔታ እንደታሰበው ሳይሆን በሰላም ተጠናቋል፡፡ ክልል የማደራጀት ሥራዎችና የድርድር ጉዳዮች ይጠበቃሉ፡፡ አገሪቱን ከሚፈታተኑ ቀጣይ ጉዳዮች ደግሞ በግንቦት ወር የሚጠበቀው ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ነው፡፡ የሕዝብና የቤት ቆጠራውም ጉዳይ እንዲሁ፡፡ እነዚህስ ቢዘገዩም በሰላም ይካሄዱ ይሆን? ሌላ ፈተናዎች እንደሚሆኑ ይታሰባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -