Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየፌዴራል ተቋማት በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ እንዲቀርብባቸው የሚያስችል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ...

የፌዴራል ተቋማት በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ እንዲቀርብባቸው የሚያስችል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ ለፓርላማ ቀረበ

ቀን:

የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችና ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ የሆኑ የከተማ አስተዳደሮች በሕግ ከተሰጣቸው ሥልጣን ውጪ በሚያወጧቸው የአስተዳደር መመርያዎችና ውሳኔዎች ቅር የተሰኘ ተገልጋይም ሆነ ማንኛውም ሰው፣ ተቋማቱን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመክሰስ የአስተዳደር መመርያውንም ሆነ በዚህ መሠረት የሰጡትን ውሳኔ ማስከለስ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

ማክሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅና የረቂቁ አስፈላጊነትና ይዘቶችን የሚያብራራው አባሪ ሰነድ፣ እስካሁን ባለው አሠራር ፌዴራል መንግሥት የአስተዳደር ተቋማት በሚያወጧቸው አስተዳደር መመርያዎችና ውሳኔዎች ቅር የተሰኙ ዜጎች መፍትሔ የሚያገኙበት አሠራር ባለመኖሩ፣ በተቋማት የዘፈቀደ አሠራር ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንዲሰፍን ምክንያት መሆኑን ያመለክታል፡፡

በመሆኑም የዜጎች መብቶችና ጥቅሞች በፌዴራል መንግሥት የአስተዳደር ተቋማት ያላግባብ እንዳይሸራረፉ የአስተዳደር ተቋማት መመርያ የማውጣት የውክልና ሥልጣን በሕጋዊ ሥነ ሥርዓት እንዲመራ፣ እንዲሁም ይህ ሥልጣንና ተግባራቸው በፍርድ ቤት የክለሳ ሥነ ሥርዓት ቁጥጥር እንዲደረግበት ማድረግ የረቂቁ መሠረታዊ ዓላማ መሆኑ የቀረበው ማብራሪያ ሰነድ ያስገነዝባል፡፡

- Advertisement -

ችግሩንም ለመቅረፍ የፌዴራል መንግሥት የአስተዳደር ተቋማት በተቋቋሙበት አዋጅ በተሰጣቸው ማስፈጸሚያ መመርያ የማውጣት ውክልና መሠረት መመርያዎችን በሚያወጡበት ጊዜ ሊከተሏቸው ስለሚገቡ የሥነ ሥርዓት መርሆዎች፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ውሳኔዎች የሚሰጡበትን የሥነ ሥርዓት ሒደትና ሊከተሉ ስለሚገባቸው መርሆዎች ዝርዝር ድንጋጌዎችን አካቶ ቀርቧል፡፡

በዚህም መሠረት የአስተዳደር ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን መመርያ የማውጣት ውክልና ተግባራዊ ሲያደርጉ፣ ባለድርሻ አካላትንና ተገልጋዮችን በግልጽ ማሳተፍ እንደሚገባቸው ግዴታ ይጥላል፡፡ በተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ላይ አስተያየት ለመሰብሰብና የውይይት ማካሄጃ በቂ ጊዜ መስጠት እንዳለባቸው፣ ጊዜው ሳይጠናቀቅም መመርያውን ማፅደቅ እንደማይችሉ በአስገዳጅ መሥፈርትነት ተካቷል፡፡

ከባለድርሻ አካላትና ተገልጋዮች የተሰበሰቡ አስተያየቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መመርያው ሊወጣ እንደሚገባ፣ የተሰበሰቡትን አስተያየቶች በመመርያው የማያካትት ከሆነም የዚህን ምክንያት በጽሑፍ መግለጽ እንዳለበትም በአስገዳጅነት ተቀምጧል፡፡

የሚዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ከመፅደቁ በፊትም የሕጋዊነት ጉዳዮችን ለማጣራት ሲባል ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መላክ እንደሚኖርበት፣ ዓቃቤ ሕግ በ15 ቀናት ውስጥ ያለውን አስተያየት አካቶ መመለስ እንደሚኖርበት፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ካልመለሰ ግን ተቋሙ መመርያውን ማፅደቅ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

መመርያው ከፀደቀ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተልኮ መመዝገብና በዓቃቤ ሕግ ድረ ገጽ ላይ እንዲጫንም አስገዳጅ ሆኖ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ መመርያው ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረውም በዓቃቤ ሕግ ከተመዘገበበትና በተቋማቱ ድረ ገጽ ከተጫነበት ቀን አንስቶ እንደሚሆንም ያመለክታል፡፡ በረቂቅ ሕጉ የተቀመጡትን የመመርያ አወጣጥ ድንጋጌዎች ሳይከተል ፀድቆ ሥራ ላይ በዋለ መመርያ፣ እንዲሁም መመርያው ከአስተዳደር ተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ ከሆነ ወይም በማናቸውም መንገድ ሕግን የሚጥስ ሆኖ ሲገኝ፣ ማንኛውም ሰው አቤቱታውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በማቅረብ መመርያው እንዲከለስ የማድረግ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡

 ከዚህ በተጨማሪም የአስተዳደር ተቋማት በሚሰጧቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ቅር የተሰኙ ተገልጋዮች ቅሬታቸውን አቅርበው መፍትሔ ማግኘት እንዲችሉ ተቋማት ራሱን የቻለ ቅሬታ ሰሚ ክፍል ማደራጀት እንደሚገባቸውና የሚቀርቡ ቅሬታዎች የሚስተናገዱበትንም ሥነ ሥርዓት ረቂቁ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

ቅሬታውን ለተቋሙ አስገብቶ በተቀመጠው ሥነ ሥርዓት መሠረት መፍትሔ ያላገኘ ተገልጋይ፣ አቤቱታውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችል በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

አስተዳደራዊ መመርያዎችንና ውሳኔዎችን በተመለከተ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የመመልከት ሥልጣንም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብቻ እንደሚሆንና ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔም ይግባኝ የማይኖረው የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሆንና ነገር ግን የሕግ ስህተት በሚኖርበት ጊዜ ብቻ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርብ ይደነግጋል፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚኖረው ሥልጣን አቤቱታውን መርምሮ የመሻር ወይም እንዲከለስ ውሳኔ መስጠት እንጂ፣ ክለሳውን ራሱ ማከናወን እንደማይችል፣ ይህ የሆነበት ምክንያትም ፍርድ ቤቱ ሕግ ከመተርጎም ባለፈ የሥራ አስፈጻሚው ሥልጣን በሆነ የአስተዳደር ሥራ ውስጥ እንዳይገባ መሆኑን ማብራሪያ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

 ከአስተዳደር መመርያ ወይም ውሳኔ ጋር በተገናኘ ጉዳት የደረሰበት ሰው አቤቱታውን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርቦ ፍትሕ ከማግኘት በተጨማሪ፣ በዚህ ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት በተመለከተ መመርያውን ወይም ውሳኔውን የሰጠውን ተቋም አግባብ ባለው ሕግ መሠረት በመክሰስ ካሳ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብት እንደሚኖረውም በረቂቁ ተካቷል፡፡

 በረቂቁ መሠረት የፌዴራል አስተዳደር ተቋም ማለት በፌዴራል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካል ሥር የተደራጁ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ የሆኑ የከተማ አስተዳደሮችን የሚያካትት ሲሆን፣ መደበኛ ሥራቸው ሕግ ማስከበር የሆኑት ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ የመከላከያና ደኅንነት ተቋማትን አያካትትም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም እነዚህ ተቋማት እንደ አስተዳደር ተቋም ተቆጥረው ባለመቋቋማቸው መሆኑን አባሪ ሰነዱ የሚያስረዳ ሲሆን፣ የተገለጹት ተቋማት መመርያ ሲያወጡና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ሲወስኑ በረቂቁ በተመለከቱት ሥነ ሥርዓቶች እንደሚገዙ ያመለክታል፡፡

ረቂቁ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...