Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል ባንኮች ለ27 በመቶ ቦንድ ግዥ ከ116 ቢሊዮን ብር በላይ አውጥተዋል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግል ባንኮች ከሚሰጡት ከእያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶ በማስላት ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያስገድዳቸው መመርያ መሻሩን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡ የግል ባንኮች ከ116 ቢሊዮን ብር በላይ ለቦንድ ግዥ ማዋላቸው ታውቋል፡፡

ከስምንት ዓመታት በላይ በአስገዳጅነት ሥራ ላይ የቆየው ይህ መመርያ እንዲነሳ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብበት ቆይቶ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማንሳቱን ያስታወቀው ሐሙስ ኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡

በዚህ መመርያ መሠረት 16 የግል ባንኮች ባለፉት ሰባት ዓመታት በጥቅሉ ለቦንድ ግዥው ያዋሉት የገንዘብ መጠን ከ116 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ የመክፈያ ጊዜ ደርሶ ለባንኮች የተመለሰው ከ30 ቢሊዮን ብር ያልበለጠ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባንኮች ለቦንድ ግዥው የሚያውሉት ገንዘብም ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ ከሚከፍሉት ወለድ ያነሰ ወለድ ይታሰብበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በየዓመቱ ለቦንድ ግዥው የሚያውሉት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በሦስት በመቶ፣ በቅርቡ ደግሞ አምስት በመቶ የወለድ መጠን ታሳቢ ተደርጎለት የቦንዱን ገዥ ከፈጸሙ ከአምስት ዓመት በኋላ ይመለስላቸው የነበረ በመሆኑ፣ በባንኮቹ የማበደር አቅም ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድር እንደነበር ሲነገር ቆይቷል፡፡

መንግሥት ይህንን መመርያ በማንሳቱ እጅግ ሊመሠገን ይገባል ያሉ አንድ የግል የባንክ ኃላፊ፣ ቀድሞም የግል ባንኮችን ለማዳከም በወቅቱ በነበሩ አመራሮች የተፈጸመ ድርጊት አድርገው እንደሚወስዱት ይናገራሉ፡፡

ሆኖም ለዓመታት ባንኮች ሲጮኹበት የነበረውን መመርያውን የማንሳት ጉዳይ አሁን ተቀባይነት ማግኘቱ፣ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ባንኮች ለግል ዘርፉ ሊሰጡት የሚችሉትን የብድር መጠን በማሳደግ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ የራሱ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚገልጹት የባንክ ኃላፊው፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት ባንኮች አለባቸው የተባለውን የገንዘብ እጥረት በመቅረፍ ረገድ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡  

ይህም ብቻ ሳይሆን ባንኮች ለብድር ያስከፍሉ የነበረውን የወለድ መጠን ዝቅ እንዲያደርጉ ጭምር ሊያደርጋቸው ይችላል የሚሉት የሌላ ባንክ ኃላፊ፣ አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት እንዲቀንስ ለማድረግም የመመርያው መነሳት የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ስላለው መንግሥት መመርያውን ማንሳቱ ተገቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቀድሞም ቢሆን በአንድ አገር በተመሳሳይ ሥራ ላይ ላሉ ባንኮች የተለያየ መመርያ በማውጣት፣ የግል ባንኮች ብቻ በአስገዳጅነት ተግባራዊ ማድረጋቸው በራሱ ትክክል አልነበረም ያሉም አሉ፡፡

መመርያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የማይመለከት ሆኖ የተሰናዳ በመሆኑ ብቻ፣ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ጤናማ ውድድር እንዳይኖር አድርጐ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

አሁን ግን የመመርያው መነሳት በኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር፣ ከሌሎች ጫናዎች ጋር ተደማምሮ ባንኮች የወለድ መጠናቸውን ጨምረው ስለነበር አሁን ወለዱን ደረጃ በደረጃ ይቀንሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ያልተጠበቀ ነው የተባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕርምጃ በባንኮች ዘንድ ደስታን የፈጠረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት የባንኮች የማበደር አቅም አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ መሆኑ እየተነገረ ስለሆነ፣ የገንዘብ እጥረት አለባቸው በሚባልበት በዚህ ጊዜ መንግሥት ይህንን መመርያ ማንሳቱ ዕፎይታ እንደፈጠርላቸው ብዙዎቹ የግል ባንኮች ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

ከስምንት ዓመታት በላይ የቆየው የብሔራዊ ባንክ መመርያ የግል ባንኮችን የማበደር አቅም ተፈታትኖ የቆየ የመሆኑን ያህል፣ ወደ ፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለመቀላቀል እየተዘጋጁ ያሉ አዳዲስ ባንኮችንም ሲያሳስብ ነበር፡፡ ነገር ግን ባንክ ለማቋቋም አስፈላጊውን ካፒታል ያሟሉ ባንኮች የዚህ መመርያ መውጣት ዕድለኞች አድርጓቸዋል እየተባለ ነው፡፡ እነሱም በመንግሥት ውሳኔ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች