Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለጤናማ ኢኮኖሚ ምቹ የመወዳዳሪያ ሜዳ ይኑር!

 

ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ከሚያስችሉና በመሠረታዊነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ጉዳዮች መካከል አንዱ ፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ የገበያ ውድድር ሜዳውን ማመቻቸትና ለዚህ ዕገዛ ማድረግ ጤናማ የግብይት ሒደት እንዲኖር ያስችላል፡፡

ለሁሉም ምቹ የሆነ የውድድር ሜዳ ማዘጋጀት ለተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን ለተገልጋዩ ጭምር ጠቃሚ መሆኑ ስለማይታበል፣ በየትኛውም የቢዝነስ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሉንም በኩል ሊያስተናግድ የሚችል የውድድር ሜዳ ይኑር መባሉ ተገቢ ነው፡፡ በአንድ ተመሳሳይ የሆነ ቢዝነስ ውስጥ ለአንዱ ሌላ ለሌላኛው ደግሞ ሌላ ሕግ ይኑር ከተባለ ጤናማ የግብይት ለመፍጠር አያስችልም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማሰብም ያስቸግራል፡፡

አንዱን የእንጀራ ልጅ ሌላውን ልጅ በማድረግ አድሏዊ አሠራር እንዲሰፍን የማያደርጉ አሠራሮች ዞሮ ዞሮ ጉዳታቸው አመዝኖ ለአገር ጠንቅ ይሆናሉ፡፡ ነፃ ገበያ ከታሰበ ከአድሎ የፀዳ የውድድር ሜዳ ማመቻቸት በምንም መለኪያ ቢሆን አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይገባም፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ይህንን ያህል ምቹ የመወዳደሪያ ሜዳ አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ እንደውም አንዳንድ ተግባራት በግልጽ ተወዳዳሪነትን የሚፃረሩ ሆነው ይታያሉ፡፡ አንዱን ከሌላው የማያበላለጡ ሕግጋት ወጥተው በሥራ ላይ ሲውሉም አይተናል፡፡ እያየንም ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አድሏዊ አሠራሮች ደግሞ ተወዳዳሪዎችንም ሆነ ተገልጋዮችን ሲበድሉ ቆይተዋል፡፡ ችግሩ ተወዳዳሪ ተቋማትንና ተገልጋዮችን ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም ጉዳት አስከትሏል ማለት እንችላለን፡፡

ለዚህ ደግሞ እንደ ምሳሌ የምናየው የግል ባንኮች ተለይተው አስፈጽሙ ሲባሉ የኖሩትን መመርያዎች እንደምሳሌ በማንሳት ነው፡፡ በተለይ ከሰባት ዓመታት በላይ ሲያሟግት የነበረውን አንድ መመርያ ብቻ እንመልከት፡፡ ይህም እያንዳንዱ የግል ባንክ ከሚሰጠው ብድር 27 በመቶ የሚሆነውን ለብሔራዊ ባንክ ቦንድ ግዢ እንዲውል የሚለው መመርያ ቀዳሚ ማሳያ ይሆናል፡፡

ይህ መመርያ ሲወጣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክን እንዳይመለከት ሆኖ የግል ባንኮች ብቻ በአስገዳጅነት እንዲፈጽሙት የወጣ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን መመርያ ሲያወጣ የራሱ ዕሳቤ ቢኖረውም፣ በአንድ ቢዝነስ ላይ ያሉ ተቋሞች በእኩል እንዳይወዳደሩ ያደረገ የነፃ ገበያ ሥርዓት የተፃረረ ተግባር መሆኑን እያወቀ መንግሥት እንዲተገበር አድርጓል፡፡

ጉዳዩን የበለጠ ተገቢ አልነበረም የሚያስብለው ደግሞ ከግል ባንኮች በቦንድ ግዥ ሲሰባሰብ የነበረው ገንዘብ ዓላማው መንግሥት ትኩረት ለሚሰጣቸው ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ነው የሚል ሆኖ ሳለ፣ በተግባር ግን ይህ ሆኗል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ገንዘቡን ወስዶ ሲያበድር የነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሁን ያለበትን ሁኔታ ስናይ፣ በእርግጥ ይህ መመርያ ብዙ በደሉ እንዲታወሰን ያደርገዋል፡፡

ለማንኛውም አጋጣሚ ሆኖ የግል ባንኮች ለቦንድ ግዥው የሚያውሉትን ገንዘብ ለብድር ቢያውሉ ኖሮ፣ አሁን ካላቸው በላይ ማበደር ችለው የተሻለ ትርፍ ባስመዘገቡ ነበር፡፡ የተሻለ ካፒታልም ሊኖራቸው በቻለ ነበር፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ይህ ሳይሆን ጤናማ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ከታሰበ እንዲህ ያሉ ሕጎች ይዋል ይደር እንጂ አደጋ የሚፈጥሩ መሆኑ የማይቀር መሆኑን ነው፡፡

ባንኮች መመርያው ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ በመፈጸማቸው የማበደር አቅማቸውን ቀንሷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ሊያበድሩ የሚችሉትን ገንዘብ በአነስተኛ ወለድ ቦንድ እንዲገዙበት መደረጉ፣ እያደረ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም መመርያው የመንግሥት ጉልበተኝነት ያሳየ ነበር ሊባል ይችላል፡፡

ዛሬ የባንኮች የማበደሪያ ወለድ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ለመምጣቱ አንዱ ምክንያት ይኸው ከባንኮቹ በግድ የሚወሰደው የቦንድ ግዥ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ አሻግሮ ባለማየት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ጣጣ የሚያመጡ መሆኑንም አሳይቷል፡፡ ባንኮቹ 27 በመቶ የሚወሰድባቸውን ገንዘብና ይህንን በማድረጋቸው የሚያጡትን በማስላት የብድር ወለዳቸውን ከፍ አድርገው ቆይተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገራዊ የዋጋ ግሽበት የራሱ አስተዋጽኦ ማድረጉ ግልጽ ነው፡፡ ሰሞኑን ግን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰማው ዜና ይህ ለዓመታት ሲጮህበት የነበረውን መመርያ መሻሩን የሚያመለክት መሆኑ ለኢንዱስትሪው ትልቅ ዕፎይታ ይሆናል፡፡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ሪፎርም ለማድረግ ከለውጡ ወዲህ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች እንደ ከፍተኛ የሚቆጠር እንደሚሆንም ይታመናል፡፡ መንግሥት ስለ እውነት ሪፎርም እያረገ ነው ሊያስብልም የሚችል ዕርምጃ ነው፡፡ መመርያው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እያስከተለ የቆየውን ተፅዕኖ ከማስቀረቱም በላይ በኢንዱስትሪው ላይ የውድድር ሜዳው የተስተካከለ እንዲሆን ያግዛል፡፡

ከዚህ መመርያ በኋላ ግን ባንኮች ቀስ በቀስ እያሳደጉ ያሉትን የመወዳደሪያ የወለድ መጠናቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል ማለት ነውና እንዲህ ያሉ ማሻሻያዎች ሲደረጉ ከእነዙም የተሻለ ነገር ይጠበቃልና ይህን በተግባር እንጠብቃለን፡፡ በወለድ መጠን ጨመረብኝ ሰበብ የተሰቀሉ ዋጋዎችና ኢንቨስትመንት ወጪዎች በተወሰነ ደረጃ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ለማንኛውም በዚህ ተግባሩ መንግሥት መመስገን አለበት፡፡

መመርያዎች ውሎ አድሮ ችግር በማይፈጥሩበት መንገድ መቀረፅ እንዳለባቸው የሚያመለክት ነው፡፡

ምክንያቱም ዛሬ ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ የሻረው ለባንኮቹ አስቦ ብቻ ሳይሆን አደጋ ያለው መሆኑን በመረዳቱ ጭምር እንደሆነ መገመት አያቅትም፡፡ በመሆኑም ጤናማ ኢኮኖሚ እንዲኖር ከተፈለገ ሁሉንም በኩል የሚያስተናግድ ሕግና ምቹ የመወዳደሪያ ሜዳ ያስፈልጋል፡፡ ለማንኛውም በዚህ መመርያ መሻር መንግሥትን ማመስገን ተገቢ ነው፡፡ እንዳይለመድህም መባል አለበት፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት