Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኅብረት ባንክ ከ979 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኅብረት ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከ979 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉንና ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶቹን በማስፋት የተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደጉ ተመለከተ፡፡

ባንኩ ከዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶቹ ጋር በተያያዘ በኤቲኤም፣ በኅብር ኦላይን፣ በሞባይል ባንክ ንግድና በመሳሰሉት ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ዓመት እንደነበር በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ከተቀመጡት ውስጥ አጠቃላይ የባንኩ የኤቲኤም ማሽኖች 118 መድረሳቸው የፓስ ማሽኖችን ደግሞ 244 ማድረስ መቻሉ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በባንኩ ኤቲኤምና ፓስ ማሽኖች 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ልውውጦች ተደርገው 1.14 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ግብይት መከናወኑ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በግብይት መጠን ላይ የ38.7 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ በግብይቱ የተመዘገበው የብር መጠን ላይ ደግሞ የ34.9 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ተገልጿል፡፡

በዚህ ረገድ ከተመዘገበው ውጤት 40,789 የሚሆነው የግብይት መጠን ወይም የ124.60 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ግብይት የተከናወነው በዓለም አቀፍ ካርዶች አማካይነት እንደሆነም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

ኅብር ዴቢት ካርድ በሚል መጠሪያ በሚታወቀው አገልገሎቱም በሒሳብ ዓመቱ በስማቸው የኅብር ካርድ የተሠራላቸው ደንበኞች ቁጥር 85,878 መድረሱንና በዚህ በኅብር ካርድ አማካይነት 1.25 ቢሊዮን ያህል ልውውጦች ተደርገው 1.29 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ግብይት መከናወኑ ተገልጿል፡፡ ይህም መጠን አምና ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር የ3.8 በመቶ ቅናሽ ቢያሳይም፣ በግብይት ዋጋው ላይ ግን የ0.8 በመቶ ያህል ጭማሪ እንዳሳየ ተገልጿል፡፡

በኅብር ኦንላን የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ላይ መሻሻል መታየታቸውን ያመለከተው የባንኩ ሪፖርት፣ በዚህም በሒሳብ ዓመቱ ማጠናቀቂያ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው አንፃር የ14.1 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 19,222 ደርሷል፡፡ በኅብር ኦንላን 5,189 ያህል ልውውጦች ተደርገው 141.5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ግብይት ተከናውኗል፡፡ በኅብር ኦላይን በተደረጉ ልውውጦች ላይ 87 በመቶ ዕድገት እንዲሁም በተመዘገበው የግብት ዋጋ ላይ ደግሞ 59.5 በመቶ ያህል ዓመታዊ ጭማሪ ስለመታየቱና ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱ ተገልጿል፡፡

የኅብር ሞባይል የባንክ አገልግሎትን በተመለከተም የኅብር ሞባይል የባንክ አገልግሎት ተጠቃዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ እንደሚገኝ የሚጠቁመው የባንኩ ሪፖርት፣ በኅብር ሞባይል የባንክ አገልግሎት ለመጠቀም የተመዘገቡ ደንበኞች ቁጥር 179,072 መድረሱን አመልክቷል፡፡ ይህም መጠን ከቀደመው ዓመት ቁጥር ጋር ሲነፃፀር የ24 በመቶ ጭማሪ ወይም በ34,172 ደንበኞች ያህል ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በኅብር ሞባይል የባንክ አገልግሎት የሚፈጽሙት ግብይት እያደገ ሲሆን፣ በተለይም  ባንኩ በበጀት ዓመቱ የጀመረው የሞባይል የአየር ሰዓት የመሙላት አገልግሎት በዚህ ረገድ እየታየ ላለው የደንበኞች ቁጥር መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ተጠቅሷል፡፡ በኅብር ሞባይል አገልግሎት የተከናወነው የግብይት መጠን ከባለፈው ዓመት ጋር በንፅፅር በ185.1 በመቶ ወይም በ88,502 ያህል ሲጨምር፣ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በሞባይል የባንክ አገልግሎት የተከናወነው አጠቃላይ የግብይት መጠን 136,312 ደርሷል፡፡ ይህ ቁጥር ከቀደመው ዓመት ጋር ሲወዳደር የ57.9 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየም ታውቋል፡፡ በኅብር የሞባል የባንክ አገልግሎት የተከናወነው አጠቃላይ የግብይት ዋጋ መጠን 489.1 ሚሊዮን ብር በላይ ስለማድረሱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሌላው አዲስ አገልግሎት የኅብር ወኪል የባንክ አገልግሎት ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ በኅብር ወኪሎች ቁጥር 428 ደርሷል፡፡ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የሞባይል ዋሌት ተጠቃሚዎች ቁጥር በሁለት በመቶ በመጨመር 11,666 ደርሷል፡፡ መጠናቀቂያ ላይ 918,180 ደርሷል፡፡ በአጠቃላይ በሒሳብ ዓመቱ ብዛታቸው 19,698 ወይም 921,219 ብር የሚሆን ዋጋ ያለው ግብቶች በኅብር ወኪል የባንክ አገልግሎት በኩል ተከናውኗል፡፡

 ይህ በእንዲህ እንዳለ የባንኩን ጥቅል ዓመታዊ የሥራና ክዋኔ በተመለከተ በባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር በቀረበው ሪፖርት፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ባንኩ በኢንዱስትሪው ጎልቶ እየታየ ያለውንና በየጊዜው በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣውን ፉክክር እንዲሁም በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈጥረው የነበሩ ተግዳሮቶችን በመቋቋም፣ የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ መልካም የሚባል ውጤት መመዝገቡንም አቶ ኢየሱስ ወርቅ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሒሳብ ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከቀድሞው ዓመት የስድስት ቢሊዮን ብር ወይም የ26.1 በመቶ ዕድገት በማሳየት 29.08 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ባንኩ በቀደመው ዓመት 23.07 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ እንደነበረው አስታውሰዋል፡፡

ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገት የባንኩን የማበደር አቅም ያሳደገለት እንደሆነም ያመለክታል፡፡ በሪፖርቱ በ2011 የሒሳብ ዓመት ለወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የተሰጠውን ጨምሮ በተለያየ ዘርፎች ለባንኩ ደንበኞች የተሰጠው አጠቃላይ የብድር ክምችት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የ14.87 ቢሊዮን ብር ወደ 21.61 ቢሊዮን ብር ሊያድግ ችሏል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ ደግሞ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰጠው 19.5 በመቶ በመሸፈን የአንበሳውን ድርሻ መያዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 ባንኩ እየተከተለ ባለው ጠንቃቃ የብድር አስተዳደር መርህ የብድር ዓይነቶቹ በሒሳብ ዓመቱ ጤናማ ሆኖ መዝለቁን ያመለከቱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ዘርፍም ከቀደመው ዓመት የተሻለ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ ባንኩ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ያገኘው 308.74 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

የባንኩ ጠቅላላ ሀብት በሰኔ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 35.74 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው የ28.03 ቢሊዮን ብር ጋር በንፅፅር ሲታይ የ7.7 ቢሊዮን ብር ወይም የ27.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ካፒታሉም  በ2010 የሒሳብ ዓመት ከነበረው የ2.95 ቢሊዮን ብር መጠን ጋር ሲነፃፀር፣ በ905.66 ሚሊዮን ብር ወይም በ30.7 በመቶ ዕድገት በማሳየት 3.86 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም ተገልጿል፡፡

ኅብረት ባንክ  በ2011 ዓ.ም. 3.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም በታሪኩ ትልቅ የሚባል የገቢ መጠን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህ ገቢ ካለፈው ዓመት ከተመዘገበው የ2.79 ቢሊዮን ብር ጋር በንፅፅር ሲታይ የ1.02 ቢሊዮን ብር ወይም የ36.5 በመቶ ያህል ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው ገቢ ውስጥ 82.6 በመቶ ያህል የሚሆነው ከወለድ የተገኘ ገቢ ነው፡፡ የባንኩ አጠቃይ ወጪው 2.8 ቢሊዮን ብር ሆኖ ሲመዘገብ ይህም መጠን አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው የ2.09 ቢሊዮን ብር ወጪ መጠን ጋር ሲነፃፀር የ747.0 ሚሊዮን ብር ወይም የ35.8 በመቶ ጭማሪን አሳይቷል ተብሏል፡፡

ባንኩ ከትርፍ ግብር በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን 979.8 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው የትርፍ መጠን ጋር ሲነፃፀር የ272.82 ሚሊዮን ብር ወይም 38.6 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሆኗል፡፡

የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ባለፈው ሐሙስ ሲካሄድ ባንኩን የሚመሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ተካሂዷል፡፡

ኅብረት ባንክ በ2011 የሒሳብ ዓመት 45 ተጨማሪ ቅርንጫፎቹን በመክፈቱ፣ አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 274 አድርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች