Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከልብም በላይ

ከልብም በላይ

ቀን:

ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ቅጥር ግቢ በሚገኘው የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል በርካታ ሕፃናት ይታያሉ፡፡ ግማሾቹ በወላጆቻቸው እቅፍ ውስጥ ሲሆኑ፣ እኩሉ ደግሞ ተቀምጠዋል፡፡ ጥቂቶቹ እየተሯሯጡ ይቦርቃሉ፡፡ ሁሉም የልብ ሕሙማን ናቸው፡፡ አንድ አባት ደግሞ ጣቶቻቸውን አፋቸው ላይ አድርገው ተክዘዋል፡፡ በሆስፒታሉ ለምን እንደተገኙ ስንጠይቃቸው ከቃላቸው የቀደመው እንባቸው ነበር፡፡ በአውራ ጣታቸውና አመልካች ጣታቸው ከዓይናቸው የሚፈሰውን እንባ ለመገደብ እየሞከሩ የሆኑትን አወጉን፡፡

የ68 ዓመቱ አቶ ነጋሳ ሰሳባ ከግንደበረት ጀልዱ ወረዳ የሰባት ዓመት ሴት ልጃቸውን ለማሳከም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚገኘው የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል የተገኙት ማክሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ እኛ ያገኘናቸው ደግሞ በማግሥቱ ነበር፡፡ ከማዕከሉ በተደረገላቸው የስልክ ጥሪ መሠረት ከዚህ ቀደም የሕክምና ክትትል ታደርግ የነበረችውን ልጃቸውን ይዘው ተገኝተዋል፡፡ ‹‹ልጄ መቼ ሕክምና [ቀዶ ሕክምና] እንደምታገኝ አላውቅም፡፡ እኔ ግን ተቸግሬያለሁ›› ሲሉ እንባቸውን አረገፉት፡፡

ለአቶ ነጋሳ ችግራቸው ልጃቸው ሕክምና አግኝታ ትድን ይሆን? ወይስ? የሚለው ብቻ አልነበረም፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ መለኩ ባዶ የሆነው ኪሳቸው እሳቸውና ልጃቸው እንዲራቡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ልጃቸው ሕክምና ክትትል ከጀመረች ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በሬያቸውን ከመሸጥ ጀምሮ ያላቸውን ብር ጨርሰዋል፡፡

- Advertisement -

ለአርሶ አደሩ ነጋሳ የትራንስፖርት፣ የማደሪያ፣ ሕክምናው ነፃ ቢሆንም በየቀኑ የሚወሰዱ መድኃኒቶችን መግዛት ፈተና ነው፡፡ በተለይ ለሕክምና ቀጠሮ አዲስ አበባ ሲመጡ ዙሪያው ገደል ነው፡፡

ለአሁኑ ሕክምና ተጠርተው ሲመጡም ልጃቸውን ታቅፈው ያደሩት በሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍል አካባቢ ንጣፍ ድንጋይ ላይ ነው፡፡ ‹‹ድንጋይ ላይ ነው ያደርነው፤›› ሲሉም ምንም ብር እንደሌላቸው አወጉን፡፡ እንዲህ ዓይነት ውስብስብ ማኅበራዊ ችግር ከክልል በተለይ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ሕክምና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለሚመጡ ታካሚዎች ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ህሊና በፍቃዱ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ከሕክምናው ጎን ለጎን በየእለቱ በማዕከሉ የሚታየው ማኅበራዊ ችግር፣ ችግሩን በየቀኑ ለሚያዩት የሕክምና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ድንገት መጥቶ የሚያየውን ዜጋ ልብ የሚሰብር ነው፡፡

ከማኅበራዊ ቀውሱ ጎን ለጎን ታመው የሚመጡ ሕፃናትም በሕመማቸው ሲሰቃዩ፣ ለዓመታት ሕክምና አጥተው ሲንከራተቱ ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚጠቁ ሕፃናት ሕክምናን በቀላሉ የሚያገኙበት በቂ ተቋም የለም፡፡ በቂ ተቋም ከማይገኝላቸው ሕመሞች አንዱ በሆነው የልብ ሕመም ከተቸገሩ ሕፃናት፣ ከቡራዩ ከተማ የመጣችው የስምንት ዓመት ሕፃን ትገኝበታለች፡፡

ሕፃኗ የልብ በሽታ ያደረባት ገና እንደተወለደች ነው፡፡ የተወለደችውም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲሆን፣ በወቅቱ በኦክስጅን በመታገዝ ሙቀት ክፍል ገብታ እንክብካቤ ተደርጎላት ነበር፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ልቧ ላይ ከፍተት በመታየቱ ነው፡፡

ወላጅ እናቷ ወ/ሮ የሺ ይመር እንዳሉት፣ ክፍተቱ በራሱ ጊዜ ይገጥማል በማለት በዚሁ ሆስፒታል ክትትል ስታደርግ ቆየች፡፡ ነገር ግን የተባለው ሳይሆን በመቅረቱ ለሕፃናት የልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ሪፈር ተባለች፡፡ በዚሁ በየወሩ ክትትል ስታደርግ ስምንት ዓመት ሆኗታል፡፡ መድኃኒት እየሰጧት ትመላለሳለች፡፡

አሁን ግን ‹‹ሴቭ ኤ ቻይልድ ኸርት›› የተባለው የእስራኤል ቀዶ ሕክምና ቡድን ስለመጣ›› እንዲያያት ተጠርታ መምጣቷንና ወረፋ በመጠባበቅ ላይ መሆኗን እናቷ ገልጸው፣ ሕፃኗ የአንደኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነች፣ ነገር ግን መንገድ ስትሄድ እንደሚደክማት፣ ጉንፋን እንኳን የያዘው ሰው አጠገቧ ከቆመ በቀላሉ ልትጠቃ እንደምትችል አስረድተዋል፡፡

ሌላዋ የልብ ታማሚ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነችው የስድስት ዓመት ሕፃን ነች፡፡ ሦስት ዓመት እንደሞላት ሜዳ ላይ ትወድቅና እግሯ ላይ የመሰበር አደጋ ይደርሳል፡፡ ወደ ሕክምና ተቋም ተወስዳ ለቀዶ ሕክምና ቅድመ ምርመራ ሲደረግላት የልብ ሕመምተኛ መሆኗ ታወቀ፡፡ በዚህም የተነሳ ለማዕከሉ ሪፈር ተደርጎላት እንደመጣች፣ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ እንደሆነችና ትምህርቷን ግን እንዳልጀመረች ወላጅ አባቷ ተናግረዋል፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር ሔለን በፈቃዱ (ዶ/ር) ‹‹ሕክምናው ላይ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ከክልል የሚመጡና ክትትል የሚያስፈልጋቸው የልብ ሕሙማን ሕፃናት መጠለያና ምግብ ባለማግኘታቸው የሚደርስባቸው ችግር ነው፡፡ ሕፃናቱ ከባድ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ እስኪያገግሙ ድረስ ለብርድና ለረሃብ  መጋለጣቸው፤ ቀዶ ሕክምና ተደርጎ በተወሰነ ቀን ከማዕከሉ የሚወጡ በመሆኑና ከዚህም በኋላ ለሳምንታት ያህል በቅርበት ማገገም ሲገባቸው ተመልሰው ቀያቸው እንዲሄዱ ማድረጉ፣ አሊያም እዚሁ [ከማዕከሉ] ውጭ መልቀቁ ከባድ ፈተና ነው›› ብለዋል፡፡

አብዛኞቹ ታካሚዎች የሚመጡት ከክልል ሲሆን፣ ሕክምናውን ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ እያሉ ለሚያጋጥማቸው ማኅበራዊ ችግር ማቃለያ የሚውል የማዕከሉ ባለሙያዎች ‹‹እኛው በእኛው›› የሚል እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ የእንቅስቃሴውም ዓላማ ማዕከሉ አካባቢ ከሚገኙት ትንንሽ ሆቴል ቤቶች ምግብ እየተገዛላቸው እንዲቀርብላቸው ማድረግ ሲሆን፣ ባለሙያዎቹ ይህን የሚያደርጉት ከኪሳቸው በማዋጣት ነው፡፡ ሆኖም ሁሉንም ለማዳረስ እንዳልተቻለ ዶ/ር ሔለን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ አባባል፣ ቢያንስ ሦስት ክፍሎች ያሉት ቤት ቢሠራላቸው ሕፃናቱ ከቀዶ ሕክምና በኋላ እስኪያገግሙ አብረው የመጡ ቤተሰቦች ምግባቸውን በዚህ እያበሰሉ ቢመገቡ ችግሩን በመጠኑ መቅረፍ ይቻላል በሚል እምነት የተጠቀሱትን ሐሳቦች ያካተተ ፕሮጀክት ተቀርፆ ለትግበራውም ድጋፍ ለማግኘት ለኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ቀርቦ ነበር፡፡ ሆኖም ምንም ውጤት ሳይገኝ ቀርቷል፡፡

በማዕከሉ ውስጥ ካርድ ከማውጣት ጀምሮ የሚሰጠው አገልግሎት ከክፍያ ነፃ ነው፡፡ በአንፃሩ ግን ለቀዶ ሕክምናው የሚያስፈልጉ አላቂ ዕቃዎች በጣም ውድና ከአቅም በላይ ሆኗል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ በቀዶ ሕክምናው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መጥቷል፡፡ ይህ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ማዕከሉ ለሕፃናቱ ማቆያ ሥፍራ የማቋቋም አቅም የለውም፡፡ ለዚህም ባለሀብቶች ተባብረው ሕሙማኑን እንዲታደጉ ዶ/ር ሄለን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማዕከሉ ከተመሠረተ ጀምሮ ከ5,000 በላይ ለሚሆኑ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ነፃ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ በቀዶ ሕክምና ሥራው ላይ ዘ ችልድረንስ ሔልዝ ፈንድ ኦፍ ኢትዮጵያ እንዲሁም ሌሎች አጋሮች ከፍተኛ ዕገዛና ትብብር እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡

ዕገዛውም ያተኮረው ባለሙያዎችን በማሠልጠንና በማዕከሉ ሊሠራላቸው የማይችሉትን ታካሚዎች ወደ እስራኤል እየላኩ ከፍተኛውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ማዕከሉ ያሠለጠናቸው 12 ሐኪሞችና ከ60 በላይ የጤና ባለሙያዎች ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ችለው ሕክምናውን መስጠት እንደቻሉ፣ ይህም እንደ አገር ሲታይ ከፍተኛ ኩራት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የ ዘ ችልድረን ሔልዝ ፈንድ ኦፍ ኢትዮጵያ ቦርድ ዳይሬክተር አቶ ሳላዲን ከሊፋ፣ ሴቭ ኤ ቻይልድ ኸርት የተባለው ቡድን በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ እየመጣ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ ይዞት ከመጣው አላቂ የሕክምና ዕቃዎች መካከል 90 ከመቶ ያህሉን ከተገለገሉበት በኋላ የቀረውን እዚህ በመተው ኢትዮጵያውያን የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች እንዲጠቀሙበት የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ድርጅታቸው ከእስራኤል ባሻገር አሜሪካና እንግሊዝ ካሉት የሕፃናት ልብ ሕክምና ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዳለው፣ በዚህም በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነፃ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

‹‹የውጭ አገሮች የሕክምና ቡድኖች እየመጡ አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረገበት ምክንያት እነሱ የሚያከናውኑትን የቀዶ ሕክምና የሚሠራ የሰው ኃይል ስለሌለን ሳይሆን፣ ይዘውት ከሚመጡት አላቂ ዕቃዎች መካከል የተረፈውን የእኛ ሐኪሞች እንዲገለገሉበት ለማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ልናደርግ ያስገደደን የአላቂ ዕቃዎች ዋጋ በጣም ውድና ከአቅም በላይ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የቀዶ ሕክምናውን ሥራ በኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ለማከናወን፣ ለቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጉ አላቂ ዕቃዎችን በተቻለና አቅም በፈቀደ መጠን በማቅረብ ማዕከሉን የምርምርና የሥልጠና ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ መዘጋጀቱን የቦርድ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ወደ 8,000 የሚጠጉ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ለቀዶ ሕክምና ተመዝግበው ለአገልግሎቱ ወረፋ በመጠባበቅ  ላይ ናቸው፡፡ ማዕከሉ ከተቋቋመበት ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ከ5,000 በላይ ሕፃናት ተገቢውን የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንዳገኙ አስረድተዋል፡፡

ማዕከሉ በዓመት እስከ 1,600 ሕፃናትን የማከም አቅም ቢኖረውም፣ እያከመ ያለው እስከ 450 ሕፃናትን ብቻ ነው፡፡ ይህም የሆነው ለቀዶ ሕክምና አገልግሎት በሚውሉ አላቂ ዕቃዎች ዕጦት ምክንያት የተነሳ እንደሆነ አቶ ሳላዲን ተናግረዋል፡፡

ለሚቀጥለው አምስት ዓመት የሚተገበር መርሐ ግብር እንደተዘረጋ፣ አደረጃጀቱንና ተደሯሽነቱን ባካተተው በዚህ መርሐ ግብር መሠረት ቢያንስ በዋና ዋና ከተሞች ሁለት ወይም ሦስት የልብ ሕሙማን ክሊኒኮችን ለማቋቋም እንደታሰበም አክለዋል፡

የቀዶ ሕክምናውን ሥራ የሚያከናውነው ቴልአቪቭ እስራኤል ከሚገኘው ኢድዝ ዋልፍሰን የሕክምና ማዕከል የመጣ ‹‹ሴቭ ኤ ቻይልድ ኸርት›› የተባለው ቡድን ሲሆን፣ ለአንድ ሳምንት ያህል በሚያካሂደው የቀዶ ሕክምና ቢያንስ 30 የልብ ሕሙማን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

የሴቭ ኤ ቻይልድ ኸርት ዋና ዳይሬክተር ሲሞን ፊሸር እንደገለጹት፣ ቡድኑ የፆታ፣ የጎሳና የሃይማኖት ልዩነት ሳያደርግ በመላው ዓለም የሚገኙ የልብ ሕሙማን ሕፃናትን ይታደጋል፡፡

በሕፃናት ልብ ሕሙማን ማዕከል ለ30 ሕፃናት የሚደረገውን የልብ ቀዶ ሕክምና አስመልክቶ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተሰጠው መግለጫ፣ በ1988 ዓ.ም. የተመሠረተው ቡድኑ የሕፃናት የልብ ሕክምና ማዕከልን ወደ ልቀት ማዕከል የማሸጋገር ሥራ እንደሚያከናውን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...