ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን ችሎ መቋቋም እንደሚችልና ባንኮች ከመስኮት አገልግሎት ውጪ ራሱን የቻለ የወለድ አልባ ቅርንጫፍ ከፍተው መሥራት እንደሚችሉ ከታወቀ ወዲህ፣ የተለያዩ ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ የሚሰጥ ቅርንጫፍ ወደ መክፈት እየገቡ ነው፡፡
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ቅርንጫፎች በመክፈት ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ሌሎች የግል ባንኮችም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎችን በመክፈት ላይ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌላ አቢሲኒያ ባንክ ተመሳሳይ ቅርንጫፍ በመክፈት አገልግሎት ጀምሯል፡፡
አዋሽ ባንክ ኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ አዲስ አበባ ቤተል አካባቢ በመክፈት ያስመርቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት 11 ባንኮች ከወለድ ነፃ ባንክ የባንክ አገልግሎቶችን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን ለማስፋፋትና እስካሁን በእምነቱ ምክንያት ወደ ባንክ ከመምጣት የተቆጠቡ የኅብረተሰቡን ክፍል ለማዳረስ፣ ከመስኮትና ከቅርንጫፍ ባሻገር ራሱን የቻለ ባንክም ወደ ማቋቋም ተገብቷል፡፡ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረጉ ስለመሆኑ ሲነገርላቸው ከነበሩት ውስጥ ዘምዘምና ሒጅራ ባንኮች ወደ ሥራ የሚያስገባቸውን ካፒታል በማሟላት ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጁ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ዘምዘምና ሒጅራ ባንኮች በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እስካሁን ባለው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች አሥራ አንዱ ባንኮች ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ መስብሰባቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡