ከሁሉም የመድን ሽፋን ዓይነቶች ትርፋማ መሆኑን የገለጸው ናይል ኢንሹራንስ፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከመድን ሥራ ውል ካገኘው ትርፍ ውስጥ ከፍተኛው ከተሽከርካሪዎች መድን ሽፋን የተገኘው እንደሆነ አመለከተ፡፡
ኩባንያው የ2011 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ኅዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንደተገለጸው፣ በሁሉም የመድን ዓይነቶች ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ከጠቅላላ የመድን ሥራ ከተገኘው 129 ሚሊዮን ብር ትርፍ ውስጥ 69.1 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ከተሽከርካሪ መድን ሽፋን የተገኘ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ውጤት የተገኘው ኩባንያው የተሽከርካሪ መድንን ትርፋማ ለማድረግ ጥንቃቄ የተሞላበት የሥራ ውል በማከናወኑ ስለመሆኑ፣ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መቅደስ አክሊሉ ባቀረቡት ሪፖርት ጠቅሰዋል፡፡
ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከመድን ሥራ ውል ያገኘው ጥቅል ትርፍ 129 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚ ዓመቱ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን ያመላክታል፡፡ ኩባንያው በ2010 የሒሳብ ዓመት ከመድን ሥራ ውል አግኝቶ የነበረው ትርፍ 77.9 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡
ይህም ከኢንቨስትመንት የተገኘን ገቢ ሳይጨምር ከአጠቃላይ የመድን ሥራ ዘርፍ ኩባንያው ከታክስ በፊት 94.7 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉ ታውቋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከመድን ሥራ የተገኘው ትርፍ ከቀዳሚ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ49 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል፡፡ በ2010 የሒሳብ ዓመት ከመድን ሥራ ያገኘው ትርፍ 63.7 ሚሊዮን ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከሪፖርቱ መረዳት እንደሚቻለው ኩባንያው በ2011 የሒሳብ ዓመት ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶች 77.3 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ አቶ መቅደስ በሪፖርታቸው እንዳመለከቱትም፣ የኢንቨስትመንት ገቢ ከውል ሥራ ቀጥሎ ለኩባንያው ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ እስከ በ2010 መጠናቀቂያ የኩባንያው ጠቅላላ ኢንቨስትመንት ከ634.6 ሚሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት አቶ መቅደስ፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ግን 570.9 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህም የአሥር በመቶ ቅናሽ አሳቷል፡፡ ቅናሹ የታየውም ለዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የማጠናቀቂያ ሥራ በጊዜ ከተገደበ ተቀማጭ ገንዘብ ላይ ወጪ በመደረጉ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኩባንያው ያገኘው የኢንቨስትመንት ገቢ ካለፈው ዓመት 79.1 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ2.4 በመቶ በመቀነስ፣ 77.3 ሚሊዮን ብር ሊሆን ችሏል፡፡
ከጠቅላላ የኢንቨስትመንት ገቢ ውስጥ በጊዜ ከተገደበ ተቀማጭ ገንዘብ የተገኘ የወለድ ገቢ የአንበሳውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ከተቀማጭ ገንዘብ ወለድ የተገኘው ገቢ 47.8 ሚሊዮን ብር መሆኑም ታውቋል፡፡ ይህም ከጠቅላላ ገቢ ውስጥ የ61 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ ከአቢሲኒያ ባንክና ከኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ የተገኘው የአክሲዮን ትርፍ ደግሞ 20.8 ሚሊዮን ብር በማስገኘቱ፣ ከጠቅላላ ገቢው የ26 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ ቀሪው 8.6 ሚሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ገቢ የተገኘው ከሕንፃ ኪራይ ሲሆን፣ ይህም የገቢ ዓይነት የ13 በመቶ ድርሻ እንደያዘ ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ ከሌሎች ምንጮች የተገኘው ገቢ 2.9 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ5.6 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡ ይህም በዋናነት ያገለገሉ ቋሚ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ የተገኘው ገቢ ነው፡፡ በድምር ሲታይ ኩባንያው ከኢንቨስትመነት ገቢውና ከመድን ሥራ ውል የተገኘው ጠቅላላ የተጣራ ትርፍ 110.5 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቀዳሚው ዓመት የተገኘው የተጣራ ትርፍ 63.5 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡
ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ይህንን ያህል ትርፍ ያገኘ ቢሆንም፣ ዓመታዊ ገቢው ግን መቀነሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያው በ2011 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የዓረቦን ገቢ 393.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት 406.9 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ3.3 በመቶ ቅናሽ እንዳለው ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ የኩባንያው የተጣራ ዓረቦን ገቢ በ6.3 በመቶ በመቀነስ 322.7 ሚሊዮን ብር መሆኑን ያመለከቱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ለመቀነሱ ምክንያትም የገበያ ውድድር ጫና ከማሳደሩ ባሻገር ኩባንያው ትርፋማ ባልሆኑ ቢዝነሶች ላይ የተከተለው ጥንቃቄ የተሞላበት የውል ሥራ አስተዋጽኦ ነበረው ብለዋል፡፡
ከጠቅላላ ኢንሹራንስ ዓረቦን ገቢ ውስጥ የተሽከርካሪ መድን 61 በመቶ ድርሻ ሲኖረው የኃላፊነት፣ የገንዘብ ነክ፣ የእሳት አደጋና የአካል ጉዳት የመድን ዓይነቶች በተከታታይ የ9.4 በመቶ፣ የ7.5 በመቶ፣ የ7.1 በመቶ እና የ5.8 በመቶ ድርሻ ወስደዋል፡፡ በሌላም በኩል የኢንጂነሪንግ፣ የባህርና የየብስ ጉዞና የሠራተኞች ጉዳት የመድን ዓይነቶች በጥቅሉ የ9.3 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኩባንያው የሒሳብ ዓመቱ የተጣራ የካሳ ክፍያም 197.5 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት 219.3 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ9.9 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ ተጠቅሷል፡፡ በተመሳሳይም ለኩባንያው የቀረቡ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች መጠን 188.9 ሚሊዮን ብር በመሆኑ የካሳ ምጣኔ 58.5 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው የ75 በመቶ ካሳ ምጣኔ ጋር በንፅፅር ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል፡፡ ይህም የካሳ ሒደቱን ለማሻሻል በተደረገ ጥረት የተገኘ ውጤት እንደሆነ የሚያመለክተው የኩባንያው ሪፖርት፣ አስተዳደራዊና ጠቅላላ ወጪዎች ካለፈው ዓመት 86.6 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ22.3 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳት 105.9 ሚሊዮን ብር ስለመድረሱም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በሁሉም የመድን ዓይነቶች የውል ሥራ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ በተለይም በሞተር፣ ገንዘብ ነክና በእሳት አደጋ የመድን ዓይነቶች የተገኘው ትርፍ በከፍተኛ ነበር፡ በሌላም በኩል ኩባንያው ያስመዘገበው የተጠቃለለ የካሳና የወጪ ምጣኔ 92.8 በመቶ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው የ102.5 በመቶ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሻሻል አለው ተብሏል፡፡
የሕይወት መድን የዓረቦን ገቢውን በተመለከተም እስከ 2011 የሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ከሕይወት መድን ያገኘው የዓረቦን ገቢ 45.2 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት 33.8 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ33.6 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ኩባንያው እየገነባ ስላለው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በሰጡት ማብራሪያ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ያለመጠናቀቁ ተናግረዋል፡፡ የማጠናቀቂያ ሥራው በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እንዳይከናወን ካደረጉ ምክነያቶች አንዱ በአማካሪ ድርጅቱ በኩል የሚከናወነው የዲዛይን ማሻሻል ሥራ በውለታ በተሰጠ ጊዜ ባለማጠናቀቁ መሆኑን አንዱ ሲሆን፣ ከዚህም ሌላ የግንባታ ማጠናቀቂያ ሥራውን ለመከወን የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ያለመገኘት ሌላ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ቢሆን የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ በማግኘት ግንባታውን በቶሎ ለማጠናቀቅ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኩባንያው የተከፈለ ካፒታሉ በቀዳሚ ዓመት ከነበረው 302.7 ሚሊዮን ብር አንፃር ሲታይ 20.9 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ለማድረስ በወሰነው መሠረት የ2011 ዓ.ም. የተጣራ ትርፉን ለካፒታሉ ማሳደጊያ ይውላል ተብሏል፡፡