የኢሕአዴግ አህት ድርጅቶችና የአጋር ድርጅቶች ሥራ አስፈጻሚ አባላት ለሦስት ቀናት የአዲሱን ፓርቲ ውህደት፣ ፕሮግራምና ሕገ ደንብ ላይ በመወያየት በሦስቱም አጀንዳዎች ላይ የሚያግባቡና የሚያቀራርቡ፣ እንዲሁም በአቀራረብ ዴሞክራሲያዊ የሆኑና ሁሉንም ሐሳብ በማንሸራሸር ውሳኔዎች መተላለፋቸውን፣ የግንባሩ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሦስቱን ቀናት ስብሰባ መጠናቀቅ አስመልክተው ማክሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ውሳኔዎቹ በዚህ መንገድ ማለፋቸው፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለመላው ለፓርቲያችን አባላት ታላቅ ድል ስለሆነ እንኳን ደስ አላችሁ፤›› ብለዋል።
በውይይቱ የመጀመሪያ ቀን ለየብቻቸው የነበሩ ፓርቲዎች ተዋህደው የብልፅግና ፓርቲ በመባል ብልፅግናን ለኢትዮጵያ በቁስ ብቻ ሳይሆን በክብርም፣ በነፃነትም፣ በሁሉም ሁለንተናዊ መንገዶች ማረጋገጥ የሚችል ፓርቲ እንዲሆን፣ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ የተበታተነ ጉልበትን ሰብሰብ ብሎ በጋራ መቆምና መምራት እንዲቻል መወሰኑ እጅግ በጣም ድንቅ ውሳኔ ነበር ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ውሳኔዎቹ በእያንዳንዱ ዕርምጃ ሕግ የተከተሉ እንዲሆኑ፣ በውይይትና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች እንዲፈሙ በማድረግ የተሳካ ውጤት ማምጣት ተችሏል ብለዋል። በተጨማሪ የፌደራል ሥርዓቱ በየጊዜው የሚሻሻልና የሚያድግ በመሆኑ እስካሁን የነበሩ ስህተቶችን በሚያርምና የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ብዝኃ ቋንቋ፣ ባህልና ፍላጎቶች ያሉባትን አገር ወጥ በሆነ መንገድ ሳይሆን ለሁሉም ዕውቅና በሰጠ፣ ባከበረና ባሳተፈ፣ በተጨማሪም ሁሉንም ወገኖች በማሳተፍና በሚገባቸው ልክ የሚያስፈልጋቸውን ማቅረብ በሚያስችል ማንነት የሚደራጅ ፓርቲ እንዲሆን መወሰኑንም ገልጸዋል።
በዚህ አግባብ አዲሱ ውህድ ብልፅግና ፓርቲ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮሚኛን፣ ትግርኛን፣ ሶማሊኛንና አፋርኛን የሥራ ቋንቋው ለማድረግ መወሰኑን፣ እነዚህ ቋንቋዎች የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ፓርቲው እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ይህም ኢትዮጵያውያን አንዱ ከአንዱ ተምረው የጋራ አገራቸውን ለመገንባት ይበልጥ የሚያጠናክር፣ እስካሁን ከነበረው በእጅጉ የላቀ ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህም በላቀ እያንዳንዱ ሕዝብ የሚሳተፍበትና ሌላውን የሚያከብርበት የዴሞክራሲ ዓውድ ለመፍጠር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ውይይቱ በጥቅሉ ለኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ያመጣ፣ ኢትዮጵያን በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ወደ ብልፅግና ተርታ ለማሸጋገር የነበረንን ትልም ለማሳካት የሚያግዝ በመሆኑ በታላቅ ደስታ ያጠናቀቅን ሲሆን፣ መላው የፓርቲያችን አባላት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እፈልጋለሁ፣ አመሠግናለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ምክትል ሊቀመንበሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ኢሕአዴግ በከፍተኛ የመዋቅር ችግር ውስጥ መቆየቱን ገልጸው፣ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን ብሔርና አገራዊ ማንነት በሚባሉ ሁለት ፅንፎች እንድትወጠር ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ አዲሱ ውህድ ፓርቲ አገራዊ አንድነትንና ብዝኃነትን፣ እንዲሁም የግልና የቡድን መብቶችን በማክበር ለኢትዮጵያ ብልፅግና እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ብልፅግና ፓርቲ የሚለውን ስያሜ ለኢሕአዴግ ምክር ቤቱ እንዲቀርብ፣ የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውይይት ካደረገ በኋላ ከስምምነት ላይ በመድረሱ ወደዚያው ተመርቷል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ከዚህ ቀደም በኢሕአዴግ የሚታወቁትን የሊቀመንበርና የምክትል ሊቀመንበር ስያሜዎች በማስቀረት፣ በፕሬዚዳንትና በምክትል ፕሬዚዳንት መተካቱን በረቂቅ ሕገ ደንቡ አካቷል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ረቂቅ ሕገ ደንብ በአምስት ክፍሎች የተዋቀረ ነው፡፡ ጠቅላላ ድንጋጌዎች፣ አባልነት፣ የፓርቲው አወቃቀርና አደረጃጀት፣ የፓርቲው የክልል ቅርንጫፎችና የአካባቢ አካላት፣ እንዲሁም ልዩ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡
ውሁድ ፓርቲው ከፌዴራሊዝም አንፃር ያለው ዕሳቤ ሲተነተን ሞግዚት የለሽ ውክልና ያለው ሆኖ፣ ሕዝቦች ያለ ሞግዚት በመረጡትና በፈቀዱት መተዳደር መቻላቸውን፣ ትክክለኛ ፌደራላዊ ሥርዓት በመከተል የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የታዩ ጉድለቶች እንደሚሞሉ፣ የጋራ ዕሳቤን በማጎልበት ልዩነትን አክብሮ አንድነታቸው የተጠበቀ አንድ ዓይነት ያልሆኑ ሕዝቦችን መገንባት ግቡ ያደረገ መሆኑን፣ ብዝኃነትን ያከበረና እኩልነትን በተግባር የሚያረጋጥ ሥርዓት መገንባት እንደሚቻል ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከውህደት በኃላ የሚመሠረተው ብልፅግና ፓርቲ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአገር ጉዳይ ላይ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማገዝ፣ ለሐሳብና ለምክክር ቅድሚያ የሚሰጥና ለዴሞክራሲያዊ ምኅዳር ዓውዱን ክፍት የሚያደርግ፣ ጊዜውን ጠብቀው ለሚነሱ ሐሳቦች ቀድሞ መደላድል መፍጠር የሚችልና ሁሌም ለለውጥ የማይዘናጋና ዳተኛ የማይሆን፣ ከለውጥ ጋር መለወጥ የሚችል፣ አገርን ወደ ለውጥ የሚያሻግር፣ ለትውልድ መሻገር የሚችል፣ በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂ፣ በልማትና በሰላም ሁለንተናዊ ብልፅግናዋ የተረጋገጠ አገር መፍጠር ግቡ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የኢሕአዴግ ሦስቱ አባል ድርጅቶች ማለትም አዴፓ፣ ኦዴፓና ደኢሕዴን ውህድ ፓርቲውን ለመመሥረት በአብላጫ ድምፅ ሲስማሙ፣ ሕወሓት ግን ባለመስማማቱ በተቃውሞ ራሱን ከሒደቱ አግልሏል፡፡