በቀድሞ ጎጃም ጠቅላይ ግዛት በመተከል አውራጃ ድባጤ ከተማ በ1961 ዓ.ም. የተወለዱት የቀድሞ የቤኒሻኑጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ በድንገተኛ ሕመም ሰኞ ኅዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት 5፡00 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
አቶ ያረጋል ኅዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በድንገት ታመው ራሳቸውን በመሳታቸው፣ በቅርብ ወደሚገኘው ሲኤምሲ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውን ሪፖርተር ከቅርብ ጓደኞቻቸው ለመረዳት ችሏል፡፡ ለሞት የዳረጋቸው ሕመም በሙሉ የምርመራ ውጤት ወደፊት የሚታወቅ ቢሆንም፣ ሆስፒታል እንደገቡ ሕመማቸው የደም ግፊት እንደነበር አክለዋል፡፡
ለሦስት ቀናት በፅኑ ሕሙማን ክፍል (ICU) መቆየታቸው፣ ኅዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት 5፡00 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ታውቋል፡፡ አቶ ያረጋል ባለትዳር፣ የአንዲት ሴት ልጅና የሁለት ወንዶች ልጆች አባት መሆናቸውም ታውቋል፡፡
የ51 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ያረጋል የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልን ከነሐሴ 1 ቀን 1987 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2001 ዓ.ም. ድረስ በፕሬዚዳንትነት የመሩ ሲሆን፣ ከ1986 ዓ.ም. እስከ የካቲት 30 ቀን 1987 ዓ.ም. ድረስ በክልሉ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ጥናትና ምርምር መምርያ ኃላፊ፣ እንዲሁም የክልሉ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሥራታቸውም ታውቋል፡፡ ከክልሉ ፕሬዚዳንትነታቸው ከተነሱ በኋላ ወደ ፌዴራል መንግሥት በመዛወር፣ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለአንድ ዓመት ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡