Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በአለመረጋጋት ሊጠቀሙ የሚሯሯጡ ነጋዴዎች ዕርምጃ ይወሰድባቸው

ለመልካም ያሰብነው ለውጥ ሲፈተን እያየነው ነው፡፡ ለውጡን በቀናነት ተቀብለው ወደፊት ለማራመድ የተቸገሩ የሚፈጥሩት ግርግር፣ የዚህችን አገር ሰላም እየበረዘና ላለመረጋጋት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የሚስተጋቡት ሐሰተኛ መረጃዎች ሲታከልበት ችግሩን አብሶታል ማለት ይቻላል፡፡ ለእንዲህ ዓይነት አለመረጋጋቶች ምክንያት የሆኑትን ችግሮች ለይቶ ማስቆም አለመቻሉም ሌላ ችግር ሆኗል፡፡ እንደ ሕዝብም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን ያህል ጥረናል የሚለውም ጥያቄ መዘንጋት የለበትም፡፡

ያም ሆነ ይህ እንዲህ ያሉ አለመረጋጋቶች አገሪቷን ዋጋ እያስከፈሏት ነው፡፡ በአለመረጋጋቶቹም የሰው ሕይወት እየጠፋና አካል እየጎደለ ነው፡፡ በየአካባቢው እየጠፋ ያለውም ንብረት በድህነት ውስጥ ላለች አገር ቀላል ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ በትንሹም በትልቁም ግጭት ዜጎች መሞት የለባቸውም፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ዋናው ጉዳይ በግጭቶች ምክንያት ዜጎች መሞት አይገባቸውም የሚለው ቢሆንም፣ አለመረጋጋቶቹ ግን እየፈጠሩ ያሉት ቀውስ የሰው ሕይወት ከመንጠቅ ባሻገር አገር በስንት መከራ ያፈራችውን ሀብት እያሳጣ ነው፡፡ በተጨማሪም ለሌላ ማኅበራዊ ቀውስ መንስዔ እየሆነ መምጣቱ ያሳስባል፡፡ እጅጉኑም ደግሞ የኢኮኖሚውን እያንገራገጨውም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጤናማ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እንዳይኖር በማድረጉ ረገድም እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሰላም በሌለበት  ጤናማ ኢኮኖሚ ለመገንባት አይቻልም፡፡ አለመረጋጋቱ ጤናማ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችንም በእጅጉ እየጎዳና ሥጋት አልባ የቢዝነስ ድባብ እንዳኖር ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ዛሬ የምናየው የኑሮ ውድነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንዱ ምክንያት ይኸው አለመረጋጋትና በየአካባቢው የሚፈጠር ግጭት ነው፡፡ ምን ይመጣብኝ ይሆን የሚል ፍራቻ ይዞ መነገድና ከቦታ ቦታ መዘዋወር ከባድ በሆነ ቁጥር ኢኮኖሚውም አብሮ ይታመማል፡፡ አለመረጋጋቱ የሚፈጥረው ቀውስ የንግድና የቢዝነስ እንቅስቃሴውን በገታ ቁጥር ደግሞ፣ በገበያ ውስጥ የሚፈጠረው የዋጋ ንረት የግብይት ሥርዓቱን እየረበሸና የሸማቾችን አቅም እየፈተነ ብሶታቸውን ያብሳል፡፡

አጋጣሚውን በመጠቀም ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው እንቅስቃሴም ዘለግ ብሎ መታየቱ የዋጋ ግሽበቱን የበለጠ ሊያንረው እንደሚችል ያሠጋል፡፡ በቅርቡ እያየን እንዳለነው አንዳንድ ምርቶች የዋጋ ማሻቀብ ሲታይባቸው አለመረጋጋቱ የፈጠረው ነው እየተባለ፣ ችግሩ ከተፈታ በኋላም በሰበብ የተጨመረው ዋጋ በዚያው ይቀጥላል፡፡ በአንድ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረ ችግር የዋጋ ጭማሪ የተደረገበት ምርት ወይም ሸቀጥ ችግሩ ከተቀረፈ በኋላም በዚያው ለምን ይቀጥላል ብሎ የሚጠይቅም የለም፡፡ በአንድ ሰበብ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ምርት ችግሩ ሲቀረፍ ወደ ቦታው ያለመመለሱ ወይም በገበያ ዋጋ አለመመራቱ የኑሮ ውድነቱን ያብሳል፡፡ ይህ ፍጹም የገበያ መርህን የሚያፋልስ አጉል ልማድ ያለ ከልካይ መቀጠሉም፣ ወትሮም ኑሮ የተጫነውን ሸማች የበለጠ እንዲማረር እያደረገ ነው፡፡

አገር ያለችበትን ችግር ዓይቶና ነገሮች ሊያልፉ እንደሚችሉ ገምቶ ገበያን ለማረጋጋትና ትርፉን መጥኖ ለመነገድ በጎ ፍላጎት የሌለው ነጋዴ በበዛ ቁጥር ደግሞ ችግሩ ሥር እንዲሰድ ያደርጋል፡፡ እንዲህ ያለው ክፉ አመል በሥነ ምግባር የሚሠሩትንም እየበረዘ ስለመሆኑ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ንግድ በአጋጣሚ የሚከበርበት አድርጎ የመመልከት ልማድ ሄዶ ሄዶ እንደ አገር ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ በመገንዘብ መተሳሰብ ካልተቻለ፣ ችግሩ እየሰፋ ገበያውም ከመስመር ሊወጣ ይችላል፡፡

በእርግጥ እዚህም እዚያ የሚነሱ ግጭቶች ወይም ሆን ተብሎ የሚለኮሱ እሳቶች የተረጋጋ ቢዝነስ እንዲኖር አያደርጉም፡፡ የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም አለመረጋጋቶችንና ሆን ተብሎ የሚፈጸሙ ግጭቶችን ምክንያት በማድረግ፣ በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጥፋት ሳያንስ አጋጣሚውን ስንጥቅ ትርፍ ለማትረፍና ኪስን ለመሙላት መጠቀም ከበደሎች ሁሉ ይብሳል፡፡ እንደውም አለመረጋጋቱን ከሚፈጥሩት አካላት ያልተናነሰ ወንጀል ተደርጎም መወሰድ አለበት፡፡ ስለዚህ በአለመረጋጋት ስም የሚፈጸም ያልተገባ የገበያ ሥርዓት ገበያውን የበለጠ ከመበረዙ በፊት፣ በዚህም ጉዳይ ሕግ ይከበር እንዲሁም ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር ሁሉም የበኩሉን ይወጣ ማለት ያስፈልጋል፡፡

በተለይ ወቅቱ አዳዲስ ምርት ወደ ገበያ የሚወጣበት በመሆኑ፣ በርካታ ምርቶች በእጥረት ሰበብ ዋጋ የሚሰቀልባቸው ሳይሆኑ ቀንሰው የሚሸጡበት ሊሆኑ ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡም በገበያ ዋጋ የመሸመት መብቱ እንዳይነጠቅ መሠራት አለበት፡፡ ገበያ ከማረጋጋትና ያልተገባ የንግዱ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት በዚህ ጉዳይ ዓይናቸውን ገልጠው መሥራት ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡

አዘውትረን እንደምንናገረውና መንግሥትም በሚገባ እንደሚያውቀው የደላሎች እንቅስቃሴን መገደብ ያሻል፡፡ በዚህ ወቅት ዋጋቸው ይቀንሳሉ የተባሉ ምርቶችን በመያዝ ዋጋው እንዳይረጋጋ ሊያደርጉ መቻላቸውን በመገንዘብ ቁጥጥርን ማድረግ ይገባል፡፡ በአለመረጋጋቱ ሳቢያ ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጽንፈኞችን ብቻ ሳይሆን በግብይት ውስጥ ነውጥ የሚፈጥሩትና ሆን ብለው ገበያውን ለማመስ የሚጥሩት ላይም ዕርምጃ ይወሰድልን፡፡

ከግብይት ጤናማነት አንፃር በቅርቡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በወጪ ንግድ ላይ ሲፈጸም የነበረውን ሸፍጥ በመረዳት፣ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት አዲስ አሠራር በመዘርጋት ቁጥጥሩን ለማጥበቅ እንደጀመረው ሥራ ሁሉ የአገር ውስጥ ግብይትና ወቅታዊውን ሁኔታ ያገናዘበ አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ዜጎች ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይጎዱ ለማድረግ በተለይ በዚህ ወቅት ገበያውን በመመልከትና በመቆጣጠር የሚሠራው ሥራ ውጤት ይኖረዋል፡፡

በዚህ አዲስ ምርት በሚገባበት ወቅት አማካይ የግብይት ዋጋዎችን በማሳወቅና ሸማቾች ባልተገባ ዋጋ እንዳይበዘበዙ መረጃ የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠርም የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የሸቀጣ ሸቀጥ የመሸጫ ዋጋቸውን በቀላሉ ከገበያ ዋጋ በላይ መሆን አለመሆናቸውን ለመለየት የሚቻልበት በርካታ አማራጮች እንዳሉ በመገንዘብ፣ በኢኮኖሚው ረገድም የሚፈጸመውን ሕገወጥ ተግባር መንግሥት ያስታግስልን፡፡ ኅብረተሰቡን የራሱን ድርሻም ይወጣ፡፡ በተለይ ደግሞ ነጋዴዎቻችን ከክፉ አመል ይቆጠቡልን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት