Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ የኤሌክትሮኒክ የበረራ ትኬት መቁረጫ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቢሲኒያ ባንክ ጉዞ ጎ ከተባለ የኤሌክትሮኒክ የጉዞ ወኪል ድርጅት ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ የበረራ አገልግሎት ከሚሰጡ አየር መንገዶች የበረራ ቲኬት መቁረጥ የሚያስችል አዲስ አሠራር ሊጀምር መሆኑ ተገለጸ፡፡ ይህንኑ አገልግሎት በሞባይል መተግበሪያ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ባንኩ ከጉዞ ጎ ጋር በጋራ ለመሥራት ያሰበውን አዲስ አገልግሎት በተመለከተ ባለፈው ማክሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሠሩ የአየር መንገዶች የበረራ ቲኬት መቁረጥ የሚያስችለው አገልግሎት የተለያዩ አማራጮችን የያዘ ነው፡፡

ደንበኞች በአቅራቢያቸው በሚገኝ በየትኛውም የአቢሲኒያ ባንክ ቅርንጫፍ በመገኘት የሚሄዱበትን አገር፣ መጓዝ የሚፈልጉበትን የበረራ ዓይነትና የጉዞውን ቀን በማሳወቅ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል፡፡ አገልግሎቱ ደንበኛው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚሠሩ ሁሉም አየር መንገዶች ውስጥ ያሉትን አማራጮች በተለያዩ መመዘኛዎች በመፈተሽ የተሻለውን ቲኬት መቁረጥ የሚያስችል ነው፡፡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አዲስ አሠራር ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ስለመሆኑ የጠቆሙት የጉዞ ጎ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው፣ የአገልግሎቱ አሰጣጥ በተለየ የሚታይበት የተለያዩ መገለጫዎች አሉት ብለዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ደንበኞች የቀረቡላቸውን የአየር መንገድ አማራጮች በዋጋ፣ በመነሻና መመለሻ ቀናት፣ በአገልግሎት ምቾትና፣ የሚወስድባቸውን የበረራ ሰዓት ከግምት በማስገባት በመረጡት አየር መንገድ ለመጓዝ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡ በባንኩ በየትኛውም ቅርንጫፍ ሆኖ አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ከሒሳባቸው ተቀናሽ በማድረግ ወይም በካሽ ክፍያ በመፈጸም የአየር ቲኬት ሽያጭ የሚያገኙበትም ነው ተብሏል፡፡

በቅርቡም ጉዞ ጎ በሚጀምረው ተጨማሪ አገልግሎት የባንኩ ደንበኞችም ሆኑ ሌሎች የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም አገልግሎቱን የሚያገኙበትን አሠራር እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች በሞባይል ስልካቸው በረራዎችን የሚከታተሉበት፣ በኦንላይን ክፍያ የሚፈጽሙበትና ኤሌክትሮኒክስ ቲኬት የሚቀበሉበትን የሚያመቻች መሆኑን ይኸው መግለጫ ያመለክታል፡፡ የጉዞ ጎ መተግበሪያ በኢትዮጵያ አቆጣጠር እንዲሠራ ሆኖ የተሰናዳ ሲሆን በአማርኛ፣ በኦሮሚኛና በትግራኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ስለመሆኑም ታውቋል፡፡ ጉዞ ጎ የክፍያ አማራጮችን በኢንተርኔት ባንኪንግ ለማቅረብ ሥራውን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ሥራውን ለማስፋትም ከውጭ ቋንቋዎች ቻይንኛ በዚሁ መተግበሪያ እንዲካተት ይደረጋል ብለዋል፡፡ ይህንን የጉዞ ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅም እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡

ጉዞ ጎ የጉዞ ቴክኖሎጂዎችን ለአቢሲኒያ ባንክ ሲያቀርብ ባንኩ አጠቃላይ የጉዞ ክፍያዎችን የመሰብሰብና የሒሳብ ሥራውን የመሥራት ኃላፊነት ይኖርበታል ተብሏል፡፡ የጉዞ ጎ ሥራ አስኪያጅ አቶ በሱፍቃድ ጌታቸው በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በሞባይል መተግበሪያ የሁሉም የአየር መንገዶችን ቲኬት መቁረጥ የሚያስችለው ቴክኖሎጂ በበረራ ኢንዱስትሪው ላይ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችላል ብለዋል፡፡

የሞባይል መተግበሪያው ስለሚለይበት ነገር ሲያብራሩ፣ የሁሉንም አየር መንገዶች ቲኬቶችን በአንድ ቋት መያዙና ደንበኞች በምርጫ የሚፈልጉትን አየር መንገድ ቲኬት እንዲያገኙ ማድረጉ አንዱ ነው፡፡  

በአቢሲኒያ ባንክ የጉዞ ጎ የአየር ቲኬት ሽያጭ የሚከናወንላቸው ደንበኞች የባንኩን የተለያዩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚበረታቱ ሲሆን፣ ለተቀዳሚ ደንበኞችም በብድር የበረራ ቲኬት መግዛት የሚችሉበትን አማራጭ ማቅረቡም አገልግሎቱን የተለየ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ በሌሎች አገሮች ሰዎች ደመወዛቸውን ከባንክ ጋር በማገናኘት የሚፈልጉትን ነገር በዱቤ ለመውሰድ ይችላሉ ያሉት አቶ በሱፍቃድ፣ እንዲህ ዓይነት አገልግሎቶችን በአገራችን ማስለመድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በአዲሱ አገልግሎት በአቢሲኒያ ባንክ የበረራ ቲኬት በመግዛት የሚደረግ በረራ የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተገልጿል፡፡ ለምሳሌ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ቲኬት ይጠፋብኛል የሚለውን ሥጋት የሚያስቀርለትና በረራ የመሰረዝና በድጋሚ ቦታ ማስያዝ የሚችልበት አሠራር ያለው መሆኑ፣ አገልግሎቱን በተለየ እንዲታይ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ ተጓዦች በአንድ አየር መንገድ የቆረጡትን ቲኬት በመሰረዝ በወረቀት የታተመ የቲኬት ማረጋገጫ ሳያስፈልግ ወደ ሌላ አየር መንገድ የሚቀይሩበት ዕድል ያለው መሆኑን የሚጠቁመው የኩባንያዎቹ መረጃ፣ ደንበኞች ከደኅንነት አኳያ ቲኬት መግዣ ገንዘብ ይዘው መዘዋወርን ያስቀርላቸዋል ተብሏል፡፡ ይህንን አገልግሎት በሁሉም ቅርንጫፎች ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉን የገለጹት የአቢሲኒያ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ወሰንየለህ አበራ፣ በተለይ የአየር በረራ አገልግሎት ባሉባቸው ከተሞች ያሉ የባንኩ ቅርንጫፎች ውስጥ በልዩ የመስኮት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ይሆናል ብለዋል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ባሉት የባንኩ ቅርንጫፎችም ሙሉ ለሙሉ ለዚሁ አገልግሎት የተዘጋጁ መስኮቶች የተከፈቱ ስለመሆኑም አቶ ወሰንየለህ ገልጸዋል፡፡ 

የሞባይል መተግበሪያው በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሠራ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነት ፈጠራዎችን ተቀብሎ ለመተግበር የአቢሲኒያ ባንክ ያሳየውን ፈቃደኝነት አቶ ቴዎድሮስ አወድሰዋል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ቀዳሚ የግል ባንኮች አንዱ ሲሆን፣ ከታክስ በፊት ዓመታዊ ትርፋቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካደረሱ ጥቂት ባንኮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች