ኅብረት ኢንሹራንስ በ2011 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የዓረቦን ገቢውና የትርፍ መጠኑን ቢያሳድግም፣ የወጪና ገቢ ንግድ መቀዛቀዝ በማሪን የመድን ሽፋን ገቢው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገለጸ፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ የ2011 የሒሳብ ዓመት ክዋኔውን ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ እንዳመለከተው፣ በሁሉም የመድን ሽፋኖች ያገኘው የዓረቦን ገቢ የ13 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይህ የዓረቦን ገቢ ዕድገት በአጠቃላይ በአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ካስመዘገበው የስድስት በመቶ አማካይ ዕድገት አንፃር ሲነፃፀር፣ በጣም አበረታች እንደሆነም የኅብረት ኢንሹራንስ የዳሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሙሉዓለም ብርሃኔ ገልጸዋል፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከባህርና ከየብስ ጉዞ የመድን ሽፋን ዓይነቶች ውጪ በሁሉም የኢንሹራንስ ዘርፎች የዓረቦን ገቢ ዕድገት የታየበት እንደነበርም አመልክተዋል፡፡ የባህርና የየብስ ጉዞ መድን ሽፋን የዓረቦን ገቢ አነስተኛ ሊሆን የቻለው በአገሪቱ የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ የታሰበውን ያህል ስኬታማ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሆነ የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ከእነዚህ ሁለት ዘርፎች የሚገኘው የዓረቦን ገቢም በገቢና ወጪ ንግድ ዕድገት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የተፈጠረ እንደሆነም የቀረበው ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በአጠቃላይ በአገሪቱ ከነበረው የንግድ መቀዛቀዝ ሁኔታና ከኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ካስመዘገበው አማካይ የዓረቦን ገቢ ዕድገት አኳያ ሲታይ፣ በኩባንያው የተመዘገበው የዓረቦን ገቢ ዕድገት በተነፃፃሪ የተሻለ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ከኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት መገንዘብ እንደተቻለውም ኅብረት ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ በጥቅል ማሰባሰብ የቻለው የዓረቦን ገቢ 533.5 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው የዓረቦን ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ13 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
ኩባንያው በ2011 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የከፈለው የካሳ ምጣኔ ከቀዳሚው ዓመት ከነበረው 86 በመቶ ቅናሽ በማሳየት 60 በመቶ ሆኖ የተመዘገበበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ይህም በቀዳሚ ዓመት ከተከፈለው የካሳ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር በ12 በመቶ የተሻለ ውጤት የታየበት መሆኑም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ውጤታማነት ከሚለካባቸው መመዘኛዎች አንዱና ዋነኛው ከቀጥታ የመድን ዘርፍ ወይም ከኦፕሬሽን የሚገኝ ትርፍ ሲሆን፣ ኩባንያው በ2011 የሒሳብ ዓመት ካገኘው 173.4 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ44 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት ነው ተብሏል፡፡
በዓረቦን ዕድገትና ለካሳ ክፍያው የዋለው ገንዘብ ቅናሽ ማሳየቱ የኩባንያውን ትርፍ ያሳደገለት ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢውም በ2011 ሒሳብ ዓመት ከግብር በፊት 121.17 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያገኘ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ዓመታዊ ትርፍ ውስጥ 40 ሚሊዮን ብር ከረዥም ጊዜ ወይም ሕይወት ነክ የመድን ዘርፍ የተገኘ ትርፍ መሆኑም ታውቋል፡፡ ይህም ኩባንያው በራያ ቢራ የነበረውን የአክሲዮን ድርሻ በመሸጥ ያገኘው ገቢ ተቀንሶ ሲታይ አምና በተመሳሳይ ጊዜ ከተገኘው ትርፍ 55 በመቶ ብልጫ ያለው እንደሆነ አቶ ሙሉዓለም ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡
ኅብረት ኢንሹራንስ በተዘጋው የሒሳብ ዓመት አንድ አዲስ ቅርንጫፍና ሦስት አገናኝ ቢሮዎችን የከፈተ ሲሆን፣ ይህም ኩባንያው አጠቃላይ ያሉትን ቅርንጫፎች ብዛት ቁጥር ወደ 50 ያደርሰዋል፡፡ ኩባንያው የገበያ ድርሻውን እያሳደገ ለመሄድ በያዘው ዕቅድ መሠረት አዋጭነታቸው በጥናት የተረጋገጡ ቅርንጫፎችን ከመክፈት በተጨማሪ፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 20 አዳዲስ የሽያጭ ወኪሎችን በማሠልጠን ወደ ሥራ ማስገባቱም ተገልጿል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ በተለየ ከውኛለሁ ብሎ ከጠቀሳቸው ተግባራቱ ውስጥ በተወሰኑ የመድን ዘርፎች የኦንላይን ሽያጭ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ነው፡፡ ይህንን የኦንላይን የመድን ሽያጭ በየጊዜው እያሻሻለ አጠናክሮ የቀጠለ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡
ኩባንያው 387 ሠራተኞች ሲኖሩት፣ ለሰው ኃይል ሥልጠናና ልማትም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ለ172 ሠራተኞች የተለያዩ የሙያና የአመራር ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ለዚህም 2.5 ሚሊዮን ብር ወጪ አውጥቷል፡፡ ሥልጠና እንዲያገኙ ከተደረጉት ሠራተኞች መካከል 13 ከኢትዮጵያ ውጭ ሄደው ሥልጠና እንዲወስዱና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ 159 ሠራተኞች በአገር ውስጥ ሥልጠና እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡ በዚህ ረገድ ኩባንያው እያካሄደ ያለው የሰው ኃይል ልማት ሥልጠና ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ የሚካሄደው የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቁ፣ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ለዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ኪራይ ያወጣ የነበረውን ወጪ ማስቀረቱን ጠቅሰዋል፡፡ ኩባንያው በቀጣይም በቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን በስተጀርባ በሚገኘው ቦታና በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው ቦታ ላይ ተጨማሪ ግንባታዎችን ለማከናወን እንዳቀደም ተገልጿል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ በቀደመው ዓመት የኩባንያው ካፒታል ከ250 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ካፒታሉ እያደገ ስለመምጣቱ ታውቋል፡፡ እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስም ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታል መጠኑ 375.5 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ኩባንያው 478 ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡