Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሒጅራ ባንክ ለምሥረታ የሚያበቃውን የተከፈለ ካፒታል ማሟላቱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወለድ የማይታሰብበት የባንክ አገልግሎት ለመስጠት በምሥረታ ላይ የሚገኘው ሒጅራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ ባንክ ለመመሥረት የሚያስችለውን ካፒታል እንዳሟላ አስታወቀ፡፡

ባንኩ የካፒታል መጠኑን እንዳሟላ ይፋ ባደረገበት መግለጫው የባንኩ አደራጆች እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ሲያሰባስብ የተፈረመ ካፒታሉንም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

ቅዳሜ ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው የአክሲዮን ሽያጭ መዝጊያ የምሥጋና ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው፣ ባንኩን ሥራ ለማስጀመር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ስለባንኩ የወደፊት አቅጣጫዎች በባንኩ መሥራቾችና ባለሙያዎች ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው የሚታዩ ክፍተቶችን መነሻ በማድረግ አዋጭ የተባሉ የባንክ አገልግሎቶችን በመለየት መስኩን ለመቀላቀል እንደተዘጋጀ ተብራርቷል፡፡

በኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችሉ ዕርምጃዎች መወሰድ መጀመራቸውን የሒጅራ ባንክ አደራጆች ይገልጻሉ፡፡ የበርካታ ዓመታት ጥያቄ ሆኖ የቆየው አካታች የፋይናንስ ሥርዓት እንዲተገበር የሚያስችል ዕድልን በመፍጠር፣ አገር አቀፍ ለውጡ በፋይናንስ ዘርፉም ይታይ የነበረውን ክፍተት ለማሻሻልና ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ የሚያስችል እንቅስቃሴ የለውጥ ሒደቱ እንደፈጠረም ተጠቅሷል፡፡

ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ሥርዓትን በማስፈን፣ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ዝቅተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየውን ሰፊ የኅብረተሰብ ክፍል፣ በኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት ውስጥ አዎንታዊ ሚናና ድርሻ እንዲኖረው ለማስቻል ባንኩ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

ባንኩ በምሥረታ ሒደቱ እንዳከናወነ ከጠቀሳቸው መካከል ከሒጅራ ባንክ በተጨማሪ ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸውን ባንኮች ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ አካላት ጋር በመነጋገር ወደ ውህደት እንዲመጡ ማድረግ መቻሉ ነው፡፡ ሌሎች ወለድ አልባ ባንኮችን በማደራጀት ሒደት ላይ ከነበሩት ጋር ውይይቶችና ምክክሮች በማካሄድ  ውህደት እንዲፈጠር መደረጉና ተጨማሪ ሥራዎች መሠራታቸው ተብራርቷል፡፡

በምሥረታ ላይ የሚገኘው ሒጅራ ባንክ በአገልግሎቱ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ለማስተካል ሥራ መሥራቱንም አስታውቋል፡፡ ለዚህ እንዲረዳም በተለያዩ ክልሎች ከአርባ በላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዳካሄደ ጠቅሷል፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብ በአፋር፣ በሶማሌ ክልሎች፣ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በተለያዩ ከተሞችና ዞኖች ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡

ሒጅራ ባንክ አካታች የፋይናንስ ሥርዓትን በማዘመን ከፋይናንስ ተቋማት የራቀውን የኅብረተሰብ ክፍል የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተዋናይ እንዲሆን ማስቻልና የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎች የሆኑትን ዘርፎች በማጤን በግብርና፣ በእንስሳት ሀብትና በቱሪዝም መስኮች ላይ፣ እንዲሁም በአገራችን አረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴዎች ላይ የጎላ ተሳትፎ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

የባንኩ መግለጫ ጨምሮ እንዳመለከተው ይህ ዘርፍ እያገኘ ያለው መንግሥታዊ ድጋፍና ዕገዛ ተጠናክሮ ከቀጠለ ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስመዝገብና ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ እንደሆነ የሚነርለት የዜጎች በፋይናንስ ተቋማት የመሳተፍ ሒደት አሁን ከሚገኝበት 35 በመቶ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ የተያዘውን ብሔራዊ ዕቅድ ተፈጻሚ እንደሚያደርግ ይታመናል በማለት ባወጣው መግለጫ አስፍሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት በምሥረታ ላይ ከሚገኙት መካከል ዘምዘም ባንክ ለመመሥረት የሚያስችለውን ካፒታል በማሟላት ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች