የአረንጓዴ ማሾ ግብይት በምርት ገበያ በኩል ብቻ እንዲካሄድ በመወሰኑ የግብይት መጠኑን በ20 በመቶ እንዳሳደገውና በአንድ ወር ውስጥ ብቻም 168 ሚሊዮን ብር ሽያጭ መመዘገቡን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ፡፡
ምርት ገበያ እንደገለጸው፣ የአረንጓዴ ማሾ የግብይት መጠን እያደገ በመምጣቱ ከመስከረም ወር ብልጫ ያለው ምርት ለማገበያየት አስችሏል፡፡ በዚሁ መሠረት በጥቅምት ወር ብቻ 6,046 ቶን የአረንጓዴ ማሾ ለገበያ ቀርቦ ነበር፡፡ የግብይት መጠኑም 168 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህ የግብይት መጠን ከመስከረም ወር አኳያ በ19 በመቶ በዋጋም የሰባት በመቶ ለውጥ አሳይቷል፡፡
እንደ አረንጓዴ ማሾ ሁሉ ግብይቱ አስገዳጅ የሆነው ቀይ ቦሎቄም በጥቅምት ወር 190 ኩንታል ቀርቦ በ184 ሺሕ ብር መገበያየቱን የሚጠቁመው የምርት ገበያው መረጃ፣ እነዚህ ምርቶች ቀጣዮቹ ወራት የምርት ጊዜ በመሆኑ በስፋት ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠቁም ገልጿል፡፡
ከእነዚህን ምርቶች ሌላ በአጠቃላይ የምርት ገበያው የጥቅምት ወር የግብይት ሁኔታን በተመለከተው መረጃ ደግሞ በ23 የግብይት ቀናት 21,034 ቶን ቡና፣ 9,434 ቶን ሰሊጥ፣ 6,534 ቶን አኩቲ አተርና 1,327 ቶን ነጭ ድቡልቡል ቦሎቄ አገበያይቷል፡፡ ይህም አጠቃላይ የወሩ ግብይት 2.16 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው መሆኑን ነው፡፡
በወሩ ውስጥ ከተካሄደው ግብይት ቡና 47 በመቶውን ይዟል፡፡ የግብይት ዋጋውን ደግሞ 67 በመቶ በመያዝ ቡና ቀዳሚ ነው፡፡ በሁሉም የቡና ዓይነቶች በተፈጸመ ግብይት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና የግብይት መጠኑንና ዋጋውን 66 በመቶና 65 በመቶ በመያዝ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ 13,947 ቶን ያልታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ938.2 ሚሊዮን ብር፣ አሥር ቶን የታጠበ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በ588.1 ሺሕ ብር ተገበያይቷል፡፡ ለአገር ውስጥ የሚቀርብ 6,309 ቶን ቡና በ432.78 ሚሊዮን ብር፣ 767 ቶን ስፔሻሊቲ ቡና በ71.14 ሚሊዮን ብር ግብይታቸው ተከናውኗል፡፡
እንዲሁም የሰሊጥ ግብይት ካለፈው ወር ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠንና በዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በምርት ገበያው መረጃ መሠረት የጥቅምት ወር የሰሊጥ የግብይት መጠን በ136 በመቶ እንዲሁም የግብይት ዋጋው በ88 በመቶ ጨምሯል፡፡ በወሩ ውስጥ 9,434 ቶን ሰሊጥ በ419.75 ሚሊዮን ብር ተሸጧል፡፡ ሁመራ/ጎንደር በግብይት መጠንና ዋጋ 61 እና 66 በመቶ በመያዝ አንደኛ ደረጃ ይዟል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የሰሊጥ ግብይት በመጠን የ26 በመቶ ጭማሪ ሲጨምር፣ በዋጋ ደግሞ የ32 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ወደ ምርት ገበያው ከሚገቡ ምርቶች የምርት መጠኑ እየጨመረ መሆኑ የተጠቀሰው ሌላው ምርት አኩሪ አተር ነው፡፡ በጥቅምት 2012 ዓ.ም. 6,534 ቶን አኩሪ አተር በ105.88 ሚሊዮን ብር እንደተገበያየ ታውቋል፡፡ የዚህ ምርት ግብይት አኩሪ አተር ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር አማካይ ዋጋው በ12 በመቶ ጨምሯል፡፡ በተጨማሪም 1,346 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ28.3 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ካለፈው ወር ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በግብይት መጠን 57 በመቶ፣ በግብይት ዋጋ 39 በመቶ ከፍ ስለማለቱም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ገልጿል፡፡