Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

እየጨመረ የመጣው የሳይበር ጥቃት ትኩረት ይሻል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሳይበር ጥቃት ጋር በተያያዘ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ጉዳዩን በትኩረት እንድናስብበት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶች እየበዙ ሲመጡ ይዘው የሚመጡት ሥጋትም ቀላል ባለመሆኑ፣ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም እየተደረገ ያለውን ትጋት ያህል አደጋ ቢደርስስ ብሎ ቀድሞ ማሰብ የግድ እንደሚሆን ያሳያል፡፡

ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ሰሞኑን በተከታታይ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ የሳይበር ጥቃቱ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሄዱ ብቻ ሳይሆን ጥቃቱ የጨመረበት መጠን ከፍተኛ መሆኑ ያሳስባል፡፡ በአጭር አገላለጽ ባለፉት ስድስት ዓመታት የጥቃቱ መጠን በ13 ዕጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን የኤጀንሲው አኅዛዊ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

አኅዛዊ መረጃው በዝርዝር ሲታይም በ2005 ዓ.ም. 59 የነበረው ዓመታዊ የሳይበር ጥቃት፣ በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 791 ደርሷል፡፡ ይህም የጥቃቱ መጠን በምን ያህል ደረጃ እንደጨመረ የሚያሳይና አገሪቱም በዚህ ጉዳይ ላይ ሊገጥማት የሚችለው ችግር ከወዲሁ በሚገባ ካልታሰበበት የከፋ አደጋ ሊያመጣ እንደሚችልም የሚጠቁም ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሳይበር ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል ተብለው ከሚታመኑትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎት ይሰጣሉ ከሚባሉት ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮምን በምሳሌነት መጥቀስ ይችላል፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማቶቻችንም በተመሳሳይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮችንም እያጎለበቱ ነው፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄው በሁሉም ደረጃ መሆኑን ያሳያል፡፡ በይበልጥ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዚህ ጥቃት ሰለባ ለመሆን ተጋላጭነታቸው ገዝፎ የሚታየው ባንኮች ናቸው፡፡ የአገራችን ባንኮች ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ መሠራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ የሚታሰብ ከሆነ ደግሞ፣ የቅድሚያ ቅድሚያ በእነዚህ ተቋማት ላይ ማተኮርን ይጠይቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፋይናንስ ኢንዱስትሪው በምንም መለኪያ ቢሆን ወረቀት አልባ ወደ መሆን እየተሸጋገረና እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ቴክኖሎጂው የሚጠይቃቸውን አዳዲስ አሠራሮች እየተከተሉ መሆኑ ለሳይበር ጥቃቱ ያላቸውን ተጋላጭነት ከፍ ያደርገዋል፡፡

ባንኮች ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን መሠረተ ልማት ለመዘርጋት ከፍተኛ መዋለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሆነም እየተመለከተ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ቢሆን አገልግሎታቸው ከዚህ ቴክኖሎጂ ውጭ የማይወጣ በመሆኑ ብዙ ኢንቨስትመንት ይጠይቃቸዋል፡፡ ስለዚህ በትንሽ ስህተት በርካታ ነገሮችን ሊያጡ የሚችሉበት የሳይበር ጥቃት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ወንጀልና አደጋ ለመጠበቅ የግድ ጥቃቱን ለመከላከል በሚያስችል ደረጃ መሠረተ ልማታቸውን ማጠናከርና ሁነኛ ባለሙያዎችን ማሰማራትን ይጠይቃል፡፡

የወንጀሉ ተለዋዋጭነት የረቀቀና በየጊዜው የሚቀየር ከመሆኑ አንፃር ባንኮቻችንና ሌሎች አብዝተው ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ኩባንያዎቻችን የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችላቸው ሥራ ላይ በይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያስገድድ ሆኗል፡፡

ከሰሞኑ የሳይበር ጥቃት ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ እንደተገለጸው፣ ችግሩን አሳሳቢ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ እንዲህ ያለ ጥቃት ይመጣል ተብሎ ኩባንያዎች በቂ የሆነ ዝግጅት አለማድረጋቸው አንዱ ነው፡፡ በዘርፉ ያለው የሠለጠነ የሰው ኃይልም ተግዳሮት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ይህን የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ራሱን የቻለ የትምህርት ፕሮግራም በከፍተኛ ተቋማት ውስጥ አለመኖሩም ተጠቃሽ ነው፡፡ ስለዚህ ቴክኖሎጂውን አስፍተን እየተጠቀምን ባለበት ወቅት እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ከወዲሁ መዘጋት አለባቸው፡፡

እንዲህ ያሉ እውነታዎችና በጥቂት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው ጥቃት፣ ነገ ተነገ ወዲያ የሕዝብ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱት ባንኮች ላይ አደጋ ከማድረሱ በፊት ከወዲሁ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲወሰድ ይጠቁማል፡፡ ተቋማት ከጊዜው ጋር የሚሄድ ባለሙያዎችን በማፍራትና የመከላከል አቅምን የሚያጎለብቱ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ቋሚ የሆነ በጀት በመያዝ መንቀሳቀስም ይኖርባቸዋል፡፡ ከአገራችን የፋይናንስ ተቋማት ሕግጋቶች ውስጥ አንዱ ተቋማቱ ከዓመታዊ በጀታቸው የተወሰነውን ለሠራተኞች ሥልጠናና አቅም ማጎልበቻ እንዲያውሉ የሚያስገድድ ሲሆን፣ እነዚህ ተቋማት ራሳቸውን ከሳይበር ጥቃቶች ለመከላከል በቂ ሥራ እየሠሩ ስለመሆኑ አስገዳጅ ሕግ ሊኖር ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከሌሎች በተለየ እነዚህ ተቋማት የያዙት የአገርና የሕዝብ ሀብት ከመሆኑ አንፃር፣ በሳይበር ጥቃት ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ወይም ለማስቀረት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ሊረባረቡበት ይገባል፡፡ ለዚህም አንዱ አስተማማኝ ጥበቃ እንዲደረግ አስገዳጅ ሕግ ማውጣት ነው፡፡ የሕዝብ ሀብትን ለመጠበቅ ሲባል መሆንም ያለበት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሳይበር ጥቃት ዙሪያ እየተደረጉ ካሉ የተለያዩ ፕሮግራሞች አንዱ በሆነው ላይ በቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በኩባንያዎች ከሚደርስባቸው ጥቃቶች መካከል 45 በመቶ የሚሆኑት በኩባንያው ሠራተኞች የሚፈጸም መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ በመሆኑም ኩባንያዎች የሠራተኞቻቸውን መልካም ሥነ ምግባር ማረጋገጥ ግድ ይላቸዋልና በዚህም ዙሪያ ብዙ መሥራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ይጠቁማል፡፡

ከሰሞኑ ከቀረቡት ጥናቶች መረዳት የሚቻለው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ በርካታ ኩባንያዎች እንደ ክፍተት ያስቀመጧቸው የተለያዩ ነጥቦች አሉ፡፡ በተለይ በሳይበር ጥቃት ለሚፈጸም ጉዳት ሊመጥን የሚችል የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲጀመር ከወዲሁ ማሰቡም በተወሰነ ደረጃ ችግሩን ለመከላከል ያግዛል፡፡ ስለዚህ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ከሚያደረገው ጥረት ባሻገር፣ ኩባንያዎቹም በራሳቸው ጥንቃቄ ሊያደርጉ ግድ ይላቸዋል፡፡

በተለይ የፋይናንስ ተቋማትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ አዳዲስ ማሻሻያ እያደረገባቸው ካሉት አዋጆች መካከል ዲጂታል አገልግሎቶች በተለያዩ ደረጃ ሥራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ያካተታቸው አንቀጾች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አገልግሎት ጋር ግን እንዴት ጥበቃ ይደረግ የሚለው ላይ ምንም ያለው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ በቀጣይ መመርያዎቹ ተቋማት ከሳይበር ጥቃት የሚጠበቁበትን ድንጋጌ እንጠብቃለን፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች