Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው ለሚጀምረው የቴሌቪዥን ጣቢያ በኢቢሲ ማሠራጫ በኩል ለመጠቀም ስምምነት መደረሱ ታወቀ

ፓርላማው ለሚጀምረው የቴሌቪዥን ጣቢያ በኢቢሲ ማሠራጫ በኩል ለመጠቀም ስምምነት መደረሱ ታወቀ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በራሱ የሚያስተዳድረው የቴሌቪዥን ጣቢያ የስቱዲዮ ግንባታ እየተጠናቀቀ በመሆኑ፣ በሳተላይት አማካይነት ማሠራጨት የሚያስችለውን የምድር  ማሠራጫ መሣሪያ (Earth Station) በኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በኩል ለመጠቀም ስምምነት ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመገንባት ላይ ያለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ምክር ቤቱ የሚያካሄደውን መደበኛ፣ አስቸኳይ ወይም ልዩ ስብሰባዎችን፣ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባዎችና ከምክር ቤቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መረጃዎችና ዝግጅቶችን በዋናነት በቀጥታ ሥርጭትና በስቱዲዮ ዝግጅቶች ትኩረት አድርጎ ለሕዝብ ለማድረስ በሚል ዓላማ የተቋቋመ መሆኑን፣ ሪፖርተር ከኃላፊዎችና በግንባታው ሥራ ላይ እየተሳተፉ ካሉ ባለሙያዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

በምክር ቤቱ ዋና የመሰብሰቢያ አዳራሽና የአፈ ጉባዔው ቢሮ ዋና ሕንፃ ውስጥ በአራት ክፍሎችና በአንድ መለስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ውሰጥ እየተገናባ ያለው ስቱዲዮ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለሥርጭት ከሚያገለግሉ መሣሪያዎች ገጠማ በስተቀር ዋና ሥራው ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለስቱዲዮው ክፍሎች ዕድሳት፣ የዋናውን የመሰብሰቢያ አዳራሽ የድምፅና ምሥል ቀረፃውን ከስቱዲዮው ጋር የሚያገናኝ የኔትወርክና የማይክሮ ዌቭ ዝርጋታና ተያያዥ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መጠናቀቃቸው ታውቋል፡፡ ከምንጮች ለመረዳት እንደተቻለው ለመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ብቻ እስካሁን ወደ አምስት ሚሊዮን ብር ገደማ ወጥቷል፡፡

ለስቱዲዮ ቀረፃና በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለሚተከሉ ዘመናዊ ካሜራዎች (Beta Canon HD Camera) ግዥ እንዲፈጸም በአመራሮች የተወሰነ ሲሆን፣  ቦሽ (Bosch)  የተባለው የጀርመን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ የወኪሉ በሆነው ኦርቢስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አማካይነት ካሜራዎቹን እንዲያቀርብ መመረጡ ታውቋል፡፡ ለግዥውም 24 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ ምንጮች አክለዋል፡፡

የግዥ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው ካሜራዎች የተወሰኑት ለስቱዲዮና ለመስክ ቀረፃ ሲውሉ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በዋናው የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ከ25 ዓመታት በፊት ተተክለው እስካሁን ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ነባር ካሜራዎችን ሙሉ ለሙሉ በዘመናዊ ዲጂታል መሣሪያዎች የሚተኩ ናቸውም ተብሏል፡፡

በፓርላማው የሚካሄዱ ስብሰባዎችን የሚመለከቱ ቀጥታ ሥርጭቶችንም ሆነ የስቱዲዮ ዝግጅቶችን ከምድር ማሠራጫ ጣቢያ ወደ ሳተላይት የሚደረገውን መልዕክት ልውውጥ ለማከናወን የሚረዳውና (Earth Station) የተባለው መሣሪያ በራሱ ከመትከል ይልቅ፣ የኢቢሲን ማሠራጫ ለመጠቀም በሁለቱ ተቋማት ስምምነት መደረጉን ነው የተነገረው፡፡

ፓርላማው የራሱን መሣሪያ ከመትከል ይልቅ ለምን የኢቢሲን ማሠራጫ መጠቀም  እንዳስፈለገው ሪፖርተር የጠየቃቸው ሌላ ባለሙያ በሰጡት ምላሽ፣ በአገሪቱ ካሉ የመንግሥትም ሆነ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ትልቁ የኢቢሲ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአንድ ጊዜ ስምንት ቻናሎችን ማሠራጭት ይቻላል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢቢሲ ሦስት ቻናሎችን ኢቴቪ ዜና፣ ኢቴቪ መዝናኛና ኢቴቪ ቋንቋዎች (Languages) ብቻ ስለሚጠቀም፣ ፓርላማው አራተኛ ቻናል በመሆን የቴሌቪዥን ጣቢያውን ማሠራጨት እንደሚችል መግባባት ስለተደረስ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ኢቢሲም ተጠሪነቱ ለፓርላማው መሆኑን በማስታወስ፣ ሁለቱ ተቋማት በቀላሉ ተግባብተው ስለሚሠሩ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...