Thursday, June 20, 2024

ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቁርስ እየበሉ ነው]

 • ምነው ተከዝክ?
 • እንዴት አልተክዝ?
 • ቡናህ እኮ ቀዘቀዘ፡፡
 • እዚህ አገር ምን ያልቀዘቀዘ ነገር አለ?
 • ቁርሱም እኮ እየቀዘቀዘብህ ነው ብላ እንጂ?
 • ባክሽ ዘግቶኛል፡፡
 • መቼም ጉሮሮህን ወጣቶቹ አላገኙትም?
 • የትኞቹ ወጣቶች?
 • መንገድ የሚዘጉት ናቸዋ፡፡
 • ተይኝ እስቲ ባክሽ?
 • ምነው?
 • ሁሉም ነገር እኮ ግራ ያጋባል፡፡
 • እንዴት?
 • አንዱን ስትይው አንዱ እያለ መከራችንን በላን፡፡
 • ብዙ አትጨነቅ ባክህ?
 • እንዴት አልጨነቅ?
 • ማለቴ ሁሉም ከልኩ አያልፍም ብዬ ነዋ፡፡
 • እየቀለድሽ ነው?
 • የምን ቀልድ ነው?
 • ታዲያ አገር እንዲህ ተወጣጥራ እያየሽ ከልኩ አያልፍም ስትይኝ ነዋ?
 • ምን ላድርግ ታዲያ?
 • በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡
 • እንዴት?
 • አንዱን ቀዳዳ ስንደፍን ሌላው እያንጠባጠበ ተቸግረናል፡፡
 • ዋናው ለራስ ማሰብ ነው ባክህ፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • መጀመርያ ለራስህ አስብ፡፡
 • አልገባኝም?
 • አንተ የተደላደለ ነገር ካለህ ሌላው ችግር የለውም፡፡
 • የአገሪቱ ጉዳይ አያሳስብሽም?
 • አንተ ጥሩ ነገር ካለህ መከራውም እኮ ቀስ ብሎ ነው የሚያገኝህ፡፡
 • እ…
 • አገሪቱ ላይ ችግር ሲከሰት እኮ ሀብታም በዜና ነው የሚሰማው፡፡
 • እንዳይመስልሽ?
 • እንዴት?
 • የከፋ ነገር ከመጣ ሀብታሙ ራሱ ዜና ሊሆን ይችላል፡፡
 • እ…
 • ሀብት መቼም የሁሉ ነገር መልስ እንዳልሆነ ታውቂያለሽ፡፡
 • በዚህ ሐሳብ ብዙም አልስማማም ባክህ፡፡
 • ለምን?
 • ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ የሚለው ነው ብዙ የሚገባኝ፡፡
 • እ…
 • ይኸው በቀድሞው ሥርዓት ሀብት የሰበሰቡ አሁን ምን ሆኑ?
 • እ…
 • ከሕግ በላይ የሆኑ ሰዎች እንዳሉ እኮ ግልጽ ነው፡፡
 • ማን ነው ያለው?
 • እሱንማ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ነው የሚናገረው፡፡
 • ምን አልሽ?
 • ለማንኛውም አንተም የድርሻህን በጊዜ ብትወስድ ጥሩ ነው፡፡
 • ሲኖር ነዋ፡፡
 • እሱማ ከአንተ በፊት የነበሩት ጠራርገው እንደበሉት አውቃለሁ፡፡
 • ተይኝ እስቲ፡፡
 • ለማንኛውም ሌላው ቢቀር አንድ ነገር ለሁላችንም አመቻችልን፡፡
 • ምን?
 • ቪዛ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ስልክ ደወለላቸው]

 • ያሳዝናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • ሁሉ ነገር፡፡
 • አልገባኝም?
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እኮ ተስፋ አስቆራጭ ሆናለች፡፡
 • እንደዚህማ አትሁን፡፡
 • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለውጥ ላይ ነን እኮ፡፡
 • ተው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • ለውጡማ ተቀልብሷል፡፡
 • እ…
 • እሱን ማረጋገጥ እችላለሁ፡፡
 • እንዴት?
 • ክቡር ሚኒስትር ብዙ ጊዜ ነው እኮ ዕድል የሰጠናችሁ፡፡
 • እሱንማ እናውቃለን፡፡
 • ግን አገሪቱ እየባሰባት እንጂ ስትሻሻል አላየንም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ይኸው የእኔ ፋብሪካ እንኳን ለሦስተኛ ጊዜ እኮ ነው ጥቃት የደረሰበት፡፡
 • ለምን?
 • ገንዘብ አልሰጥም ስላልኩ ነዋ፡፡
 • ለማን?
 • ለስውር መንግሥቱ ነዋ፡፡
 • የምን የስውር መንግሥት ነው?
 • ይኼ እኮ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
 • ምኑ ነው የአደባባይ ሚስጥሩ?
 • ከመንግሥት ውጪ ሌላ ስውር ኃይል መኖሩ ነዋ፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ክቡር ሚኒስትር ይህ ኃይል ባለሀብቶችን እያስጨነቀ ነው፡፡
 • ምን አድርጉ ብሎ ነው የሚያስጨንቀው?
 • ገንዘብ አምጡ እያለ ነዋ፡፡
 • እ…
 • አላመጣም ያለ ባለሀብት የእጁን ያገኛል፡፡
 • ወይ ጣጣ?
 • እኔም እንግዲህ የዚያ ገፈት ቀማሽ ነኝ፡፡
 • ማለት?
 • ይኸው ገንዘብ አልሰጥም በማለቴ ጥቃት ደርሶብኛል፡፡
 • ይኼማ ሕገወጥ ድርጊት ነው፡፡
 • የአገሪቱ ሕገወጥነት ከተንሰራፋ እኮ ቆየ፡፡
 • እ…
 • የሕግ የበላይነት ከተረሳ ሰነባበትን፡፡
 • እንደዚህ አትበል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ራሱ ሕግ ማስከበር ካቃተው ሰነባበተ እኮ፡፡
 • እ…
 • ለማንኛውም አደዋወሌ ለመሰነባበት ነው፡፡
 • የምን ስንብት ነው?
 • ከእነ ቤተሰቤ ልንለቅ ነው፡፡
 • ምን?
 • አገር!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]

 • ምን እየተካሄደ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የት?
 • አገሪቱ ውስጥ ነዋ፡፡
 • ለውጥ ነዋ፡፡
 • ነውጥ ማለትዎ ነው?
 • ኧረ አይባልም፡፡
 • እንዴት አይባልም?
 • አንተ ሚኒስትር ነሃ፡፡
 • ብሆንስ?
 • እንዴት አገሪቱ ውስጥ ነውጥ አለ ትላለህ ታዲያ?
 • መቼም ሰላም አለ አልል ታዲያ?
 • ለውጥ ላይ ነን ነው የሚባለው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሁሉም ነገር አንገሽግሾኛል፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ሥልጣን ላይ የወጣነው እኮ ሕዝብን ለማገልገል ነው፡፡
 • ማን አይደለም አለህ ታዲያ?
 • እሱን እያደረግን ግን አይደለም፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ሕዝብ እኮ እያለቀ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ይደረግ ታዲያ?
 • ይኼ ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ?
 • ምን ማለት ነው?
 • እኛ ሥራችንን እየሠራን አይደለም ማለት ነው፡፡
 • ያለብንን ፈተና ታውቃለህ አይደለም እንዴ?
 • ባውቅስ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሁሉም ነገር በአንዴ አይለወጥማ፡፡
 • ሕግ ማስከበር ግን የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • አሁን ግን ግለሰቦችና ቡድኖች ከሕግ በላይ እየሆኑ ነው፡፡
 • እ…
 • በዚህ ምክንያት ደግሞ በርካቶች እያለቁ ነው፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ታዲያ እንዴት እንቅልፍ ይወስድዎታል?
 • እ…
 • አገራችን ላይ ይኼ ሁሉ እየሆነ እንቅልፍ መተኛት አልቻልኩም፡፡
 • ጭንቀትህ ይገባኛል፡፡
 • እሱ መፍትሔ አይሆንም፡፡
 • አሁን እኮ እያደረግን ያለነው ከዚህ የባሰ ዕልቂት እንዳይመጣ ነው፡፡
 • እንደዚህ ግን ነገሮች አይቀጥሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ይደረግ?
 • ይኼንን ጥያቄ ነዋ መመለስ ያለብን፡፡
 • እ…
 • እኔ በበኩሌ የማደርገውን አውቃለሁ፡፡
 • ምን ልታደርግ ነው?
 • ሕዝብ እንደዚህ እያለቀ ሥልጣን ላይ መቀመጥ አልችልም፡፡
 • ማለት?
 • እለቃለሁ፡፡
 • ከምን?
 • ከሥልጣን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ተጨንቄያለሁ፡፡
 • በአገሪቱ ጉዳይ ነው?
 • ከአገሪቱ በላይ ያስጨነቀኝ የፓርቲያችን ጉዳይ ነው፡፡
 • እ…
 • ያው ፓርቲያችን ፈረሰ ማለት እኮ አገር ፈረሰ ማለት ነው፡፡
 • ይህቺን ነገር የት ነበር የሰማሁዋት?
 • እ…
 • ፓርቲና አገርን ምን አገናኛቸው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ አገር ሁለቱ መቼ ይለያያሉ?
 • ማወቅ ያለብህ ግን ሁለቱ አንድ ያለ መሆናቸውን ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ውህደቱ ግን ጠቃሚ አይመስለኝም፡፡
 • ለምን?
 • እውነቱን ልንገርዎት?
 • አዎ ንገረኝ፡፡
 • እንደ እኔ ዓይነት ሰዎች ምንም ቦታ አያገኙማ፡፡
 • እንዴት?
 • ማለቴ ፓርቲያችን ተዋህዶ አንድ ከሆነ አቅም ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸዋ ወደ ሥልጣን የሚመጡት፡፡
 • ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አሉ፡፡
 • እ…
 • ስለራስህ ብቻ ነው አይደል የምታስበው?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼን ቦታ ያገኘሁት አቅም ኖሮኝ አይደለም እኮ፡፡
 • እሱንም ማወቅህ ጥሩ ነው፡፡
 • እውነቴን እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለነገሩ አንተ ጥሩ አቅምህ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
 • ምንድነው?
 • ሴራህ ነዋ፡፡
 • እ…
 • ስለዚህ መቀላቀል ትችላለህ፡፡
 • ማንን?
 • ሴረኛ ፓርቲውን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...