Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ላኪዎችንና የወጪ ንግዱን የሚያስተካክል መመርያ እንደሚተገብር አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለውጭ ምንዛሪ ሲሉ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሐሰተኛ ላኪዎችን አስጠንቅቋል

የወጪ ንግድ ገበያን ለማሳደግ የግብይት ሥርዓትን ማስተካከል ቅድሚያ ትኩረት እንደሚሰጠውና ላኪዎች በሕጋዊነት ፈቃድ ባገኘ አግባብ ብቻ ምርቶቻቸውን እንዲልኩ የሚያስገድድ አሠራር የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምሥጋና አረጋ (አምባሳደር) ይህንን የገለጹት፣ ብሔራዊ የግብይት ፈጻሚዎች ማኅበር ጠቅላላ ጉባዔውን ባካሄደበትና ለአባላቱ ዕውቅና በሰጠበት ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነበር፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፣ በወጪ ንግድ ዘርፉ የተንሰራፉትን ችግሮች ለመፍታት የግብይት ሥርዓቱ መስተካከል እንደሚያስፈልገውና መንግሥትም የቁጥጥር ሥራ ጀምሯል፡፡

በውሸት ላይ የተመሠረተ የግብይት ሥርዓት፣ በተለይም ከዓለም የግብይት ሕጎችና ግብይት ሁኔታዎች ጋር የማይጣጣሙ ሥርዓቶችን በማስተካከሉ ረገድ መንግሥት እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

‹‹የግብይት ተዋንያን በአግባቡ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፤›› ያሉት አምባሳደር ምሥጋናው፣ ‹‹የአገራችን የወጪ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ለመሄዱ አንዱ ምክንያት ገበያን ያገናዘበ የግብይት ሥርዓት ካለመኖር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ሆን ብለው በኪሳራ ምርት ወደ ውጭ የሚልኩትን የመቆጣጠር ሥራ እንደጀመረ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በቁጥጥር እንዲመራ ሳናደርግ ቆይተናል፡፡ በቅርቡ የጀመርነው የመቆጣጠር ሥራ ዋናው ዓላማ ከስረህ አትሽጥ፡፡ አትርፈህ ሽጥ፤›› የሚል መመርያ እንደሚከተል አስታውቀዋል፡፡

ነጋዴው አትርፎ ለመሸጥ የገባበት የወጪ ንግድ ዘርፉ በኪሳራ የሚሸጥበት ሁኔታ ሲፈጠርበት፣ ‹‹በሰላማዊ ሠልፍ ሊጠይቀው የሚገባ ጉዳይ ነበር፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ መንግሥትም ቢሆን ይህ ሁኔታ ሲፈጠር መመርያ ሊያወጣበት ይገባ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ኤክስፖርት አትራፊ ቢዝነስ በመሆኑ አትርፎ መሸጥ ሲገባ ጭራሹኑ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል ከስሮ በመሸጥ የሚንቀሳቀሱ፣ ዋና ሥራቸው አስመጪ የሆኑ፣ ለመንግሥትም ኪሳራ ውስጥ እንደወደቁ በመጥቀስ የውሸት ሪፖርት የሚያቀርቡ በመገኘታቸው ይህ ይቁም በማለት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ በገበያ ሥርዓትና በውድድር መመራት እንዳለበት፣ ዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓቱም የዋጋ ጭማሪ እያሳየ ባለበት ወቅት እንኳ፣ ላኪዎች እንደከሰሩ የሚገልጽ የውሸት ሪፖርት ለመንግሥት ሲቀርቡ የቆዩበት አካሄድ አግባብ እንዳልሆነና ከአሁን በኋላም ይህ እንደማይቀጥል አስታውቀዋል፡፡

‹‹የውሸት ሪፖርቱ ከሃይማኖታዊም ሆነ ከሥነ ምግባር አኳያ፣ ከራስ እምነት አኳም እንዲህ ያለው ውሸት ከእንግዲህ መቆም አለበት፤›› በማለት በኪሳራ ሪፖርት ማድረግና እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለማረም መንግሥት ማስተማርን እንደሚያስቀድም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን በነበረው አሠራር ‹‹ከቡናችን በላይ ታዋቂ የሆናችሁ፣ በዓለም ገበያ ከቡናችን በላይ እንደ ብራንድ የምትታዩ ኤክስፖርተሮቻችን ከጨዋታ ውጪ ሆናችኋል፤›› በማለት፣ ሆነ ተብሎ በሚደረግ የተዛባ ከግብይትና ከንግድ ሥርዓቱ ውጪ የተደረጉ ነጋዴዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም ነጋዴው የአገር ውስጥ ገበያውም ሆነ የዓለም ገበያ የሚሰጠውን ዋጋ መሠረት በማድረግ ምርቶች መላክ እንደሚጠበቅበት በማሳሰብ፣ መንግሥት ሕጋዊና ውድድር ላይ የተመሠረተ የወጪ ንግድ እንዲንሰራፋ ድጋፍ እንደሚሰጥና የተበላሸውን የላኪነት ሥርዓትም እንደሚያስተካክል ሚኒስትር ዴኤታው በንግግራቸው አመላክተዋል፡፡ የግብይት ተዋንያንያኑም የአገሪቱን ወጪ ንግድ በማሻሻሉ ረገድ ትክክለኛ የግብይት ሥርዓት እንዲስፋፋ በማድረግ ተቀዳሚ ሚናቸው እንዲወጡ  አሳስበዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሔራዊ የግብይት ማኅበሩ ሥር ያሉ አባላት በ2011 በጀት ዓመት ብቻ ከ691,216 ቶን ምርት ከ34.3 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ማገበያየት መቻሉ ታውቋል፡፡ 339 በሚሆኑና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወንበር ባላቸው አባላት የተፈጸመው ይህንን ያህል ግብይት በዘመናዊ ግብይት ውስጥ ያላቸውን ሚና አሳይቷል ተብሏል፡፡ ከእነዚህ አባላት ጋር ከ20 ሺሕ በላይ የንግድ ኅብረተሰብ በአቅራቢነትና በገዥነት የሚሠሩ መሆኑን የሚጠቁመው መረጃ፣ ከእነዚህ የግብይት ተዋናይ ውስጥ ከፍተኛ ግብይት ለፈጸሙና ለተመረጡ ተዋንያን በቅዳሜው ፕሮግራም ላይ ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ የዕውቅና አሰጣጡ ከፍተኛ ግብይት በመፈጸማቸው ብቻ ሳይሆን በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የተቀመጡ ሕግጋቶችን በአግባቡ መፈጸማቸውና አለመፈጸማቸው እንደ መሥፈርት ተወስዶ የተመዘኑ መሆኑንም የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ወርቅነህ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

በዕውቅና አሰጣጡ ከፍተኛ ምርት እንዲገበያይ ማስቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በግብይት ሒደት ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸው ማናቸውንም ክንውኖች በአግባቡ ስለሚካሄዱ ጭምር በመገንዘብ ነው፡፡

ይህም የሆነበት ምክንያት ማኅበሩ በአዋጅ እንዲቋቋም በተደነገገው መሠረት ከዓላማዎቿ አንዱ ሥነ ምግባር የተላበሰ የግብይት ሥርዓትን ማስረፅ ከመሆኑ አኳያ የሽልማት መሥፈርቱን እንዲህ ያሉትን እንዲያካትት ተደርጓል፡፡

በዕለቱ የዕውቅና መሥፈርቶቹን በተመለከተ እንደተጠቀሰውም የተሸላሚ አባላት ዋና ዋና የማወዳደሪያ መሥፈርቶች ውስጥ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ምርት በመግዛት ወይም በመሸጥ ከአንደኛ እስከ አሥረኛ የወጣ፣ ከፍተኛ የግብይት ክፍለ ጊዜ ያስመዘገበ የሚሉ ይገኝበታል፡፡ ከዚህም ሌላ በምርት ገበያው የግብይት እንቅስቃሴ በራሱ ወይም በመድረክ ወኪሎች አማካይነት ምንም ዓይነት ጥቁር ነጥብ ያልተመዘገበበትና በምርት ገበያው የግብይት እንቅስቃሴ በራሱ ወይም በበኩሉ ምንም ዓይነት የጥፋት ሪከርድ ታይቶበት ያልተቀጣ የመሳሰሉ ይገኙበታል፡፡

በመመዘኛው መሠረት የተሻለ ግብይት አፈጻጸም ያሳዩ የምርት ገበያው አባላትን በሽያጭና በገዥ ወገን በመለየት በየምርት ዓይነቶቹ ከአንድ እስከ ሦስት የወጡት እንዲሸለሙ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የሽልማት ዘርፉ በሁለት የተከፈለ ሲሆን፣ ከዋናዎቹ ወንበር ካላቸው አባላት ሌላ የመድረክ ወኪሎችም በተናጠል እንዲሸጡ የተደረገበት ነው፡፡ ለእነሱም ራሱን የቻለ መሥፈርት ተዘጋጅቶ የተለዩ ሲሆን፣ ከክንውኖቹ አንደኛ ብቻ የወጡት በዕለቱ ተሸልመዋል፡፡

የመድረክ ወኪሎች፣ ተሸላሚዎች ዋና ዋና መሥፈርቶች፣ አንደኛ በምርት ገበያው የመድረክ እንቅስቃሴ በግብይት ዓመቱ በግብይት የተሳተፉበት ብዛት፣ የአቅራቢ ወኪሎች የገዥ ወኪሎች፣ የአገር ውስጥ ቡና ጄኔራል ወኪሎች፣ የመድረክ ወኪሎች በግብይት እንቅስቃሴው ምንም ዓይነት ጥቁር ነጥብ የሌለበት፣ የጥፋት ካርድ የሌለው መሆኑ ተረጋግጦ ዕውቅና የሚሰጥበት ሲሆን፣ በዚህ መመዘኛ መሠረት የምርት ገበያው መድረክ ወኪሎች በቡና በሽያጭ ወገን ተለይቶ አንደኛ ለወጡት ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

የተሻለ የግብይት አፈጻጸም በማስመዝገባቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ገዥ አባላት (ኤክስፖርት ቡና ገዥዎች) ሆራ ትሬዲንግ፣ አባህዋ ትሬዲንግና ኤስኤ ባገርሽ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ተሸልመዋል፡፡ ከአገር ውስጥ ቡና ገዥዎች ደግሞ ከፍተኛ አፈጻጸም በማስመዝገብ ተሸላሚ የሆኑት እምባራዶም ቢዝነስ፣ ሳጉሬ ትሬዲንግና አልሁስ ቡና ግዥና ሽያጭ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበሮች ናቸው፡፡

በሰሊጥ ገዥዎች በኩል ዋርካ ትሬዲንግ ሐውስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በላይነህ ክንዴ ወደ ውጭ ላኪና አልፋ ሰሊጥ አቅራቢ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው በዕለቱ ዕውቅና ሲሰጣቸው፣ ከጥራጥሬ ምርት ገዥዎች ሙሉዓለም አለበለው፣ መሐመድ ሁሴን በያንና አዝመራው በቀለ አስመጪና ላኪ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

የተሻለ የግብይት አፈጻጸም በማስመዝገባቸው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ሻጭ አባላት ደግሞ ቡና አቅራቢዎች ደጀኔ ታደሰ ጌታሁን፣ ወጂን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና መኩሪያ መርጊያ ሊባቦ ሆነዋል፡፡

ሰሊጥ አቅራቢዎች አብርሃም፣ ወላይና ሙሉ ሰሊጥ አቅራቢና ወኪል ሽርክና ማኅበር፣ ሲናር መር ትራድ ቢዝነስና ኤቢሲዲ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲሸለሙ፣ ጥራጥሬ ምርት አቅራቢዎች ገላዬ ይንገሥ ፈለቀ፣ ዓባይ ነው ዘርፉ አለነና ሰዒድ ሁሴን አህመድ በየደረጃቸው ተሸላሚ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የተሻለ የግብይት አፈጻጸም ያስመዘገቡ መድረክ ወኪሎችም በተመሳሳይ ተሸልመዋል፡፡

ብሔራዊ ማኅበሩ የተቋቋሙ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሥራ በጀመረ በሁለተኛው ዓመት ነው፡፡ ከአቶ ፍፁም ገለጻ መረዳት እንደተቻለው፣ ማኅበሩ የተቋቋመት ዓላማ የግብይት ተዋንያንን የየማኅበሩ አባላት እውነት ሥነ ምግባርና ክህሎት ለመጠበቅና ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው ደንብ ላይ ደግሞ የግብይት ተዋንያን የምርት ገበያውንና የባለሥልጣኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የሚወጡትን ሕግና መመርያ አክብረው መሥራታቸውን ያረጋግጣል የሚል ኃላፊነት ማኅበሩ እንደተሰጠውም ገልጸዋል፡፡

አባላት መብትና ጥቅማ ጥቅማቸውን ለማስከበርም ድምፃቸውን በማኅበሩ በኩል ያሰማሉ በዕውቀት በክህሎትና በሥነ ምግባር እንዲሠሩም ያደርጋል ተብሏል፡፡ በዚህ ብሔራዊ ማኅበር ውስጥ አባል የሆኑት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውስጥ በመሸጥና በመግዛት ወንበር ያላቸው ናቸው፡፡ ወንበር ያለው በቀጥታ የማኅበሩ አባል የሚሆኑ ሲሆን፣ አንደኛ ማኅበር ሆኖ የተቋቋመ ነው፡፡ በምርት ገበያው 547 ወንበር ያላቸው ነጋዴዎች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ግን እየሠሩ ያሉ 339 አባላት ናቸው፡፡ ምርት ገበያው ሲመሠረት አጠቃላይ የአገሪቱ ምርት በምርት ገበያው በኩል ይካሄዳል በሚል እንደ ስንዴ፣ ጤፍና የመሳሰሉ ምርቶች ግብይት ውስጥ ለመግባት ወንበር ገዝተው ስለነበር አሁን የሚፈልጉት ምርት ባለመኖሩ የተፈጠረ ክፍተት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች