Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በነገ ለማትረፍ ከዛሬ እንጨልፍ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥቅምት 2012 ዓ.ም. የቁጠባ ባህልን ለማዳበር የቁጠባ ንቅናቄ በማለት የአንድ ወር ዘመቻ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ የቁጠባ ንቅናቄውን ተግባራዊ ለማድረግ ከያዛቸው ተግባራት መካከል ታዳጊዎችን ታሳቢ ያደረገው ክንውኑ ትኩረቴን ስቦታል፡፡

ይህ የባንኩ ተግባር ለታዳጊዎች የቁጠባ ባህልን ከማስገንዘብ ያለፈ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ታዳጊዎች ስለተቋሙ ግንዛቤ እንዲኖቸው ዝርዝር መረጃ የሚሰጡ ጉብኝቶችን በማካተት እግረ መንገዱንም ቁጠባ ምን ማለት እንደሆነ ያስገነዘበ አካሄድ እንደጀመረ ከባንኩ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተገንዝቤያለሁ፡፡

በዙሪያችን የምናየው የአገልግሎት አሰጣጥና አንድን ተቋም የበለጠ ለማሳደግ የሚረዱ ተግባራት ሁሉ ታሳቢ የሚያደርጉት ትኩረት የሚሰጡበትን የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ተቋማት የተመረጡ ወይም ትኩረት የሚያደርጉባቸው መስኮች ላይ ተጠቃሚው ማን እንደሆነ በመለየት አገልግሎት ማቅረባቸው የኖረና የነበረ ነው፡፡ ንግድም ደንበኛ ተኮር በመሆኑ ለዚህ መርሕ ይገዛል፡፡

ንግድ ባንክ ግን በተለየ መንገድ ታዳጊዎችን ታሳቢ ማድረጉ መልካም ጅምር ነው፡፡ ለነገሩ ባንኩ የተቀሩትን ባንኮች በብዙ ሁኔታ ‹‹ሰርፕራይዝ›› ሲያደርጋቸው መኖሩ የታወቀ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችን የጎበኙት ተማሪዎች በአዲስ አበባ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ነበሩ፡፡ ስለባንክ አሠራርና ስለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ታሪክ በአቅማቸው ደረጃ ግንዛቤ ሲሰጣቸው ተመልክተናል፡፡

በእኔ አመለካከት ባንኩ ራሱን ለማስተዋወቅና የተቀማጭ ገንዘቡን ለማሳደግ ካለው ፍላጎት ባሻገር፣ ታዳጊዎች ኢንዱስትሪውን እንዲያውቁትና እንዲገነዘቡት ያደረገው ጥረት የሚወደስ ነው፡፡ አገር ተረካቢዎቻችን ዛሬ ያዩትንና የተገነዘቡትን ነገ ይረከባሉ፡፡ ንግድ ባንክም ይህንኑ ተግባር የመወጣት ጅምር ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ትልልቅ ተቋሞች አሏት፡፡ እነዚህን ተቋማት ዛሬ ለሚገኙበት ደረጃ ያበቋቸውም እነ እከሌ እከሌ ናቸው በማለት የአገር ባለውለታዎችን ለመዘከርና ለማስተዋወቅ የሚጠቅም ጅምር ስለመሆኑም በተጨባጭ ያየንበት በመሆኑ ንግድ ባንክ ፋና ወጊ ነው ለማለት እንችላለን፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ተግባር የታዳጊዎችን ሥነ ልቦና በማነጽ ስለ አገራቸውና አገራቸው ስላሏት ሀብቶች የሚኖራቸውን ጠቅላላ ዕውቀት ለማስፋትም ጥሩ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ባንኩ የጀመረው ዓይነት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በአዲስ አበባ ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ በርካታ ሕዝብ ወደ ሚኖርባቸው ገጠራማ አካባቢዎች በመሄድም ባንኩ ታዳጊዎችን ማነቃቃት ቢችል የበለጠ ጥሩ ውጤት ሊያገኝበት ይችላል፡፡

የባንኩ ተግባር ስቦኝ ስለ ንግድ ባንክ አዲስ ተግባር መግለጼ ሌሎቹም እኛም እንዲሉ ለመጎትጎት ጭምር ነው፡፡ ልጆች ነገን በጉጉትና በተስፋ እንዲያዩ፣ በዛሬ ማንነታቸው ውስጥ የነገዋ ኢትዮጵያ ባለቤት የመሆናቸውን ሥነ ልቦና የሚፈጥሩ አሠራሮችና ተሞክሮዎች ቢጠናከሩ፣ ለወደፊቷ ኢትዮጵያችን ተጠሪና ኃላፊ ዜጎች እንዲኖሩን ለማድረግ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡ በተግባር ለማስተማርም ጥሩ ዘዴ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ለዚህ ማረጋገጫው የንግድ ባንክን የተለያዩ የአገልግሎት ክፍሎች የጎበኙ ልጆች ሲሰጧቸው የነበሩ አስተያየቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ባለው መንገድም ትውልድ ለመቅረፅ ይቻላል የሚል መልዕክት የተላለፈበት ጅምር ነው፡፡ ልጆቹ ስለ ንግድ ባንክ በሚዲያ እንኳ ያልሰማናቸውን ወይም ብዙም ትኩረት ያልሰጠናቸውን ጉዳዮች ነቅሰው ሲናገሩ መስማት በራሱ ውጤቱን ያሳያል፡፡

ከገረሙኝ የልጆች አስተያየቶች መካከል ለምሳሌ በግንባታ ላይ የሚገኘውን ሕንፃ ከጎበኙ በኋላ ‹‹የዚህ ሕንፃ ርዝመት ከኢትዮጵያ አንደኛ ከአፍሪካ ሦስተኛ እንደሆነ አውቄያለሁ፤›› በማለት አንዷ ተማሪ ስትገልጽ፣ ሌላኛዋ ‹‹ዶክተር መሆን እፈልግ ነበር፡፡ አሁን የተረዳሁት ግን ዶክተር ለመሆንና ሕንፃ ለመገንባት ገንዘብ ስለሚያስፈልግ ከዛሬ ጀምሮ እቆጥባለሁ፤›› ብላለች፡፡ በትምህርት ቤት ከሚነገራቸውና ከሚማሩት በተጓዳኝ ስለ ቁጠባ ጠቀሜታ ተማሪዎች በቀላሉ መማር የቻሉበትን ዕድል አግኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸው የተደሰቱ ተማሪዎች ወደፊት የባንክ ባለሙያ ለመሆን መጓጓት ሲያድርባቸው ተመልክተናል፡፡ ተማሪዎቹ አንጋፋ የባንክ ባለሙያዎችን ከማወቅ ባሻገር እግረ መንገዳቸውን የአገር ባለውለታዎችን እንዲያውቁና የእነሱንም መልካም ሥራ እንዲገነዘቡ ጉብኝቱ አግዟቸዋል፡፡

ስለዚህ ወጣቱን ትውልድ ለማነጽ ከሚያግዙን በርካታ ተግባራት መካከል አንዱ እንዲህ ያሉ መልካም ጅምሮች ናቸውና ታዳጊዎቻችን ጭንቅላት ውስጥ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማስቀመጥ ትልቅ ውጤት ማስገኘቱ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ ተቋማት እንዲህ ያለውን አካሄድ ቢለምዱት መልካም ነው፡፡ ለነገው ትውልድ ምን እናወርሳለን የሚለው ወሳኝ ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንደ ዜጋ ነገ ተረክቦ አገርና ሕዝብን እንዲያገለግሉ እንዲህ ባሉ ኩባንያዎች ውስጥ የመሥራት ጉጉት እንዲያድርባቸውም ጭምር አጋዥነቱን ያሳየ ጅምር በንግድ ባንክ አሐዱ መባሉ እሰየው ነው፡፡ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ዋጋ እንዲሰጡም የሚያግዝ ተስፋ ሰጭ ጅምር ነው፡፡ ልጆች ነገ ምን መሆን እንደሚፈልጉ ሲጠየቁ፣ አብዛኞቹ ዶክተር ወይም ፓይለት ወይም ሌሎች ትልልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጣቸውን የሙያ መስኮች ይገልጻሉ፡፡

እንደ ንግድ ባንክ አካሄድ ከሆነም፣ የባንክ ባለሙያነትን፣ ፖሊስነትን፣ የእሳት አደጋ ሠራተኛነትንና ሌሎችንም ሙያዎች እንዲያውቁ፣ ነገን እንዲናፍቁ ለማገዝ  ተቋማትንና ሌሎችም የሙያ መስኮችን አግባብ ባለው መልኩ እንዲጎበኙ የማድረጉ ሥራ ትርፉ የበዛ ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት