Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአሜሪካ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያን ከግብፅና ከሱዳን ጋር ማደራደር ልትጀምር ነው

አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያን ከግብፅና ከሱዳን ጋር ማደራደር ልትጀምር ነው

ቀን:

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተለይ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል እንደ አዲስ የተነሳውን አለመግባባትና መካረር በአደራዳሪነት ለመፍታት፣ የሁለቱ አገሮችና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዋሽንግተን እንዲገኙና እንዲደራደሩ አሜሪካ ጥሪ አደረገች፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሠረትም የሦስቱ አገሮችን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከመጪው ረቡዕ ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በዋሽንግተን ተገናኝተው ድርድራቸውን እንደሚጀምሩ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህ መሠረት በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የሚመራ ቡድን ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ሥፍራው እንደሚያቀና የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

- Advertisement -

ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅና ከሱዳን የተወጣጡ ባለሙያዎች የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ሲያደርጉት የነበረውን ድርድር በማቋረጥ ሦስተኛ ወገን፣ በተለይም የአሜሪካ መንግሥት በአደራዳሪነት እንዲገባ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ጥሪ ያቀረበችው ግብፅ መሆኗ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የግብፅ አቋምና የሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ጥሪ እንደማይቀበለው በመግለጽ መግለጫ ያወጣው፣ ወዲያውኑ ድርድሩ ሲካሄድ በነበረበት ሱዳን ሳለ ነበር፡፡

በማግሥቱም የግብፅን የሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ፍላጎትና ከቴክኒክ ድርድሩ ማፈንገጥ በተመለከተ፣ ዝርዝር መግለጫ በማውጣት አጣጥሎት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው በዚህ ዝርዝር መግለጫ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ያሉ ልዩነቶች ቴክኒካዊ በመሆናቸው፣ የመፍትሔ መንገዱ ሳይንሳዊ ጥናት ብቻ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በመሆኑም ግብፅ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ያቀረበችው ጥያቄ፣ የልዩነቶቹን ተፈጥሯዊ ባህርይ ያላገናዘበ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ሳይንሳዊ ጥናትን መሠረት በማድረግ ሊፈቱ የሚገቡ የልዩነት ነጥቦች በፖለቲካዊ መድረክ ይፈታሉ ብሎ መጠበቅ ከልዩነቶቹ ይዘት አንፃር ስህተት እንደሆነ፣ ከኢትዮጵያና ከሱዳን መንግሥታት ስምምነትም ሆነ ፍላጎት ውጪ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ከሳምንት በፊት በተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (እና) የግብፅ አቻቸው ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ያሉ ልዩነቶችን በተመለከተ የጎንዮሽ ውይይት አድርገው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ግብፅ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ያቀረበችውን ጥያቄ በተመለከተ ተወያይተው ስምምነት ላይ እንደደረሱ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ ግብፅ ያቀረበችውን የሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ጥያቄ የተቀበለችው በቅድመ ሁኔታ መሆኑን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በወቅቱ መናገራቸውን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህ ቅድመ ሁኔታም በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት ጠቃሚ የሆነው የቴክኒክ ባለሙያዎች ድርድር መቀጠል እንዳበለት የሚያመለክት ሲሆን፣ የሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ብቻ የሚመለከት ነው የሚለው ደግሞ ሌላኛው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡

“የህዳሴ ግድቡን በሚመለከቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ኢትዮጵያ ቀደም ሲልም በሯ ዝግ አልነበረም፡፡ አሁንም ከማንም ጋር ለመነጋገገር በሯ ክፍት ነው፡፡ ስለሆነም ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት መግባቱ የሚያመጣው ችግር የለም፤” ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እምነት ይህ ቢሆንም ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ስምምነት ላይ መደረሱ በግብፅ መንግሥት የተሰጠው ትርጉምና ፋይዳ ግን የተለየ ስለመሆኑ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ከሚያወጡዋቸው መረጃዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በተካሄደው የዓረብ አገሮች የውኃ ደኅንነት ውይይት ላይ የተገኙት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሽኩሪ፣ “በአሜሪካ መንግሥት አደራዳሪነት የሚጀመረው ውይይት በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ያለውን ልዩነት በመቅረፍ ሕጋዊ አስገዳጅነት ወደሚኖረው የሦስትዮሽ ስምምነት ያደርሳል የሚል ትልቅ እምነት ግብፅ አላት፤” ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው የዓባይና የህዳሴ ግድቡን ፖለቲካዊ ጉዳዮች በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተመራማሪ፣ ኢትዮጵያ የሦስተኛ ወገን አደራዳሪነትን መቀበል የለባትም ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ፡፡

ለዚህ የሚሰጡት ምክንያትም፣ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት ሲገባ የራሱን ፖለቲካዊ ፍላጎቶችና ጥቅሞች ጥሎ ጥርት ባለ ገለልተኝነት የማደራደር ሚናውን ይወጣል ብሎ ለመቀበል አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ ይህም ነገሩን ውስብስብ በማድረግ መካረርን ሊፈጥርና የዚህም ውጤት በእነዚህ አገሮች ላይ ወይም በቀጣናው ላይ ፍላጎትና ጥቅም ያላቸው ሌሎች አገሮችን በመሳብ፣ የበለጠ መወሳሰብ ሊፈጥር እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ባትስማማ ተመራጭ እንደነበር ቢያምኑም፣ ይህ ጉዳይ አሁን ያለፈ በመሆኑ ቀጣዩ ጥንቃቄ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ በዋናነትም የሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ሚና፣ እንዲሁም በድርድሩ የሚሸፈኑ ጉዳዮች ይዘትና ወሰን በግልጽ እንዲቀመጥ፣ የሦስቱ አገሮች መሪዎች የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ2015 ከተፈራረሙት የትብብር መግለጫ መርሆች (ዴክለሬሽን ኦፍ ፕሪንስፕልስ) እንዳያፈነግጥ፣ ቴክኒካዊ የሆነው የውኃ ሙሌትና የግድቡ ኦፕሬሽን በዚህ ፖለቲካዊ ድርድር እንዳይታይ ኢትዮጵያ ማድረግ ይገባታል ሲሉ አክለዋል፡፡

ግብፅ የጀመረችውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመመከት አፀፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ በኢትዮጵያ በኩል ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሦስተኛ ወገን ድርድር ላይ ከተስማማች በኋላ በግድቡ ግንባታ ላይ ያላትን አቋምና ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያስረዳ መልዕክት ለአሜሪካ መንግሥት መላኳን፣ ከሁለት ሳምንት በፊት መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ድርድሩ ሊጀመር ቀናት ሲቀሩት ዓርብ ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ጋር በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን፣ በስልክ ውይይቱ ወቅት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የህዳሴ ግድቡ አንደኛው አጀንዳ እንደነበር ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...