Wednesday, June 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ተቋማት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሁሉም የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚያስችላቸውና የፋይናንስ ተቋማትም ተፈጻሚ የሚያደርጉት አዲስ ረቂቅ መመርያ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ሁሉም የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት አስተያየት እንዲሰጡበት የላከው ይህ ረቂቅ መመርያ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ዜጎች ወይም በትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሀብቶች የሚተዳደሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች፣ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የአክሲዮን ባለድርሻ ለመሆን የሚያስችላቸውን ዝርዝር ሕግጋቶች የያዘ ነው፡፡

በአዳዲስ ባንኮች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣ እንዲሁም በመድን ተቋማት ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚፈቀድ መሆኑን ረቂቁ በዝርዝር ያስረዳል፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፋይናንስ ተቋማት ሕጋዊ ባለድርሻ መሆን እንዲችሉ የሚፈቀደው፣ አክሲዮኖችን በውጭ ምንዛሪ ሲገዙ ብቻ መሆኑን ረቂቁ ይጠቁማል፡፡

ረቂቅ መመርያው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት እንዴት መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንዳለባቸው ከመጠቆሙም በላይ፣ የፋይናንስ ተቋማት አክሲዮኖቻቸውን ሲሸጡ ማድረግ አለባቸው የተባሉ ተግባራትንም ያካተተ ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማት አክሲዮኖች ሽያጭ ዝግጅትም ሆነ ተያያዥ የባለአክሲዮኖች ምዝገባ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ አግባብ ብቻ መፈጸም እንደሚኖርበትም ይኸው ረቂቅ ያመለክታል፡፡

የሒሳብ አከፋፈት ምዝገባን በተመለከተም በሚጠቅሰው አንቀጽ ውስጥ የአዲስም ሆነ የነባር ባንክ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም፣ እንዲሁም የመድን (ኢንሹራንስ) ድርጅት መሥራቾች (በምሥረታ ላይ ያለም ቢሆን) የባንኩንና የቅርንጫፉን ስም ጠቅሰው የአክሲዮን ተመዝጋቢዎችን መቀበልና ዝግ የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ መክፈት እንዲችሉ የሚጠይቅ የጽሑፍ ማመልከቻ ወይም የተከፈተውን የሒሳብ ቁጥር ጠቅሰው ብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንዳለባቸው በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

በዚህ መመርያ መሠረት በተጠቀሰው የሒሳብ ቁጥር የተሰበሰበው የውጭ ምንዛሪ የአክሲዮን ምዝገባው ወይም ሽያጭ እንደተጠናቀቀ፣ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረግ እንደሚኖርበት በአስገዳጅነት አስቀምጧል፡፡

የአክሲዮን ምዝገባው ተቀባይነት ባለው የውጭ ምንዛሪ ሊከናወን እንደሚገባው የሚደነግገው ይህ መመርያ፣ ለትውልደ ኢትዮጵያዊያን የውጭ ዜጎች የሚቀርበው አነስተኛ የአክሲዮን መጠን ለነባርም ሆነ ለአዳዲስ የሚሠራ ሆኖ በአዘጋጁ ባንክ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ወይም የመድን ድርጅት የሚወሰን ይሆናል ይላል፡፡

የአክሲዮን ምዝገባው ክፍያ የሚከናወንበት አሠራር በረቂቅ መመርያው እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ዜጎች ለአክሲዮን ግዥ የሚከናወኑ ክፍያዎች ገንዘብ መጠን ወደ ባንክ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ወይም የመድን ድርጅት የሒሳብ ቁጥር በባንክ የስዊፍት ሥርዓት ሊተላለፉ ወይም ገቢ ሊደረጉ እንደሚገባ በረቂቅ መመርያው ተጠቅሷል፡፡

ሆኖም በአገር ውስጥ ባንኮች የውጭ አገር ነዋሪ (ዳያስፖራ) የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የውጭ አገር ዜጎች፣ በሒሳባቸው ካለው የውጭ ምንዛሪ ላይ ለአክሲዮን ግዥ ማስተላለፍ ወይም መጠቀም የሚችሉ እንደሆነም ረቂቁ ያሳያል፡፡

የተመዘገቡ አክሲዮኖችን በማጣራትና በማረጋገጥ በመመርያ የተጠቀሰው ሁሉ የተሟላ መሆኑን አክሲዮኑን ያዘጋጀው ወይም በምሥረታ ላይ ያለው ባንክ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ወይም የመድን ድርጅት መሥራቾች የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

በባንኩ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋሙ ወይም በመድን ድርጅቱ ለአክሲዮን ምዝገባ ወይም ሽያጭ በውጭ ምንዛሪ የተሰበሰበውን ገንዘብ መርምሮ በቀረበለት ሪፖርት መሠረት የማፅደቅ ተግባር፣ በብሔራዊ ባንክ የሚፈጸም እንደሚሆንም ረቂቁ ያመለክታል፡፡

እንዲህ ባለ መንገድ ባለአክሲዮን የሚሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚያገኙትን የትርፍ ክፍፍል፣ እንዴት እንደሚከፈላቸው የሚደነግግ አንቀጽ በረቂቁ ተካቷል፡፡

በየትኛውም የፋይናንስ ተቋም ኢንቨስት ያደረጉ የውጭ ዜግነት ያላቸው ዳያስፖራዎች የሚያገኙት ትርፍ በኢትዮጵያ ብር የሚከፈላቸው ሲሆን፣ ከኢንቨስትመንቱ የሚገኝ ትርፍ ወደ ውጭ አገሮች ተመላሽ እንደማይደረግ ያመለክታል፡፡ የተገኘው የአክሲዮኖች ትርፍ በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ወይም ተቀባይነት ባለው የውጭ ምንዛሪ ለዳግም ኢንቨስትመንት ሊውል እንደሚችል ግን በረቂቁ ተገልጿል፡፡

ረቂቁ መመርያ የፋይናንስ ተቋማት ይመክሩበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አንዳንድ የፋይናንስ ባለሙያዎች ግን ባንኮች አክሲዮን ሸጠው የሚሰበስቡትን የውጭ ምንዛሪ ለምን ለብሔራዊ ባንክ አስገቡ ይባላሉ የሚል ጥያቄ ያስነሳል ብለዋል፡፡ ሌላው የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት ያደረጉና ኑሯቸውም እዚህ በመሆኑ፣ የአክሲዮን ሽያጩ በውጭ ምንዛሪ ብቻ መሆኑ እንዲህ ያሉትን ትውልደ ኢትጵያውያን እንዳይሳተፉ እንቅፋት ስለሚሆን ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች