በኢትዮጵያ የመጀመርያው የግል ባንክ በመሆን የሚጠቀሰውና ከእህት ኩባንያው አዋሽ ኢንሹራንስ ጋር 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን በመዘከር ላይ የሚገኘው አዋሽ ባንክ ካፒታሉን በእጥፍ በመጨመር 12 ቢሊዮን ብር እንደሚያደርስ አስታወቀ፡፡
ከአገሪቱ የግል ባንኮች በሀብት መጠኑና በአትራፊነቱ ቀዳሚውን ደረጃ የያዘው አዋሽ ባንክ፣ ካፒታሉን በዕጥፍ ለማሳደግ የዳይሬክተሮች ቦርድ መወሰኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የባንኩን ካፒታል በዕጥፍ እንዲያድግ በዳይሬክተሮች ቦርድ የተወሰነው ውሳኔ በቅርቡ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የባንኩን አቅም የበለጠ ለማሳደግ ታስቦ የተወሰነው ውሳኔ በአገሪቱ የግል ባንኮች ከፍተኛውን ካፒታል በመያዝ የሚንቀሳቀስ ባንክ ያደርገዋል፡፡
እስካሁንም ድረስ ከ16ቱ የግል ባንኮች የተፈቀደ ስድስት ቢሊዮን ብር ይዞ የቆየው አዋሽ ባንክ ነው፡፡ ከአዋሽ ባንክ ሌላ የተፈቀደ ካፒታላቸው አራትና አምስት ቢሊዮን ብር ያደረሱ ባንኮች አምስት የግል ባንኮች ናቸው፡፡
አዋሽ ባንክ ከ25 ዓመታት በፊት ወደ ሥራ ሲገባ ይዞት የተነሳው 24.5 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንደነበር አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ15 ዓመታት በፊት ከእህት ኩባንያው ጋር በመሆን ከገነባው የመንትያ ሕንፃ ዋና መሥሪያ ቤት ባሻገር፣ አዲስ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ለመገንባት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አስታውቋል፡፡ እንደ አቶ ፀሐይ ገለጻ፣ ለአዲሱ ሕንፃ መገንቢያ ቦታ በቅርቡ እንደሚረከብ ይጠበቃል፡፡ የሕንፃ ግንባታው አዋሽ ባንክን በሚገልጽ ደረጃ ይካሄዳል ብለዋል፡፡