Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ድጋፍ የሚሻው የደም ልገሳ

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያሠራው ባለ ሦስት ፎቅ ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ሕንፃ ባለፈው ሳምንት ተመርቋል፡፡ የደም ባንኩ መገንባት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የሚሰበሰበው ደም በተቀላጠፈ መንገድ ለማከናወን አስችሎታል፡፡ በደም ልገሳው ሥራና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዩች ዙሪያ የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል ባንቲን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ ደላሎች በደም ልገሳ ላይ ተሰማርተው ሲያሻሽጡ ይስተዋላል፡፡ ይህ ዓይነት ሁኔታ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የደም ልገሳውስ እንዴት እየተከናወነ ነው?

አቶ ያረጋል፡- በተለያዩ አገሮች የደም ልገሳው በተለያየ መንገድ ይካሄዳል፡፡ በዚህም መሠረት በአንዳንድ አገሮች ሰዎች ለራሳቸው የሚውል ደም ሲለግሱ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ከሁለት ወራት በኋላ የቀዶ ሕክምና ቀጠሮ ያለው አንድ ታካሚ የራሱን ደም ለደም ባንክ ይሰጣል፡፡ ቀዶ ሕክምናው ሲከናወን ከባንኩ አውጥቶ ይጠቀምበታል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ደም የሚሸጡ አገሮችም አሉ፡፡ ይህም በሕግ የተፈቀደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ደም መሸጥ ክልክል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደም ባንክን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ማለትም ከ2005 ዓ.ም. በፊት ደም የሚለገሰው በአብዛኛው ከበጎ ፈቃደኞች ሳይሆን ከቤተሰብ በምትክ ነበር፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት ደም ይለግሱ የነበሩት አሥር በመቶ ሲሆኑ፣ የቀረው 90 በመቶ ይለገስ የነበረው ከቤተሰብ ምትክ ነበር፡፡ ከቤተሰብ ምትክ ደም የመለገሱ ሁኔታ ብዙ ጉዳቶችና ችግሮች ነበሩበት፡፡ አንደኛው ችግር ለኤችአይቪ፣ ለሄፒታይተስ ቢ እና ሲ መዳረጉ ሲሆን፣ ሁተኛው ችግር ደግሞ ብዙ ቤተሰብ የሌላቸው ሰዎች ደም ለመግዛት መገደዳቸው ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ደላሎችንና ጎዳና ተዳዳሪዎችን በመጠቀም ነው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ በመንገድ ላይ ደም በመሸጥ የሚንቀሳቀሱ ደላሎች ነበሩ፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በሽታን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበሩ፡፡ በደላላ አማካይነት ይካሄድ የነበረው እንቅስቃሴ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቤተሰብ ምትክ ከሚገኘው የደም ልገሳ ይልቅ በበጎ ፈቃደኞች የሚሰጠውን ልገሳ ለማበረታታት ምን እየተደረገ ነው?

አቶ ያረጋል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው ደሙ የራሱ ቢሆንም ሊሸጥ አይችልም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደም የሚያስፈልገው ታካሚ ደም ማግኘት ያለበት ከማያውቀው ሰው በነፃ ሲሰጠው ወይም ሲለገሰው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ብሔራዊ የደም ባንክ በሚገባ ከተደራጀ ወዲህ ከሐረርና ከጅግጅጋ የደም ባንክ ቅርንጫፎች በስተቀር በአዲስ አበባና በቀሩትም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ 41 የደም ባንኮች ከቤተሰብ ምትክ አካሄድ ነፃ ናቸው፡፡ ደም የሚሰበሰበው ከበጎ ፈቃደኛ ሆኗል፡፡ ደም ከቤተሰብ ምትክ በተሰበሰበበት ጊዜ የኤችአይቪ ሥርጭት መጠኑ 3.5 በመቶ ነበር፡፡ ከበጎ ፈቃደኞች መሰብሰብ ከተጀመረ ወዲህ ግን ቁጥሩ ወደ 0.3 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ ከበጎ ፈቃደኞቹ የመሰብሰቡ ሥራ 98.4 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ደም በራሳቸው በበጎ ፈቃደኝነት የሚሰጡ ሰዎች ከበሽታ በጣም ነፃ ናቸው፡፡ የአኗኗር ዘይቤያቸው የተሻለና ኃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው፡፡ የደም ልገሳው በበጎ ፈቃደኞች ላይ ከተመሠረተ ወዲህ ከ1000 በጎ ፈቃደኞች መካከል ኤችአይቪ የተገኘባቸው ሦስት በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎ በ2004 ዓ.ም. 100 ሰዎች ደም ሰጥተው ኤችአይቪ የተገኘባቸው 3.5 በመቶ ያህሉ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ እንደ ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት የበጎ ፈቃደኞችን የደም ልገሳ እናበረታታለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሐረርና ጅግጅጋ የደም ልገሳው ከበጎ ፈቃደኞች ውጪ የሆነበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ያረጋል፡- የምሥራቅ ኢትዮጵያ ነዋሪዎች የሚከተሉት የአኗኗር ዘይቤ ይህ ዓይነቱን አካሄድ የማይከተል በመሆኑ ነው፡፡ ሐረር ላይ የታመመችው አንዲት እናት የሚያስፈልጋትን ደም የምታገኘው ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ሳይሆን ከቤተሰብ ምትክ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ሰው በጎ ፈቃደኛ የሚባለው ስንት ጊዜ ደም ሲለግስ ነው? ቋሚ በጎ ፈቃደኛ የመመዝገቡ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ያረጋል፡- በዓመት አንድ ጊዜም ቢሆን ደም የሚለግስ ሰው በጎ ፈቃደኛ ይባላል፡፡ ቋሚ በጎ ፈቃደኛ የሚባለው ግን በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ደም የሚለግስ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ 4000 በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት 80 ጊዜ ደም የለገሰ በጎ ፈቃደኛ ያለ ሲሆን በሌሎች የሠለጠኑ አገሮች ግን በዓመት 1000 ጊዜ ደም የለገሰ በጎ ፈቃደኛ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው በዕድሜ ዘመኑ 287 ጊዜ ደም መለገስ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከበጎ ፈቃደኞች የሚለገሰው ደም ከኤችአይቪና ከተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች የፀዳ መሆኑንና አለመሆኑን የማጣራቱ ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ ያረጋል፡- ከአንድ በጎ ፈቃደኛ ሰው የሚለገሰው ደም ከኤችአይቪና ከሌሎችም መሰል በሽታዎች ነፃ ለመሆኑ መጀመሪያ የማጣራት ሥራ እናከናውናለን፡፡ ደም ከመለገሱ/ሷ ከ14 ቀናት በፊት ከትዳር አጋር ወይም ከፍቅረኛ ውጪ ግብረ ሥጋ ግንኙነት አድርገው ነበር ወይ? የሚሉና ሌሎችም ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄ በማንሳት ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ጥራቱ በተጠበቀ ላቦራቶሪ ምርመራ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ለባንኩ መጎልበት የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ድጋፉን አቋርጧል ወይስ ቀንሷል? የድጋፉ መጠን ምን ያህል ነበር?

አቶ ያረጋል፡- ዩኤስኤአይዲ ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ለደም ባንክ በየዓመቱ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡ ከ2010 ዓ.ም. በኋላ ግን ራሳችሁን ችላችኋልና የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ አቆማለሁ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት ይደግፋችሁ የሚለውን አቋም ገለጹ፡፡ ድጋፉንም ለማቆም ያነሳሳው ከቤተሰብ ምትክ የደም ልገሳ ተላቅቃችኋል በሚል ምክንያት ነው፡፡ ሲደረግልን የነበረው ድጋፍ በአንድ ጊዜ እንዲቋረጥ መደረጉ ለእኛ በጣም ከባድ ነው፡፡ በዚህም የተነሳው ድጋፉ እንዲቀጥል ድርጅቱን እየተማፀንን ነው፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ መንግሥት ለዚህ ሥራ የተለየ በጀት እንዲመድብልን እየጠየቅን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተለገሰው ደም ለተጠቃሚው እስከሚደርስ ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል?

አቶ ያረጋል፡- አንድ በጎ ፈቃደኛ ደም የሚለግሰው በነፃ ነው፡፡ ምንም ገንዘብ አይፈልግም፡፡ ባንኩ በነፃ የተቀበለውን ደም ፕሮሰስ አድርጎ ለታካሚው እስከሚደርስ ድረስ ብዙ ወጪ አለው፡፡ ነርሷ ከምታደርገው የእጅ ጓንት ጀምሮ የደም መቀበያ ከረጢት የማቅረቡ፣ ደሙ ከኤችአይቪ፣ ከሄፒታይተስ ቢናሲ ወዘተ ነፃ ለመሆኑ የሚካሄደው የምርመራ ሥራ፣ ደም ለጋሹ ደሙን ከለገሰ በኋላ የሚቀርብለት ለስላሳ ወይም ብስኩት ሁሉ ሲታይ ብዙ ወጪ አለው፡፡ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ጥናት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ከረጢት ደም ለታካሚው እስከሚደርስ በአማካይ 82 ዶላር ያስወጣል፡፡ በእኛ ዕይታና ግንዛቤ ግን አንድ በጎ ፈቃደኛ በነፃ በለገሰው ደም ላይ 100 ዶላር ታክሎበት ነው ጥቅም ላይ የሚውለው፡፡ ይህንንም ወጪ ሲደጉም የቆየው ዩኤስአይኤዲ ነበር፡፡ አሁን ግን ቀርቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ደም ባንክን የመደገፉ ሥራ የመንግሥት ድርሻና ኃላፊነት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል ሲታይ ደግሞ መንግሥት ይህን ሁሉ ለመሸፈን የሚያስችል ቁርጠኝነት አለው ለማለት አያስችልም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...