Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢሠማኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያነጋገሩት ጠየቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የደመወዝ ወለል ሕግ እንዲተገበር አሳስቧል

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በወቅታዊ የአገራዊ ጉዳዮችና በሠራተኛው መብት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ ጥሪ በማድረግ የአቋም መግለጫ አወጣ፡፡ የኮንፌደሬሽኑ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲያነጋገሯቸው ጠይቀዋል፡፡

ኢሠማኮ ዋና ዋና ባላቸው ችግሮች ላይ የአቋም መግለጫውን ይፋ ያደረገው ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. 18ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባጠናቀቀበት ወቅት ነበር፡፡ አሥራ አንድ ነጥቦችን ያካተተው የአቋም መግለጫ፣ በተለይ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚጥሱ ተግባራት እንዲገቱ የጠየቀበትና የሠራተኛው የመደራጀት መብት እንዲከበር ያሳሰበበት ይጠቀሳል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታየው የኢንቨስትመንት መስፋፋት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለሥራ ዕድል መፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ የሥራ ዕድል ያገኙ በርካታ ዜጐች ግን በሕገ መንግሥቱ የተጎናፀፉትን መብት የሚፃረሩ ተግባራት እንደሚፈጸሙባቸው ኢሠማኮ አስታውቋል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የተረጋገጠው የመደራጀትና የመደራደር መብትን የሚጋፉ፣ ሠራተኛው በማኅበር እንዳይደራጅ በይፋ የሚከለክሉ፣ ከዚህም አልፈው ጉልበትና ገንዘባቸውን በመጠቀም፣ የተደራጁ ማኅበራትን ያለ ተጨባጭ ምክንያት የሚያፈርሱና የማኅበር አመራር አባላትን ከሥራ ገበታቸው የሚያባርሩ ድርጅቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ኢሠማኮ አስታውቋል፡፡ የሠራተኞች የመደራጀት መብት በበርካታ የግል ድርጅቶች ክልከላ እንደሚደረግበት፣ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በኢንዱስትሪ ዞኖችና በውጭ ኩባንያዎች በኩል ተባብሶ እንደሚስተዋል ኢሠማኮ ይፋ አድርጓል፡፡

በመሆኑም የሠራተኞች በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብት ጥሰትን በጥብቅ እንደሚያወግዝና መንግሥት ጣልቃ በመግባት ሕግ እንዲያስከብር በማለት ጠይቋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የኢንቨስትመንት መስፋፋት የሠራተኛውን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ያመለከተው ኢሠማኮ፣ በርካታ አሠሪዎች ግን ትልቁ ስትራቴጂያቸውና ግባቸው ሠራተኞችን በዝቅተኛ ክፍያ በማሠራት፣ ከፍተኛ ትርፍ ማግበስበስ ብሎም በአጭር ጊዜ ውስጥ የብልፅግና ማማ ላይ መውጣት እንደሆነ አትቷል፡፡ አሠሪዎች በኑሮ እየበለፀጉና እየደረጁ፣ ሠራተኞች ደግሞ የደሃ ደሃ በሚያስብል ደረጃ ‹‹በቀን አንድ ጊዜ እንኳ መብላት የማይችሉ አማራጭ በማጣት የሚሠሩ ናቸው፤›› በማለት ቅሬታውን አሰምቷል፡፡

በአሠሪና ሠራተኛው መካከል ያለውን ከፍተት እንደሚሞላ የሚጠበቀው አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2ዐ11 ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ወይም (Minimum Wage) በመደንገግ ሥራ ላይ ለማዋል እንዲቻል የደመወዝ ወለልን የሚወስን ‹‹የደመወዝ ቦርድ›› እንደሚቋቋም በአዋጁ መካተቱን ኢሠማኮ አስታውሷል፡፡

ይህ ቦርድ እንዲቋቋም በሕግ መደንጉ፣ ‹‹የረዥም ጊዜ ጥያቄያችን ምላሽ ነው፤›› ያሉት የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ለኢንዱስትሪ ሰላም መሥፈንና ለሠራተኛው ኑሮ መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው፣ ኢሠማኮ መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃ አክብሮት እንደሚመለከተው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሠራተኛው ኑሮ እንዲሻሻል፣ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ውስጥ በተቀመጠው ድንጋጌ መሠረት ‹‹ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል›› ተወስኖ በአፋጣኝ እንዲተገበር፣ መንግሥት የደመወዝ ቦርድን በአፋጣኝ አዋቅሮ ጥናቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቅ ኢሠማኮ ጠይቋል፡፡

የሙያ ደኅንነትና ጤንነት አጠባበቅ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል፣ ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲሰፍን፣ አሠሪዎች መውሰድ የሚገባቸው ዕርምጃዎች በሕግ መደንገጋቸውን የሚጠቅሰው የኢሠማኮ መግለጫ፣ በልማት ተቋማትና ኩባንያዎች አካባቢ የሥራ ላይ አደጋን ለመከላከል እንዲቻል ተነሳሽነታቸውና ፍላጐታቸው ዝቅተኛ ሆኖ እንዳገኘው አስታውቋል፡፡

በማምረቻ መሣሪያዎች አጠቃቀም ላይ ለሠራተኞች በቂ ግንዛቤ ሳይፈጥሩ ወደ ሥራ በማሠማራት፣ በብዙ ዜጐች ላይ የአካል ጉድለት እያስከተሉ ነው በማለት ኩባንያዎች ላይ ወቀሳውን ያቀረበው ኢሠማኮ፣ አንዳንድ አሠሪዎች የሥራ ላይ አደጋ መከላከያ ማቅረብን፣ ከወጪ አንፃር እየተመለከቱ ለሠራተኞች እንደማያቀርቡ አስታውቋል፡፡ በሠራተኛው ላይ የአካል ጉዳትና የሞት አደጋ እየተባባሰ ስለመምጣቱም ኢሠማኮ አጣቅሷል፡፡ በመሆኑም የመንግሥትም ሆነ የግል አሠሪዎች፣ ለሠራተኛው ሕይወትና አካል ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና በሕግ የተቀመጡ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ማስጠበቂያ መመርያዎችን እንዲተገብሩ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ የሕጉ አስፈጻሚዎችም ሠራተኞች ለሚደርስባቸው የመብት ረገጣና የሥራ ላይ ጉዳት አጽንኦት እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

ኢሠማኮ በአቋም መግለጫው ትኩረት የሰጠበትና ሊስተካከል ይገባል ያለው ሌላው ጉዳይ፣ በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩና ወደ ግል የተዛወሩ ማምረቻ ተቋማትን በተመለከተ ነው፡፡ ተቋማቱ ወደ ግል ባለሀብቶች ሲዛወሩ በተገባው ውል መሠረት ተረካቢዎቹ ባለሀብቶች ተቋማቱን ማሻሻልና ምርታማ ማድረግ ሲገባቸው ይብሱኑ የተቋማቱን የሥራ እንቅስቃሴ፣ በመንግሥት እጅ ከነበሩበት ደረጃ በታች ወርደው በተዳከመ አቋም ላይ ስለሚገኙ፣ በዚህ ሁኔታቸው የሠራተኞች የሥራ ዋስትና ሥጋት ላይ ከመውደቁም በላይ፣ ለመንግሥት ማስገባት የሚጠበቅባቸውን ልዩ ልዩ ክፍያ እንደማይፈጽሙ ኢሠማኮ በመግለጫው ቢያስታውቅም በአስረጅነት አላቀረበም፡፡  

በተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ ሁከቶች ምክንያት ሠራተኞች በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ላይ መስተጓጐል እያጋጠማቸውና ከሥራ እንዲርቁ የሚያስገድዱ አጋጣሚዎችም እየተበራከቱ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡ ለአብነት ያነሳቸውም የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ፣ የአዶላ ወርቅ ማዕድን ኢንተርፕራይዝና የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ እንዲሁም የሴሮፍታና ጐፈር እርሻ ልማትን የመሳሰሉት ከመበኛው የምርት ሒደት ውጪ በመሆናቸው በበርካታ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ላይ እየደረሰ የሚገኘው የኢኮኖሚ ቀውስና የሥነ ልቦና ችግር ከፍተኛ እንደሆነ ኢሠማኮ አመልክቷል፡፡ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እየወሰደ የሚገኘውን ዕርምጃ  ቢያበረታታም፣ በተቋማቱ ላይ የደረሰው የሥራ መስተጓጐል እንዲስተካከል መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠት የዕርምት ዕርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል፡፡

በአቋም መግለጫው ከተነሱ አንኳር ነጥቦች መካከል በአገሪቱ በሚደረገው ብሔራዊ የፖለቲካ ምርጫ ላይ የተንፀባረቀው የኢሠማኮ አቋም ነው፡፡ በመጪው ምርጫ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ሚናና መርህ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድና መላው የማኅበር አመራሮች ተወያይተውበት በኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት በተወሰነው መሠረት፣ ከአገር አቀፍ እስከ መሠረታዊ ማኅበራት ያሉ አካላት ገለልተኛ በመሆንና የትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይደግፍ እንዲሳተፍ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ሠራተኛው በግሉ ለፈለገው የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት ድምፁን የመስጠት መብቱ የተጠበቀ ሲሆን፣ ምርጫው ላይ ኢሠማኮ በአስፈጻሚነት ሲሳተፍም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ሚና ለመጫወት እንደተዘጋጀም ይፋ አድርጓል፡፡

በሠራተኛው ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያነጋግሩት የጠየቀው ኢሠማኮ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ኃላፊነት ከመጡ ወዲህ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እንዳወያዩ በማስታወስ፣ ሠራተኛውንም እያጋጠሙት በሚገኙ ችግሮች ዙሪያ ‹‹የውይይት መድረክ አመቻችተው እንዲያወያዩን አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› ብሏል፡፡

ከባለሀብቶች ጋር በተያያዘም መንግሥት የኢንቨስትመንት መስፋፋትን መሠረት ያደረገ ባለሀብቶች አቅማቸው እንዲጐለብት ከባንክ የሚፈቅድላቸውን ከፍተኛ ገንዘብ በጊዜው ተቆጣጥሮ ተመላሽ እንዲሆን ያለማድረግ ችግር እንደሚታይበት የጠቀሰው ኢሠማኮ፣ ድርጅቶቹ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ተሽመድምደው እስከ መዘጋት ከመድረሳቸውም በላይ በአገሪቱ ሕግ አግባብ የሚጠበቅባቸውን ታክስ በአግባቡ ባለመክፈል ችግር እየፈጠሩ እንደሚገኙ አትቷል፡፡ በወቅቱ ባለመክፈል ምክንያት ከአቅማቸው በላይ ክፍያ ሲጠየቁ፣ ድርጅቶቻቸውን ዘግተውና ሠራተኞቻቸውን በትነው የሚሄዱ ድርጅቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ መንግሥት የክትትልና የቁጥጥር አሠራሩን እንዲያጠናክር ጠይቋል፡፡ የተከማቸ የመንግሥት ዕዳ ያለባቸው ድርጅቶች አቅማቸው ታይቶና ጊዜ ተሰጥቷቸው በረዥም ጊዜ የሚከፍሉበት ዕድል ተመቻችቶ የሠራተኛው በሥራ የመተዳደርና የመኖር ዋስትና እንዲከበር በማሳሰብ ኢሠማኮ ለመንግሥት አቤቱታውን አሰምቷል፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2ዐ11 በተመለከተም በአዋጁ ከተቀመጡ ድንጋጌዎች መካከል የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ኤጀንሲዎች አስተዳደር ላይ አዳዲስ አንቀጾች በመካታቸው፣ በአዋጁ መሠረት የኤጀንሲዎች አስተዳደር መመርያ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንዲውል ጠይቋል፡፡   

ኢሠማኮ ጥቅምት 12 ቀን 2ዐ12 ዓ.ም. ያካሄደው 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት በኃላፊነት የሚያገለግሉ የጠቅላይ ምክር ቤት አባላትን፣ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ መካከልም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን፣ የኦዲት ኮሚቴ አባላትን፣ እንዲሁም የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን በመምረጥ ተጠናቋል፡፡ ኮንፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት አቶ ካሳሁን ፎሎና አብዛኛዎቹ የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚዎች በድጋሚ ተመርጠዋል፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ከተለያዩ አገሮች የተወከሉ የሠራተኛ ማኅበራት ተጠሪዎች ታድመው ነበር፡፡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የበርካታ አገሮች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች